ቅዱስ ጎርጎርዮስ ፓላማስ እንደ ሰበከው
የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ እሑድ ሚያዝያ 25/2012 ዓ.ም.
ቃሉና ምሥጢሩ ከራሱ ከምልክቱ አስቀድመው ስለመጡ እነርሱን አስቀድመን ልናብራራላችሁና ልንተረጉምላችሁ ይገባል ። ቅዱስ ጳውሎስ ከእኛ አስቀድሞ ተርጉሞአቸዋል ። በመስቀሉ የሚመካው ጳውሎስ ጌታ ኢየሱስ እርሱም እንደ ተሰቀለ ከዚህ ውጪ ሌላ እንዳያውቅ ቆረጠ (ከ1ኛ ቆሮ 2፥2 ጋራ ያነጻጽሩ)። ምንድር ነው ያለው ? መስቀል ማለት ሥጋን ፣ ከክፉ ምኞቱና መሻቱ ጋር መስቀል ነው (ከገላ 5፥24 ጋራ ያነጻጽሩ)። ስለ አካላዊ ደስታ ስሜቶችና ስለ ሆዳምነት ብቻ እየተናገረ ይመስላችኋልን ? እንደዚያ ቢሆንስ ለቆሮንቶሳውያን እንደዚህ ብሎ ባልጻፈ ነበር “ቅናትና ክርክር ስለሚገኝባችሁ ሥጋውያን መሆናችሁ አይደላችሁምን?” (1ኛ ቆሮ 3፥3)። ስለዚህ ገንዘብ አልያም ክብርና ዝና የሚወድ አልያም አሸናፊ ለመሆን የራሱን ፈቃድ (ሌሎች ላይ) የሚጭን ማንኛውም ሰው እንዲህ ያሉ ነገሮች የመከፋፈል ምንጭ ናቸውና ሥጋዊ ነው ኑሮውም እንደ ሰው ነው።[1]የጌታ ወንድም ያዕቆብ እንዳለው “በእናንተ ዘንድ ጦርና ጠብ ከወዴት ይመጣሉ? በብልቶቻችሁ ውስጥ ከሚዋጉ ከእነዚህ ከምቾቶቻችሁ አይደሉምን? ትመኛላችሁ ለእናንተም አይሆንም፤ ትገድላላችሁ በብርቱም ትፈልጋላችሁ፥ ልታገኙም አትችሉም፤ ትጣላላችሁ ትዋጉማላችሁ ነገር ግን አትለምኑምና ለእናንተ አይሆንም” (ያዕ 4፥1–2)። ሥጋን ከምኞቱና ከመሻቱ ጋር መስቀል ማለት እግዚአብሔርን ደስ የማያሰኙ ነገሮችን ሁሉ መተው ማለት ነው። ግዙፉ ሰውነታችን/ሥጋችን ቢያውከንና ተጽእኖ ቢያሳድርብንም በፍጥነት ወደ መስቀሉ ከፍታ ከፍ እናደርገው ዘንድ ይገባል። ምንድር ለማለት እየሞከርኩ ነው? ጌታ በምድር ላይ በነበረ ጊዜ የድህነት ኑሮ ነበር የኖረው። ድህነትን መኖር ብቻ ሳይሆን እንዲህ በማለትም ሰበከው “እንግዲህ እንደዚሁ ማንም ከእናንተ ያለውን ሁሉ የማይተው ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም” (ሉቃ 14፥33)።
ወንድሞቼና እህቶቼ ማናችሁም ብትሆኑ ንጽሕ በሆነ መንገድ መልካም፣ ተገቢና ፍጹም የሆነውን የእግዚአብሔርን ፈቃድ ስናውጅ ስትሰሙን አትቆጡ አትበሳጩም። አልያም እነዚህ ነገሮች ፍጹም ሊደረሱ የማይችሉ በመሆናቸው አትታወኩ። በመጀመሪያ መንግሥተ ሰማያት የምትገፋ እንደሆነችና ግፈኞችም እንደሚናጠቋት ልብ በሉ (ማቴ 11፥12)። እንዲህ የሚለውን የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት አለቃ የሆነውን ጴጥሮስን ስሙት “ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሎአልና” (1ኛ ጴጥ 2፥21)። ከዚህም በመቀጠለ አንድ ሰው ምን