የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ወለተ ኢያኢሮስ

  

/ማር. 5፡21-43/

እግረ መንገድ የምናከናውናቸው ብዙ ተግባራት ያልተጠበቁና እንደ ተአምር የሚቆጠሩ ፣ “በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ” ተብለው ስያሜ የሚያገኙ ናቸው ። እግዚአብሔር ግን እግረ መንገድ በሚመስል የታቀደ ተግባር ይሠራል ፣ በአንድ ሰዓትም የብዙ ሰዎችን ጉዳይ ይፈጽማል ፣ የዘመናትን እንቆቅልሽ ይፈታል ። አንዱ ታሞ ሌላው ሞቶበት ቢሆንም ሳያወዳድር ለሁሉ ያዝናል ። እናቱ ለሞተችበትም እናቱ ገበያ ለሄደበትም ለሁሉም የአባትነቱን ድምፅ ያሰማል ። ሕመምን እፈውሳለሁ ፣ ሞት ይሳነኛል ሳይል በጌትነቱ ሁሉን ይገዛል ። ጸጋ ልዩ ልዩ ቢሆንም ባለ ጸጋውና አዳዩ ግን አንድ መንፈስ ቅዱስ ነው ። ጉዳይ ብዙ ቢሆንም ማኅተሙን የሚፈታው ግን አንድ ክርስቶስ ነው ። ጸሎት ወደ እግዚአብሔር ልበ ሰፊነት ፣ ወደ አምላክ ይቅር ባይነት ፣ ወደ ጌታ ችሮታ የምንገባበት በር ነው ። ከልቡ የሚጸልይም ጠባብነት ፣ ምቀኝነትና ስስት ይርቁለታል ። ኢያኢሮስ ለሌላው ስትደርስ ለእኔ ዘገየህ ፣ በእኔ ጸሎት እነ እገሌ ተጠቅመው እኔ ባዶዬን ቀረሁ ፣ እኔ ሙት ተሸክሜ አንተ ግን ለበሽተኛ ትቆማለህ አላለም ። እኔ ናዳ ወርዶብኝ አንተ ግን ጠጠር ለመታው ታዝናለህ የሚል ልብ አልነበረውም  ። 

ኢያኢሮስ በአሮጌይቱ ድንኳን አዲሱን ወንጌል የሚያገለግል ነበር ። አሮጌይቱ ድንኳን ሰማይን የማታይ ፣ ከምድረ እስራኤል ውጭ አስፍታ የማትሄድ ፣ ወደ እኔ ኑ እንጂ ልምጣ የማትል ፣ ሙከራ እንጂ መፍትሔ የሌለባት ነበረች ። አዲሲቱ ወንጌል ግን ምድርን ትታ ሰማይ ሰማይ የምታይ ፣ ግዛቷን በዳርቻ በምድር ጥግ ያደረገች ፣ ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ የሚል  አደራ የተቀበለች ፣ በአንዱ በግ ፍጥረት መጥገቡን ያበሰረች ናት ። ትንቢት ሳይሆን ፍጻሜ ፣ ሙከራ ሳይሆን መፍትሔ ያለባት የእግዚአብሔር ድንኳን ናት ። ኢያኢሮስ ወደ ክርስቶስ በራሱ ተነሣሽነት ለመምጣት ቀኑ ባይረዳውም በልጅ ሞት ግን መጥቷል ። ሰው በተለያየ ደወል ወደ ክርስቶስ ይመጣል ። ለልጅ ሕመም መጥተው ራሳቸው በነፍስ መሞታቸውን ያወቁ አያሌ ናቸው ። ሰው ሊያሳክሙ ሄደው የራሳቸውን የከፋ በሽታ የሚያገኙ ብዙ ናቸው ። ታክሜአለሁ ታከሙ የሚል ወንጌላዊ ነው ። እግዚአብሔር በመምጣታችን ደስ ይለዋል እንጂ “እንዴት ነው የመጡት ?” ብሎ አመጣጣችንን አያጠናም ። “እኔ ባጣ ቆየኝ ነኝ ወይ ?” አይልም ። “አልሳካ ሲላችሁ ነው የመጣችሁት” አይልም ። “ደስታችሁን ከዓለም ጋር ነስንሳችሁ የኀዘን አመዳችሁን እኔ ጋ ለመበተን መጣችሁ” አይልም ። እግዚአብሔር አልመጣም ስንል ይገሥጸናል ፣ ስንመጣ መንገድ አጋምሶ ይቀበለናል እንጂ አይታዘበንም ። 

