የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ወለተ ኢያኢሮስ /3

 

ገሊላ የሁሉ ሰብሳቢ ነች ። ከገሊላ ደግሞ የጥብርያዶስ ባሕር ዳርቻ ነዋሪዎች ገራሞች ፣ ልፋተኞች ፣ ሁሉን ተቀባዮች ፣ ብዙ ደክመው ጥቂት ተጠቃሚዎች ናቸው ። ይበቃል ሲሉት ይበቃልና በኑሮአቸው የረኩ ነበሩ ። የዋህነታቸውን ፣ ታታሪነታቸውን ፣ በትንሹ መርካታቸውን አይቶ ጌታ የሚበዙትን ደቀ መዛሙርት ከጥብርያዶስ አካባቢ መረጠ ። በረሃ የሚሰጠው የራሱ ጸጋና ጠባይ አለ ። የባሕር ዳርቻ ኑሮም የራሱ ጸጋና የሚያላብሰው ጠባይ አለ ። በረኸኞች ንግድ ሲያስተላልፉ ፣ የባሕር ዳርቻ ነዋሪዎች ደግሞ ሰው ሲያስተናግዱ ይኖራሉ ። ሰው ሁለት ነገርን ይመስላል ። የመጀመሪያ ኑሮውን ይመስላል ። ኑሮው ቆንጆ ከሆነ መልኩም ቆንጆ ይሆናል ። ሁለተኛ ሰው መኖሪያውን ይመስላል ። መኖሪያው በረሃ ከሆነ የዕለት ነዋሪ ይሆናል ፣ መኖሪያው የባሕር ዳርቻ ከሆነ በተስፋ ያድራል ። ኢያኢሮስም እንደ ከተማው ነዋሪ ልቡ ቶሎ የሚነካ ፣ እግዚአብሔር ተብሎ ሲጠራ ሊናገር የፈለገውን ክፉ የሚመልስ ፣ የተቸገረ ሲያይ ልቡ የሚላወስ ሰው ነበር ። 

አገልጋይና ምእመናን ቅርበታቸው ከትዳር ይዘልቃልና ምእመን ከትዳሩ የደበቀውን ምሥጢር ለእነርሱ ይነግራቸዋል ። ሰው ራሱ ሊያመልጠው ሲልም ያዘኝ ብሎ የሚማጸነው እግዚአብሔርንና የእግዚአብሔርን አገልጋይ ነው ። እኔ ብደክም ፣ እንቅልፍ ቢጥለኝ እንኳ ስለ እኔ በጸሎት መትጋትን እንዳታቋርጥ ብሎ የሚያዝዘው አገልጋዩን በመሆኑ አገልጋዩ ለምእመኑ የነፍስ አምባ ነው ። ብሶት ፣ ፍርሃት ፣ ጭንቀት ፣ የወዳጅ መክዳት ፣ የልጅ ጠላት ፣ የሥራ መሰናክል ፣ የመንግሥት አባራሪ ፣ የዘመን መጋኛ ፣ የወዳጅ ሸረኛ ፣ የጤና መቃወስ ፣ የእምነት መናወጥ ፣ የተስፋ መሟጠጥ ፣ ስንዴ ብሎ የከመሩት አመድ ሲሆን ፣ ያለቀው ነገር ገና ወደ ጅምርነት ሲለወጥ ፣ ማፈር ሲበዛ ፣ ለዓመት ያሉት በዕለት ሲያልቅ ፣ ሰውን ማመን ጉዳት ላይ ሲጥል ፣ ልሸከምህ ያሉት ጀርባን ሲነክስ ፣ አበባ የሰጡት አፈር ሲበትን ፣ መልካም ልደት ያሉት የሞት ድንጋይ ሲወረውር… ይህን ሁሉ የሚነግሩት ለእግዚአብሔር አገልጋይ ነው ። አገልጋዩ ግን ቶሎ ይረሳል ፣ ሰው ቢጤውን ሲያገኝ የእግዚአብሔርን ሰው ማቃለል ይጀምራል ። ክፉውን ቀን ሲሻገር ያሻገረውን ድልድይ ካልሰበርኩ ይላል ። ስንዴ ዘርቶ እንክርዳድ ለማጨድ ዝግጁ ያልሆነ ወደ አገልግሎት ባይገባ ይመከራል ። አገልጋይ በደጅ ከማያምን ልብ ጋር ፣ በቤት ከሚያቃስት ትዳር ጋር የሚታገል ነው ። 

