“ቄሬኔዎስ በሶርያ አገር ገዥ በነበረ ጊዜ ይህ የመጀመሪያ ጽሕፈት ሆነ።” ሉቃ. 2፡2።
አውግስጦስ ቄሣር ብዙ ቆጠራዎችን አከናውኗል ። እስከሚሞትበት ዓመት እስከ 14 ዓ.ም. ድረስ ለሦስት ጊዜ ያህል የሕዝብ ቆጠራ ያደረገ ሲሆን በሁለተኛው ቆጠራ ክርስቶስ ተወለደ ። ክርስቶስ የተወለደው ቄሬኔዎስ የተባለው የሮማ ጀነራልና የሶርያ ገዥ አካባቢውን በሚያስተዳድርበት ዘመን ነው ። የመጀመሪያ ጽሕፈት የተባለው ለቄሬኔዎስ ነው ። ሉቃስ በጥንቃቄ ይጽፋል ። የጥንት የዘመን አቆጣጠር ነገሥታት በነገሡበት ዓመትና ዘመን ላይ ይመሠረታል ። በከተሞች ምሥረታ ለምሳሌ በሮም አመሠራረት ላይ የሚጀመር አቆጣጠር አለ ፣ በወንዞች ሙላት ላይም ሊመሠረት ይችላል ። በክርስቶስ መወለድ ግን ዓመተ ምሕረት ተብሎ ዓለም አቆጣጠሩን ወጥ አደረገው ። የዘመናት ጌታ ዘመንን ወረሰው ።
ዘላለማዊው በጊዜ ውስጥ ገባ ። ላለፉት ሁለት ሺህ ዓመታትም ዓመተ እግዚእ የጌታ ዓመት ፣ ዓመተ ምሕረት ብለን የምንጠራው በጌታችን ልደት ነው ። ሕግን የሰጠው ከሕግ በታች ሆነ ። ሕገ ተፈጥሮን ፣ ሕገ ጠባይያትን ፣ ሕገ ኦሪትን ፣ ሕገ ሕፃናትን ጠበቀ ። ፈጣሪ ፍጡር ሥጋን ተዋሐደ ። ልዑል ወደ ወራዳው ዓለም መጣ ፣ የተዋረደው ሰው ወደ ዙፋነ መለኮት ወጣ ። ሊያድነን የሞተው ጌታ ሰው ሊያደርገን ሰው ሆነ ። ልደቱ የብርሃን መስኮት ነው ። የድኅነትም ጅማሬ ነው ። ቤዛ ኵሉ ዓለም ዛሬ ተወለደ የምንለው ልደትና መስቀል አንድ ስለሆኑ ነው ። አንዱ መነሻ አንደኛው ፍጻሜ ናቸው ። በልደት ቀን ሞት አይወራም ። ሕፃን ሁሉ ለመኖር ይወለዳል ፣ ክርስቶስ ግን ለመሞት ተወለደ ። ሞትን ዓላማ አድርጎ ተወልዷልና ዘመኑ ሁሉ ፍኖተ መስቀል /የመስቀል መንገድ ነው ።
ልደቱ በፍጹም ድንግልና ነው ። በዝግ መቃብር የተነሣው ጌታ በዝግ ማኅፀን ተወለደ ። ልደቱና ትንሣኤው ይነጋገራሉ ። ዛሬም በተዘጋው ልባችን ገብቶ ሰላምን ማወጅ ይቻለዋል ። ልደቱ ድንግል ማርያምን ያገኘንበት ፣ ያወቅንበትም ነው ። እግዚአብሔር ለሰው ያለውን ክብር ሰውን ወክላ የተቀበለች የታደለችው ድንግል ማርያም ናት ። ልደቱ ባይኖር ነቢያት ፣ ነቢያት አይባሉም ነበር ። ልደቱ ሰማዕታትን ያፈራ ነው ። ሕፃን ሲወለድ ሰዎች ከበው ፣ እየተራዱ ነው ። ድንግል ማርያም ግን ስትወልድ ከአረጋዊው ዮሴፍ ውጭ ማንም አልነበረም ። ሰው ነሥቶ ምጥ አይሰጥምና እርስዋ ያለ ምጥ ወለደችው ። ያለ ድካም ከአባቱ የተወለደው ፣ ያለ ሕማምም ከድንግል ተወለደ ። ዛሬ የሰው ልጆች ተሰባስበው ልደቱን ያከብራሉ ፣ ድንግል ማርያም ግን ብቸኛ ነበረች ። ክርስቶስ ያለው ብቸኛ አይባልምና ሕይወቷ መምህራችን ሁኖ ይኖራል ። ሁሉን የያዘው ጌታ እናት ሁሉም ነገር አልነበራትም ። ጸጋ የበዛላት ብትሆንም ድህነት ግን ጸናባት ።