እግዚአብሔር የወደቀውን ዛፍ አንሥቶ ባለ ፍሬ ያደርገዋል እንጂ በወደቀ ዛፍ ላይ ምሳር/መጥረቢያ አያበዛም ። 

ሲነጋ የነጋላቸው የታደሉ ናቸው ። ንጋትን ንጋት ፣ ደስታንም ደስታ አድርግልን ማለት ትልቅ ጸሎት ነው ። ኢያኢሮስ ነግቶ የጨለመበት በልጁ ሞት ነው ፤ የልጅ ደስታን ሳይጨርስ የልጅ ኀዘን የወደቀበት መከረኛ ነው ። ከሁሉ የሚከፋው በንጋት ውስጥ ያለው ጨለማ ፣ በደስታ ውስጥ ያለው ኀዘን ነው ። ሲነጋ የጨለመባቸው ፣ ሌሊትና ቀን አንድ የሆነባቸው ብዙ መከረኞች አሉ ። ጌታችን ሌሊቱን ሙሉ ሲገሰግስ አድሮ ማለዳ ደረሰ ። የዘመናትንና የዕለትን ልመና ለመፈጸም አለሁ አለ ። የዘመናት ችግረኞች የጌርጌሴኖኑ እብድና ደም ይፈስሳት የነበረችው ሴት ናቸው ፣ የዕለት ችግረኛ ወለተ ኢያኢሮስ ናት ። ቀን ሲደርስ አምባ ይፈርስ እንዲሉ ቀን ሲደርስም የዘመናት ጥያቄ መልስ ያገኛል ። 

ያ እብድ ዓመታት ያለፉት ፣ ይህች ሴትም አሥራ ሁለት ዓመት ደም ይፈስሳት የነበረች ናት ። የኢያኢሮስ ቤት የገባው የሞት አደጋ ግን ከባድ ነበረ ። ሕመምን ማስታመም ይቻላል ፣ ሞትን ማስታመም ግን አይቻልም ። የጠፋ ፋኖስን መለኮስ ይቻላል ፣ የጠለቀች ፀሐይን መመለስ ግን አይቻልም ። እግዚአብሔር የዘመናት ሕመምን ፣ የዕለት ሞትን ሊያስወግድ ገሰገሰ ። ሕመም የዘመናት ሲሆን ሞት ግን አንድ ቀን ነው ። ይህ ጌታ የጠራው ጸሎታቸው ብቻ ሳይሆን የሚጮኸው ጭንቀታቸውም ነው ። እግዚአብሔር ለለመኑት ቸር ነው ፤ ላልለመኑትም እስኪለምኑት ድረስ መንገድ የሚጠርግ ነው ። ፈውሱ ልዩ ልዩ ነው ። አንዳንዱን በሽታ በተግሣጽ ፣ አንዳንዱን በልብሱ ዘርፍ ፣ ሌላውንም በሥልጣን ቃል የሚናኘው ነው ። እብደት መገሠጽ አለበት ። ራስን ብቻ ማዳመጥ ፣ ሌላውን ዕረፍት መንሣት ያለበት ፣ ምቾትን ማምለክ ሌላው መርገጥ ፣ እኔ ልኑር ብዙዎች ቤዛ ይሆኑልኝ ማለት ፣ ራስን ገለልተኛና ጉዳተኛ ሌላውን ጠላት አድርጎ መመልከት … ይህ እብደት ነው መገሠጽ አለበት ። ድምፅ የሌለው የደም ዥረትም ድምፅ በሌለው የልብሱ ዘርፍ መቆም አለበት ። ሞትም ስለሌላው በሚማልዱ ይወገዳል ። እግዚአብሔር ምልጃን ይወዳል ። 

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከበሽታ ብቻ ሳይሆን ከሞትም ያድናል ። 

የጌርጌሴኖኑ እብድ መጸለይ አይችልም ። ለመጸለይም አእምሮ ያስፈልጋል ። ደም ይፈስሳት የነበረችው ሴትም ድምፅ አላሰማችም ። መቃተትንም ጸሎት ብሎ የሚሰማ የኤልያስ አምላክ ሕያው ነው ። ወለተ ኢያኢሮስ/ የኢያኢሮስ ልጅም ለመጸለይ የማትችል ሙት ናት ። አባትዋ ግን ስለ እርስዋ ለመነላት ። መጸለይ የማይችለውንና ችግር እንዳለበት እንኳ የማያውቀውን እብድ ጌታ ተለመነው ። ስንት ምንጮች ሲደርቁ ደምዋ ያልቆመውን ሴት በልብሱ ዘርፍ ፈወሳት ። የሞተችውም በሚጸልይላት አባት ተነሣች ። ሰውዬው ባይናገርም መልኩ ይናገራል ። እግዚአብሔር አይቶም ይለመናል ። የሚገድለው ችግር ሳይገድላት ተንቀሳቃሽ ሬሳ ያደረጋትን ያቺን ሴት የደም ምንጭዋን አነጠፈላት ። “ደህና ሁኑ” ያለችውን ሟች “እንዴት አረፈዳችሁ ?” እንድትል አበቃት ። እርሱ ሲመጣ መለመን ፣ ፊቱን ሲያበራ ደጅ መጥናት መፍትሔ አለው ። 

እብዱ በጣም ይጮኻል ፣ ደም ይፈስሳት የነበረችው ሴት ወደ ውስጥ ትጮኻለች ። ወለተ ኢያኢሮስም ከብበው የሚጮኹላት ብዙ አልቃሾች ነበሩአት ። ለራሱ የሚጮኸውን ፣ ወደ ውስጥ የሚጮኸውንም ፣ ሌሎች የሚጮኹላቸውንም ሁሉንም በዓይነ ምሕረት አየ ። ያ ጌታ ዛሬም ይመልከተን ።

ይቀጥላል

ዲያቆን አሸናፊ መኮንን

ኅዳር 27 ቀን 2013 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