ኢያኢሮስ የምኵራብ አለቃ እንደ መሆኑ ብዙ ሸክሞች አሉበት ። ለዚህ ነው ጌታን ሲያገኝ ማረፍ ፈልጎ በእግሩ ሥር የወደቀው ። ሸክሙን መጣል ሽቶ በጌታ እግር ሥር የተዘረረው ጭስ በማይታይበት ቃጠሎ ያለ በመሆኑ ነው ። ኢያኢሮስም ሆነ የዛሬ አገልጋዮች እግዚአብሔር ያጽናችሁ ! የወደቁ ሰረገሎችን የሚያነሡ የማንሻ መሳሪያዎች እነርሱ የወደቁ ቀን የሚያነሣቸው የለም ። ብዙዎችን ያቀኑ አገልጋዮችም የወደቁ ቀን የሚያነሣ አጥተው ቀርተዋል ። የስንቱን ንስሐ የደበቁት አገልጋዮች የእነርሱ ብናኝ ኃጢአት ዜና ተሠርቶበታል ። ኢያኢሮስ እግሩም ልቡም ያነክስ ነበር ። ልቡ የሚያነክሰው በሚያገለግለው ሕዝብ ፣ እግሩ የሚያነክሰው ከምኵራብ ወደ ቤት ሽቅብ ቁልቁል ሲል ነው ።

 

አገልግሎት የሚያጎብጥ ቀንበር ያለበት ፣ ልተውህ ቢሉት የማያስኬድ ገመድ የተተበተበበት ነው ። ከሰው እልከኛ ልብ ጋር መታገል ፣ ፈጣሪው ያልቻለውን ሰው ለማለዘብ የሚደረግ ተግባር ነውና ግብ ግቡ ከባድ ነው ። “እናንተ ከደከማችሁማ…” ስለሚባሉ አገልጋዮች ሲደክሙም እንደ በረታ ሰው ተውኔት ይሠራሉ ። “እናንተ ካለቀሳችሁማ…” ስለሚባሉ ስሜታቸውን አፍነው እንባቸውን ወደ ውስጥ ያፈስሳሉ ። ኢያኢሮስ አገልግሎት ብቻ ሳይሆን ኑሮም ነበረው ። ከኑሮም በሽተኛ ልጅ ተሸክሞ የሚኖር ነው ። አገልግሎት ፣ ትዳር ፣ ኑሮ ፣ ልጅ ፣ የግል ስሜትና የልብ ትግል የነበረው ሰው ነው ። አገልጋይነት ሰውነትን አይሽርም ። መስቀል ተሸክሞ ለመኖር ያልወሰነ ሰው አገልጋይ እንዲሆን አይመከርም ። ኢያኢሮስ በዚያ ማኅበረሰብ አስተሳሰብ የልጁ ሕመም የሐሜት ርእስ የሆነበት ጅራፍ ነው ። “የተደበቀ ኃጢአት ቢኖርበት ነው በልጅ የተቀጣው ፣ እምነት ስለሌለው ነው ልጁን መፈወስ ያልቻለው” የሚሉ የአላዋቂዎች ድምፅ ሊያደክመውና በቁሙ ሊጥለው ይታገለዋል ። የሰውን አስተሳሰብ ማከም ከባድ ነው ። የአገልