መግቢያ » ልዩ ልዩ አንድ » ክርክር እንዳልገጥም

የትምህርቱ ርዕስ | ክርክር እንዳልገጥም

ላንኳኳ የምትከፍት ፣ ለሻህ የምትገኝ ፣ ለለመነህ የምትሰጥ ፣ ለተማጸነህ የምትደብቅ ፣ ለተጨነቀ የምትደርስ ፣ ለፈረሰበት የምትጠግን ተለማኝ እግዚአብሔር ሆይ ተመስገን ። ትጉሃን መላእክት ሳሉልህ እንቅልፋሙን እኔን ትቀሰቅሳለህ ፣ የተቀደሰ ሰማይ ሳለህ ወዳረከስነው ምድር ትመለከታለህ ። ሳትቸገር ሰውን ትፈልጋለህ ፣ እንኩ ለማለት ደጅ ትጠናለህ ። የተማጸኑብህን አሳልፈህ የማትሰጥ ፣ ሲጠጉህ የምትምረው ፣ ሲርቁህ ተመለሱ የምትለው አንተ ቸር ነህ ። በምድር ላይ መኖሪያ ቤትና መቀበሪያ አፈር ላጣ በሰማይ ርስት ሰፍረህ ትጠብቀዋለህ ። ፍጹም ደሀውን ፍጹም ባለጠጋ ለማድረግ ትተጋለህ ። በምድር የተበደሉትን በሰማይ ትክሳለህ ። ነፍሱ የደቀቀችበትን በምክርህ ትጠግናለህ ። ቆይ እያለ ቀጠሮ ያበዛውን ሰብረህ ትገሥጸዋለህ ።
ጻድቃን አሉኝ ብለህ ኃጥአንን አትንቅም ። አመስጋኙ ዳዊት ሳለልህ የማይረካውን ሳኦልን ትመክራለህ ። በደብርህ የጸና ሙሴ ሳለህ ከደብር በታች የሚበድልህን አሮንን ትታገሣለህ ። የመዓትህን ሰይፍ በትዕግሥትህ ሰገባ ትከተዋለህ ። ቊጣውም ምሕረቱም ያንተ ሲሆን ምሕረትህን ትናኛለህ ። አንተ ታላቅ ነህ ።
ዓይኖቼ ወደ ሞት ሸለቆ ሲመለከቱ አንተ ግን የብርሃን ተራራን ታሳያቸዋለህ ። እግሮቼ መጽናት ሲያቅታቸው አንተ ግን መርገጫውን ዓለት ታደርግላቸዋለህ ። አንደበቴ ምስጋናን ሲነጥፍ አንተ ግን የሚያስደንቅ ነገርን ታደርጋለህ ። እጆቼ ምሰሶ ሲፈልጉ እጆችህን ትዘረጋለህ ። አንድ ጊዜ አስበኝ ስልህ እልፍ ጊዜ ድል ትሰጠኛለህ ። ዝናህን የገደበ ክፉ ፣ ምስጋናህንም የጨረሰ ቅዱስ የለም ። በልደትህ ሰውና መላእክትን ያስማማህ ፣ በመስቀልህ ከጠፋው ዓለም ጋር አንተው ክሰህ የታረቅህ ፣ በትንሣኤህ የድል ሠራዊት ያደረግኸን አንተ ነህ ። ምስጋናችንን ከወደድከው እንካ ተቀበለው ።
የፍቅርህ ብርሃን ልቡናዬን ያብራው ። ልመናዬም በፊትህ ሞገስ ያግኝ ። የደስተኞች ደስታ ያስደስተኝ ። የመልካሞች ሩጫ ያስፈንድቀኝ ። መልካም ዜናን ለመስማት ልቡናዬን አዘጋጅልኝ ። ሰባሪ ቀኖችን ለማለፍ ኃይል ስጠኝ ። የምክርህ ጠል ያረስርሰኝ ። ትምህርትህ በእውቀት ያንጸኝ ። ያማረ አነጋገር ፣ የተወደደ አንደበት ስጠኝ ። የተቀበልሁ ነኝና ለመስጠት እንዳልፈተን እርዳኝ ። ከትልቁ ጌታ ካንተ ጋር ክርክር እንዳልገጥም ማስተዋል ስጠኝ ። ለዘላለሙ አሜን ።
የነግህ ምስጋና /3
የካቲት 17 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ

አዳዲስ መጻሕፍት

ትርጉሙ:- ቀይ ዕንቈ

ለምድራችንና ለአገልግሎታችን በረከት የሆነ መጽሐፍ
የመጀመሪያ እትም ጥቅምት 2016 ዓ.ም

1ኛ ጢሞቴዎስ ትርጓሜ – ክፍል አንድ

የመጀመሪያ እትም ሐምሌ 2013 ዓ.ም

ምክር አዘል መጽሐፍ

የመጀመሪያ እትም