ያህል የጌታው ባለ ዕዳ እንደሆነ ሲያውቅና ሙሉውን መክፈል እንደማይቻለው ሲረዳ ትሑት በመሆን የሚችለውን ሁሉ ይሰጣል ፤ ይህንንም ነጻ ሆኖ በመምረጥ ያደርገዋል። ስለ ቀረው ዕዳ ራሱን በጌታ ፊት ትሑት ያደርጋል ፣ በትሕትናውም ምሕረቱንና ርኅራኄውን በመቀበል የጎደለውን ይሞላል። አንድ ሰው ልቡናውና አእምሮው ወደ ሀብትና ንብረት እንደሚባዝን ከተረዳ ይህ ሥጋዊ አሳብ በውስጡ ከተሰቀለው ክርስቶስ እንደለየው ማወቅና መረዳት አለበት።
ይህንን አሳባችሁን ወደ መስቀሉ ከፍታ ከፍ ለማድረግ እንዴት መጀመርን ትችላላችሁ? ለፍጥረት ሁሉ የሚሰጠውንና ሁሉንም የሚመግበው ክርስቶስ ላይ ተስፋችሁን ጣሉ። ኢፍትሐዊ ከሆነ ማግኘት ራቁ። ከሐቅና በላባችሁ ካገኛችሁት ገንዘብ ጋር እንኳን አብዝታችሁ አትቆራኙ፣ አትሳቡ አትውደዱትም። ለበጎ ምግባር አድርጉት ፣ ድሆች የሚቻለውን ያህል ይካፈሉ። ይህ ራስን ክዶ መስቀልን ከመሸከም ትእዛዝ ጋር ተመሳሳይ ትእዛዝ ነው። እንደ ፈቃዱ የሚኖሩ የእግዚአብሔር ሰዎች ሥጋ/ሰውነት ያላቸው ቢሆኑም ከእርሱ ጋር አብዝተው የተቆራኙ አይደሉም። በተቃራኒው አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ አስተዋጽኦውን ይጠቀማሉ። (ከሥጋ) ይነጠሉ ዘንድ ሲጠሩ ያደርጉት ዘንድ ዝግጁ ናቸው። ስለ ሥጋ ፍላጎትና ባሕርይ እንደዚህ ካደረጋችሁ ከዚህ በላይ አንዳች ማድረግ ባትችሉ እንኳን ይህ (ብቻውን) መልካምና እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ነው። የዝሙት አሳብ በውስጣችሁ በኃይል ሲነሣ ተመለከታላችሁን? (እንዲህ ከሆነ) አሁንም ራሳችሁን እንዳልሰቀላችሁ እወቁ። ይህ እንዴት ሊተገበር ይችላል? ሴቶችን በጥልቀት፣ በጉጉትና በመደነቅ ከመመልከት ሽሹ። ከእነርሱ ጋር ካለ አላስፈላጊ ከሆነ ቅርበትና አላስፈላጊ ከሆነ ንግግር ራቁ። መጠጣት፣ መስከር፣ እስክትጠግቡ ድርስ መመገብና አብዝቶ መተኛት በመተው ለዚህ ስሜት ጉልበት የሚሰጡትን ነገሮች ቀንሱ። እነዚህን ክፉ ነገሮች ከመተው በተጨማሪ ትሑት ልቡናን ጨምሩበት እነዚህን ስሜቶች ለመዋጋት ይረዳችሁ ዘንድ በጭምት ልብ ወደ እግዚአብሔር ተጣሩ። ከዚያ በኋላ፡- “ኃጥእን ከፍ ከፍ ብሎ እንደ ሊባኖስ ዝግባም ለምልሞ አየሁት። ብመለስ ግን አጣሁት ፈለግሁት ቦታውንም አላገኘሁም” (መዝ 36(37)፥35–36)።
ክብርን በመውደድ አሳብ ተቸግራችኋልን? በጉባኤ አልያም በስብሰባ መሐል ስትሆኑ ጌታ በወንጌል ስለዚህ ጉዳይ የተናገረውን ምክር አስታውሱ። በምትናገሩበት ጊዜ ሌሎች ላይ የበላይ ለመሆን አትሞክሩ። ያላችሁን መልካም ምግባር ለእርሱ ብቻ በማሳየትና በእርሱ ብቻ በመታየት በስውር ተግብሩ። “በስውር የሚያይ አባትህም በግልጥ ይከፍልሃል” (ማቴ 6፥6)። የሁሉንም ክፉ ስሜቶች ምንጭ ከቆረጣችሁ በኋላ አሳባቸው በውስጣችሁ ያናውጻችኋል። በዚህም አትፍሩ። ያስቸግራችኋል ሆኖም ግን ፈጽሞ ድል አያደርጋችሁምና ሕያውም አይደለምና አክሊልን ያስገኝላችኋል። መንፈሳዊ በሆነ ትግላችሁ ድል የተደረገ ሙት የሆነ እንቅስቃሴ ነው።