ሲፈጥረን በኃይል ነው ፣ ሲያድነን ግን ደካማ ሥጋ ለብሶ ነው ። ድኅነትን የሚያውጅ ፣ ልብን የሚለውጥ ፣ ሕይወትን የሚያከብር የጌታ ልደት እንዴት ልዩ ነው ! ሰማያውያን እንድንባል ምድራዊ ሆነ ፣ የእግዚአብሔር ልጆች ሊያሰኘን የሰው ልጅ ተባለ ። እርሱ ተወልዶ ያበቃ አይደለም ፣ በየዕለቱ በሚያምኑት ልብ ይወለዳል ። ለመወለድ በረትን የመረጠ ፣ ዛሬ ግን ንጹሕ ልብን ፈለገ ። ክርስቶስ የተወለደው ለበግና ለዶሮ ድግስ አይደለም ፣ የመንፈስ ቅዱስን ደስታ ሊመልስልን ነው ። ሰማይ እስከ ዛሬ ሩቅ ነበረ ። “ሰማይ ሩቅ አደራ ጥብቅ” ይባል ነበረ ። በልደቱ ሰማይ ቀረበ ። ለአደራ የሚበቃ ትውልድም በቀለ ። ለአማኝ ምድር ሩቅ ፣ ሰማይ ቅርብ መሆን ጀመረ ። ስለ ድኅነቱ ከመላእክት ጋር መዘመር የቻለው አማኝ የገዛ ቤተሰቦቹ እንደ ጠላት የሚያዩበት ቀን ዛሬ ተጀመረ ።
ያልተዋሐደውን አላዳነውም የሚለው ቋሚ መርሕ ነውና ክርስቶስ ሥጋችንንና ነፍሳችንን ተዋሐደ ። ልደቱ ከድኅነት ጋር እንጂ ከምድራዊ ሆታ ጋር ግንኙነት የለውም ። ልደቱ ታሪክ ሳይሆን ሕይወት ነውና ዮም ተወልደ- ዛሬ ተወለደ ብላ ቤተ ክርስቲያን ትዘምራለች ። በሃይማኖት ውስጥ ትላንት የለም ፣ ሁሉም ነገር አሁን ነው ። መዳን እግዚአብሔር ሰውን መቀበሉ ነው ። ሥጋና ነፍሳችንን በመዋሐዱ መዳናችን እርግጥ ሆነ ። ከዚህ በላይ እንዴት ይቀበለን ? ስንፈጠር በቤቱ ሊቀበለን ነበር ፣ ስንድን ግን አካላችን ሆነ ። ከእንግድነት ወደ ሥጋ ዘመድነት መጣን ። ለካ ኃጢአት በበዛበት ጸጋ ይበዛል! ልደቱ የፈውሳችን መድኃኒት ቅመማው ተጀመረበት ። መድኃኒት መራራ ነውና መራራ ሞትን ተቀበለ ። በልደቱ ቀንም መራራው ሐሞት ቤዛነቱን ለመግለጥ ስጦታ ሆኖ ቀረበለት ። ከባርነት ሊያወጣን ከሕግ በታች ሆነ ። እርሱ ሁልጊዜ እውነት ነው ። አምላክነቱ እውነት ነው ብለን ካመንን በእውነትም ሰው ሆኗል ብለን እናምናለን ።
የልደቱ ብርሃን ከሁላችን ጋር ይሁን!
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ታኅሣሥ 29 ቀን 2018 ዓ.ም.