“ኢየሱስም፦ እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም ። እኔንስ ብታውቁኝ አባቴን ደግሞ ባወቃችሁ ነበር። ከአሁንም ጀምራችሁ ታውቁታላችሁ አይታችሁትማል አለው።” ዮሐ. 14 ፡ 6-7 ።
መንገድ የጠፋው ሰው ይባዝናል ፣ ይንከራተታል ፣ ይንቀዋለላል ፣ ይፈራል ፣ ይጨነቃል ፣ ያገኘውን ሁሉ ይጠይቃል ፣ የነገሩትን ሁሉ ያምናል ፣ እየለፋ ይመለሳል ፣ ፀሐዩ ሲያዘቀዝቅ ዱር ላድር ነው ፣ አውሬ ሊበላኝ ነው ብሎ ይሸበራል ። መንገድ የጠፋው ሰው እዚህ ነኝ ብሎ ለማመልከትም ፣ ያለበትን አድራሻ ለመግለጥም አይችልም ። መንገድ ሲጠፋ የወደፊቱ ብቻ ሳይሆን አሁን ያሉበትም አይታወቅም ። መንገድ ሲጠፋ ብዙ ነገር ይባክናል፡- ጊዜ ፣ ጉልበት ፣ ገንዘብ ፣ ሕይወት ። መንገድ የጠፋው እናውቃለን ባዮች የማያውቁትን መንገድ ሲጠቁሙት እሺ ብሎ ይሄዳል ። ደፋር አላዋቂ ፈሪ አላዋቂዎችን ይመራል ። መንገድ የጠፋው ሰው እርሱ ብቻ አላዋቂ ሰዎች ሁሉ አዋቂ እንደሆኑ ይገምታል ። ሰዎች ለሰዓታት መንገድ ሊጠፋቸው ይችላል ። እስራኤላውያን ግን በምድረ በዳ ለዐርባ ዓመታት ያህል መንገዱ ጠፍቷቸዋል ። ባመኑ ሰዓት መንገዱ ወለል ብሎ ይታያቸዋል ፣ ጠላትም ወዶ ሳይሆን ተሸንፎ ጎዳናውን ይለቅላቸዋል ። ከእምነት ጎድለው በማየት ሲመላለሱ ግን መልሰው የበረሃ አዙሪት ውስጥ ይገባሉ ። ዙሪያውን ቢያዩት ከአድማሱ ጋር የተጋጠመ የአሸዋ ክምር ነው ። ምድረ በዳው ለምልክት የሚሆን አንድ ዛፍ እንኳ አልነበረውም ። የሚመጡትን ለመጠየቅ እንዳይቻል በዚያ መንገድ ማንም አይሄድም ነበር ። ያላቸው ብቸኛው መንገድ እግዚአብሔርን መስማት ነው ። እርሱ በግብጽ ምድር ደመላሽ ፣ በቀይ ባሕር መርከብ ፣ በምድረ በዳ ጓደኛ ፣ በጉዞው መሪ ፣ በበረሃው ጥላ ፣ በቃጠሎው እርካታ ነበረ ። እስራኤልን በበረሃ የመራ ዛሬም በበረሃው ዓለም ይመራናል ።
ብዙ ሰው መንገድ ጠፍቶታል ብንል ማጋነን አይሆንም ። መንገዱን ባገኝ ብሎ ሃይማኖት ይቀይራል ፣ እምነትን በፍልስፍና ይለውጣል ። ጽድቅን በኃጢአት ይተካል ። መድረሻውን ሳያውቅ የሚጓዝ ብዙ ነው ። ብቻ አለመቆም ነው እያለ ሲጓዝ የሚኖር ብዙ አለ ። ፎቅ ላይ የወጣ ወደ ላይ ቢሄድም ወደ ታች ሁለቱም ጉዞ ነው ። ስለሄድን እየደረስን አይደለም ። አለመቆም መሄድ ቢሆንም ግብ ግን ሊሆን አይችልም ። እየተረጋጋን ያለነው ባለመቆም ነው ። ቁልቁል እየወረድን ነው ። ስላልቆምን እየተጓዝን ይመስለናል ። መባዘን ፣ መቦዘን ፣ ሥራ መፍታት ፣ ትርጉም የሌለው ድካም ውስጥ መውደቅ የብዙዎች ኑሮ ነው ። ራስን በማሰቃየት መርካት ፣ ሁሉንም ነገር በጭንቅ ለማግኘት መሞከር ፣ ከአንዱ ሃይማኖት ወደ አንዱ መሰደድ ፣ መምህርን በመምህር መለወጥ ፣ አዋቂ ጠንቋይ መፈለግ ብዙዎችን መንፈሳዊ ዘማ ያደረገ ነው ። አልተቀመጡ ፣ አልቆሙ ፤ አልተራመዱ ፣ ወይ አልደረሱ ብዙዎች በመንቀዋለል ሽቅብና ቁልቁል ይላሉ ። እስከ ዛሬ የሄዱበት የኃጢአት መንገድ እረፍት እንደሌለው ቢገባቸውም ወይ ከቃለ እግዚአብሔር አሊያም ከኪሣራቸው መማር አልቻሉም ። መንገድ ሲጠፋ የሚከፈለው ዋጋ ብዙ ነው ። ከተጠሩበት ዘመን አንጻር አስተማሪ መሆን ሲችሉ ዛሬም መንገዱን ያላገኙ አያሌ ናቸው ። መንገዱን አለማግኘት ፈሪ ፣ ተጨናቂ ፣ ሁልጊዜ በጥያቄ ውስጥ ነዋሪ ያደርጋል ። መኖርም መሞትም ሊያስፈራ ይችላል ።
ጌታችን ወዳለበት የሚያደርሰውን መንገድ እንፈልጋለን ። እርሱ የነፍስ ጥማት ነውና የማይፈልገው ሰው የለም ። ያለ እርሱም እፎይ ማለት የማይቻል ነው ። ሩጫ ምንም መልካም ቢሆን የሚሸለመው የጀመረው ሳይሆን የፈጸመው ነው ። ብዙዎች ይጀምራሉ ፣ ግን መፈጸም አይችሉም ። መንገዱም ክርስቶስ ግቡም ክርስቶስ መሆኑን ማወቅ ፣ እርሱ አስጀማሪና አስፈጻሚ አልፋና ዖሜጋ መሆኑን መረዳት ልብን የሚያስደስት ነው ። በየትም ዓለም መንገድ የጠፋውን ሰው መንገደኛ ሁሉ ይራራለታል ። በአንዳንድ አገር ቆመው በትክክል ያመለክታሉ ፣ በሌላ አገር ትንሽ አብረው ተጉዘው በዚህ በኩል ሂድ ይላሉ ። ከሁሉ የሚያረካው ፣ ልብን ከፍርሃት ነጻ የሚያወጣው እኔም ወደዚያው ነኝ አብረን እንሄዳለን የሚል ወዳጅ ከተገኘ ነው ። በእውነት ሁላችንም የጽዮን መንገደኞች ነን ። አብረን ብንጓዝ ስጋት ይቀንሳል ፣ አብረው ሲጓዙ ሽፍታም ፣ ቀማኛም አያሰጋም ፣ አብረው ሲጓዙ ሳቁ ጨዋታው መንገድ ያጋምሳል ፣ አብረው ሲጓዙ ስንቅ ይቃመሱ ።
ያለ መንገድ መድረስ የለም ። ያለ ክርስቶስም ሰማይን መውረስ አይቻልም ። ምሥጢረ ጥምቀትና ምሥጢረ ቍርባን መሠረቱ ምሥጢረ ሥጋዌ ነው ። የምሥጢረ ሥጋዌ መሠረትም ምሥጢረ ሥላሴ ነው ። ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል ሰው ሆኖ በአንድ አካልና ባሕርይ ተገልጦ በመስቀል ላይ ሞቶ መንገዱን ከፍቶልናል ። እርሱ መንገድ ነው ፣ ወደ ዘላለማዊ አባቱ ያደርሳል፤ ወደ ሕይወት እልፍኝ ያስገባል ። እርሱን ወልድ ዋሕድ ብሎ ማመን የዘላለም ሕይወት ያሰጣል ። ቅድመ ዓለም ከአብ ያለ እናት የተወለደውና ድኅረ ዓለም ከድንግል ማርያም ያለ አባት የተወለደው አንድ ክርስቶስ ብሎ ማመን እርሱ የመጨረሻው እውነት ፣ የሚያድነው ሕይወት ነው ። ያለ ክርስቶስ እውነትን ማወቅ ፣ ያለ ክርስቶስ በሕይወት መኖር አይቻልም ። የደመ ነፍስ ሕይወትን እንስሳትም እየኖሩት ነውና በዚያ የሚመካ ካለ እንደ እንስሳ ኖሮ ማለፍ ይችላል ፤ ክርስቶስ ግን ዘላለማዊ ሕይወትን ይሰጣል ።
ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ታኅሣሥ 24 ቀን 2017 ዓ.ም.