የመስቀሉ ቃል እንዲህ ነው (1ኛ ቆሮ 1፥19 ጋር ያነጻጽሩ)። (የመስቀሉ ቃል) ከመፈጸሙ አስቀድሞ በነቢያት ጊዜም ብቻ ሳይሆን አሁንም ከተፈጸመ በኋላም ታላቅና መለኮታዊ ምሥጢር ነበረ ነውም። ይህ ለምን ሆነ? በሁሉም ነገሮች ራሱን ትሑትና ዝቅ የሚያደርግ ራሱ ላይ ንቀትን የሚያመጣ ይመስላል። ሥጋዊ ፍላጎቶችን የሚሸሽ ማናኛውም ሰው ራሱ ላይ ብርቱ ድካምና ልፋት ብሎም ኀዘን የሚያመጣ ይመስላል። ያለውን ጥሪት የሚሰጥ ራሱን ድሀ የሚያደርግ ይመስላል። ነገር ግን በእግዚአብሔር ኃይል ይህ ድህነት፣ ኀዘንና መናቅ በዚህና በሚመጣው ዓለም የማያልቅ ሀብት፣ በቃላት የማይገለጥ ደስታና ዘላለማዊ ክብርን ይወልዳል። ጳውሎስ ይህንን የማያምኑትንና እምነታቸውን በተግባር የማይገልጡትን ከጠፉት አልያም ከግሪካውያን ጋር ይደምራቸዋል። “እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን” ይለናል (አይሁድ) አዳኝ የሆነውን (የክርስቶስ) መከራ ስለማያምኑ “ይህም ለአይሁድ ማሰናከያ” (አሕዛብ/ግሪኮች) የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ፈጽመው ባለማመናቸውም ምክንያት ከሁሉም በላይ ለጊዜያዊና ኃላፊ ለሆኑ ነገሮች ዋጋ ስለሚሰጡ “ለአሕዛብም ሞኝነት ነው” (ካለ በኋላ) “ለተጠሩት ግን፥ . . . የእግዚአብሔር ኃይልና የእግዚአብሔር ጥበብ የሆነው ክርስቶስ ነው” ይላል (1ኛ ቆሮ 1
፥23)።
፥23)።
በድካም ድል ማድረግ፣ ዝቅ በማለትና በትሕትና ከፍ ማለት፣ በድህነት ባለ ጸጋ መሆን ይህ የእግዚአብሔር ጥበብና ኃይል ነው። መለኮታዊ የሆነው ክብር የሚያስፈልጋቸው የመስቀሉ ቃልና ምሥጢር ብቻ ሳይሆኑ ምልክቱም ጭምር እንጂ። ምልክቱ ቅዱስ፣ አዳኝና ክቡር ማኅተም ነው። እግዚአብሔር ለሰው ዘር በሙሉ ያደረገውን መልካም፣ ድንቅና ከቃላት በላይ የሆነውን ነገር ሁሉ መቀደስና ፍጹም ማድረግ የሚቻለው ነው። እርግማንንና ኩነኔን ማስወገድ፣ ሞትንና መበስበስን የሚያጠፋ፣ ዘላለማዊ ሕይወትና በረከትን የሚሰጥ ነው። ምንም እንኳን የምንፍቅና ተከታዮች በቅናት የሚከፉና ቅር የሚሰኙ ቢሆኑም መስቀል የድኅነት እንጨት[2]፣ በትረ መንግሥት፣ በሚታዩና በማይታዩ ጠላቶች ላይ መለኮታዊ የድል ሽልማት/አክሊል ነው። እንዲህ የሚለውን የሐዋርያውን ጸሎት አልደርሱበትም “ከቅዱሳን ሁሉ ጋር ስፋቱና ርዝመቱ ከፍታውም ጥልቅነቱም ምን ያህል መሆኑን ለማስተዋል፥ ከመታወቅም የሚያልፈውን የክርስቶስን ፍቅር ለማወቅ ትበረቱ ዘንድ” (ኤፌ 3፥18)። የጌታ መስቀል በሥጋ የመምጣቱን ምሥጢር በሙላት እንደሚገልጽና የዚህን መገለጥ ሙሉ ምሥጢር እንደያዘ አልተረዱም። በሁሉም አቅጣጫዎች በመስፋት ከላይ፣ ከሥር፣ በዙሪያና በመካከል ያለውን ነገር ሁሉ ይይዛል። መናፍቃኑ ሰበብ በመደርደር ምክንያታዊ ቢሆኑ ከእኛ ጋር በኅብረት ሆነው ያከብሩት ዘንድ የሚገባውን የክብርን ንጉሥ (መዝ 23(24)፥7–10) ምልክት ይጠየፋሉ። ጌታም ራሱ በግልጽ መስቀሉን ሊያከብር ከፍ ማለቱና ክብሩ እንደሆነ ጠቁሟል (ዮሐ 3፥14–15)። ዳግም ሲመጣና ራሱን ሲገልጥ ይህ የሰው ልጅ ምልክት በኃይልና ከታላቅ ክብር ጋር እንደሚመጣ አውጇል (ማቴ 24፥30)።
መናፍቃኑ ክርስቶስ መስቀል ላይ ተቸንክሮ ስለ ሞተ እርሱ የሞተበትን የመስቀል ምልክት መመልከት አቅም እንደሌላቸው ይናገራሉ። ነገር ግን እኛ ባለመታዘዛችን ምክንያት አባታችን (አዳም) እጁን ወደ ዛፉ በዘረጋ ጊዜ በእኛ ላይ ተጽፎ የነበረው የዕዳችንን ጽሕፈት የት ነበር የተጠረቀው? [3]ወደ እግዚአብሔር በረከት እንድንመለስ አድርጎ ከመንገዳችን እንዴት ነበር የተወገደውና የተቀደደው ? ከመተላለፍ ዛፍ በኋላ ሰልጥነውብን የነበሩትን የርኩሳን መናፍስትን አለቆችና ሥልጣናት ክርስቶስ መቼ ነበር የገፈፈውና ያባረረው? እኛ ነጻ እንወጣ ዘንድ ድል ያደረጋቸውና ያሳፈራቸው የት ነው ? በመካከል የነበረው የጥል ግድግዳ የፈረሰው ከእግዚአብሔር ጋር የነበረው ጠላትነታችንም የሞተውና የተወገደው የት ነው ? ከእግዚአብሔር ጋር በምን ዓይነት መንገድ ነበር የታረቅነው? ከእርሱም ጋር መልካሙን ዜና ወንጌልን እንዴት ነበር የሰማነው? እርግጥ ነው መስቀሉ ላይና በመስቀሉ ነበር። ይህንን የሚጠራጠሩ ሐዋርያው ለኤፌሶን ሰዎች የጻፈውን ያድምጡ “እርሱ ሰላማችን ነውና፤ ሁለቱን ያዋሐደ በአዋጅ የተነገሩትንም የትእዛዛትን ሕግ ሽሮ በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳን በሥጋው ያፈረሰ፤ ይህም ከሁለታቸው አንድን አዲስን ሰው በራሱ ይፈጥር ዘንድ ሰላምንም ያደርግ ዘንድ፥ ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ በእርሱ ሁለታቸውን በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው”(ኤፌ 2፥14–16)። ለቆላስይስ ሰዎች ደግሞ እንዲህ ብሎ ጻፈ “እናንተም በበደላችሁና ሥጋችሁን ባለመገረዝ ሙታን በሆናችሁ ጊዜ፥ ከእርሱ ጋር ሕይወትን ሰጣችሁ። በደላችሁን ሁሉ ይቅር አላችሁ። በእኛ ላይ የነበረውን የሚቃወመንንም በትእዛዛት የተጻፈውን የዕዳ ጽሕፈት ደመሰሰው። እርሱንም በመስቀል ጠርቆ ከመንገድ አስወግዶታል። አለቅነትንና ሥልጣናትን ገፎ፥ ድል በመንሣት በእርሱ እያዞራቸው በግልጥ አሳያቸው” (ቆላ 2፥15–15)።
በእውነት ይህንን የሁሉም የሰው ልጆን ነጻነት መለኮታዊ ሽልማት የሆነውን (መስቀል) ልናከብረው ይገባል። መልክና ገጽታው ብቻ የክፋት አባት የሆነውን እባቡን መሸነፉንና መቀጥቀጡን በማወጅ አሸሸው፣ አሸነፈው አዋረደው። (መስቀል) ክርስቶስን ያከብረዋል ከፍ ከፍም ያደርገዋል፣ ድል ማድረጉንም ለዓለም በግልጽ ያሳያል። ክርስቶስ መከራ ሞትን በእርሱ ላይ በመቀበሉ ምክንያት መስቀልን ማቃለልና ማዋረድ የተገባ ቢሆንስ ሞቱም የሚከበርና የሚጠቅም ባልሆነ ነበር። ሐዋርያው እንዳስተማረን እንዴት ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ ተጠመቅን (ሮሜ 6፥3)? ሞቱን በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር የተባበርን እንዴት ትንሣኤውን እንካፈላለን (ሮሜ 6፥5)? በሌላ መልኩ አንድ ሰው የጌታ ስም በላዩ ላይ ሳይጻፍ የመስቀሉን ምልክት ቢያከብር በትክክል ይህ ሰው የተሳሳተ ነገር እያደረገ እንደሆነ ይከሰሳል/ይወቀሳል። “ይህም በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ” (ፊል. 2፥10) ተብሎ ተጽፏልና መስቀል ይህንን ክቡር ስም ተሸክሟል። በክርስቶስ መስቀል ፊት ጉልበትን አለማንበርከክ እንዴት ያለ ሞኝነት ነው !
ልባችንን ወደ ሰማይ ሰቅለንና ከፍ አድርገን ከመዝሙረኛው ዳዊትና ከነቢያቱ ጋር “ወደ ማደሪያዎቹ እንገባለን እግሮቹ በሚቆሙበት ስፍራ እንሰግዳለን/እናመልካለን” [4] (መዝ 131(132)፥7)። ስለ እኛ ሁሉን የሚያቅፉ እጆቹ ወደ ተዘረጉበት ሕይወት ሰጪ የሆነውን ሥጋውም ወዳለበት (ወደ ማደሪያዎቹ እናመልከው ዘንድ እንሂድ)። መስቀሉን በእምነት ስናከብረውና ሰላም ስንለው ከእርሱ የሚመነጨውን የተትረፈረፈውን ቅድስና እንቀበል እንያዝም። ምሥጢርና ስውር ሆኖ ክቡር በሆነው በጌታችንና በአምላካችን በመድኃኒታችን ዳግም ምጽአት ሐሤት እናደርግና ፍጻሜ ወደ ሌለው ደስታ እንሻገር ዘንድ፣ በቀኙ መሆንን አግኝተን ተስፋ የተሰጠውን የደስታ ቃላትና ባርኮት በሥጋ ለእኛ ሲል ስለ ተሰቀለው የእግዚአብሔር ልጅ ክብር እንሰማ ዘንድ።
መጀመሪያ ከሌለው አባቱ ጋርና ቅዱስ፣ መልካምና ሕይወት ሰጪ ከሆነው መንፈስ ቅዱስ ጋር ለእርሱ ሁሉም ክብር ይገባዋል። አሁንና ለዘላለም ለትውልደ ትውልድ አሜን!
ተፈጸመ
[1]ለፍጥረታዊ ሰው የእግዚአብሔር መንፈስ ነገር ሞኝነት ነውና አይቀበለውም፤ በመንፈስም የሚመረመር ስለ ሆነ ሊያውቀው አይችልም። መንፈሳዊ ሰው ግን ሁሉን ይመረምራል ራሱ ግን በማንም አይመረመርም። (1ኛ ቆሮ 2፥14-15)
[2] ሐዋ 10፥39
[3] ቆላ 2፥14
[4]እዚህ ጋር የእንግሊዘኛውን የዕብራይስጡ ትርጉም “መስገድ” የሚለውን ሳይሆን “ማምለክ” ብሎ ነው የተጠቀመው። ስግደት የተለያየ መልክና ትርጉም ሊሰጠው የሚችል ቃልና ተግባር ሲሆን አምልክ ግን ለፈጣሪ ብቻ የሚሰጥና የመገዛታችን ማመላከቻ፣ የተፈጠርንበትም ዓላማ ነው ነው።