የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ክፋትን ጠግቦ

በአጋጣሚ የምናገኛቸው መልካም ሰዎች አሉ። በጥቂት ደቂቃ የዘመናት ስንቅ የሚሆን ምክር ይሰጡናል። በአጋጣሚ ያገኘሁት ይህ ሰው ሙያው ሕክምና ሲሆን ሰውን በመርዳት የሚደሰት ነው። መልካም ሰው ከተገኘ ያስደስታል፣ ክፉ ሰው ፈላስፋ ያደርጋል።  መልካም ጓደኛ ልብን ያሳርፋል ፣ ክፉ ጓደኛ የዕድሜ ልክ ትምህርት ይሰጣል። በዚህ ዓለም ላይ እግዚአብሔር አምላካችን ከሆነ ምንም አንጎዳም፤ ሁሉን ለጥቅም ያደርግልናል። ደጎች ደግነትን ያስተምሩናል፣  ዓመፀኞች ግን ዓለምን የምናይባቸው መስተዋት ናቸው። ጠንካራ ሰው ለመሆን ከደጎች ይልቅ የሚገፉን ሰዎች ያግዙናል። ይህ ሰው ከሙያዊ እውቀት አልፎ ሕይወት አብስሎታል። በገዛ ልጆቹ፣ ቤተሰቡ  ብዙ ጉዳት አስተናግዷል። የኮሌጅ እውቀት ብቻ ሳይሆን የሕይወት እውቀትም ገብይቷል።

የሕይወት እውቀት ያላቸው ከትልቁ እግዚአብሔር የተማሩ ናቸው ። ሕይወት ትልቁ   ትምህርት ቤት ነው። ሕይወት የሚያስተምረን በፈተና እያበጠረን፣ በእጦትና በሕመም ውስጥ እያሳለፈን ነው። እንዲህ ሕይወት ካስተማረው ጋር ማውራት እርካታ አለው። ሕመምህን ከታመመ ጋር አውራው ይባላል። የታመመ ሰውም ተራ ንግግር አይናገርም፣ ንግግሩ ደርዝ አለው። ይህ ሰው የጎዱት ሰዎች ቢመለሱ ብሎ መልካም ሲያደርግ እየባሰባቸው መጥቷል።  እነርሱ ሲሄዱ ሌላ ክፉ ተክተው ይሄዳሉ። የቀደሙት ክፉዎች ክፋታቸው ስለ ተለመደ አዲሶቹ የራሳቸውን ጨምረውበት  የበለጠ ክፉ ይሆናሉ። ይህ ሰው ከብዙ ታሪኮቹ በኋላ ቀጥሎ ያለውን ጥያቄ ጠየቀኝ፦ “ሰው ምግብ በልቶ እንጂ ክፋት ጠግቦ እንዴት ያገሣል?”

አራዊት በግሣት ይታወቃሉ። አንበሳ ሲያገሣ  ብዙዎች ይደነግጣሉ። ግሣት የጥጋብ፣ የማን አለብኝነት፣ የቍጣ፣ የመግደል ጥማት ፣ ከእኔ በላይ ማንም የለም የሚል ስሜት ያለው ነው ::  ግሣት ፉከራ ፣ ከራስ በላይ ነፋስ እንጂ እግዚአብሔር የለም ብሎ ማሰብ ነው:: ብዙ አምባገነን ነገሥታት በዘመናት ሁሉ በኃያል ድምፅ ተናግረዋል። ሁሉም ዳግም ላይናገሩ ፀጥ  ብለዋል። የእግዚአብሔር ፍርድ የዘገየ የመሰላቸው ፣ ኃጢአታቸው ጽድቅ ሆኖ የታያቸው፣ ተዉ የሚል መካሪ የሌላቸው፣ በእነርሱ ደረጃ ወርዶ የሚሰዳደብ ያጡ ፣ ጉርምስናን እስከ አሁን የኖሩ ሰዎች ግሣት ይታይባቸዋል።

ሰው እንደ መሆናችን ብንበድልም ፣ የሰውነት ክብሩ ወድቆ አለመቅረት ነው። በሁሉም የዕድሜ ዐውድ ትክክል መስሎ የሚሰማን ጊዜ አአ። ማደግ ግን ያለፈውን እውቀት ይሽረዋል። የምንኖረው ለመታረም ነው። ማንም ልከኛ ሰው ባለበት ቦታ ቆሞ አይቀርም። ለውጥ እያለ ነውጥን አይፈልግም። ራሱን ሳይለውጥም ዓለምን እለውጣለሁ ብሎ አይነሣም። በክፋት መመካት ከዲያብሎስ በላይ ዲያብሎስ መሆን ነው።

ሰው እንዴት በሌላው ልቅሶ ደስታውን ይመሠርታል? ሌላውን አራቁቶ እንዴት ያሸበርቃል? ከዘመን ዘመን ልክ ነኝ ብሎ እንዴት ይኖራል? ከጠላት ጋር እየመከረ ከወዳጁ ጋር እንዴት ይኖራል? ያልደረሰበትን ሰው አንኳኩቶ እንዴት ይጣላል? በራሱ ወገን ላይ ሞትን እንዴት ይደግሳል? ሥራ እያለ ሴራን እንዴት ይይዛል? እገሌን አነሣሁት ሳይሆን ጣልኩት ብሎ እንዴት ይኮራል? የእኔን ተንኮል ማንም አይፈታትም ብሎ በነውሩ እንዴት ይኮራል? ዕድሜን ለንስሐ ሳይሆን ላላለቀው ክፋታቸው የሚያውሉ፣ የፀፀት ልብ የራቃቸው ሰዎች ብዙዎች ናቸው።

ብቻ ዛሬም ክፋትን ጠግበው የሚያገሡ ሰዎችን ስናይ የሚመለስ ልብ እንዲሰጣቸው እንጸልያለን !

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ኅዳር 27 ቀን 2017 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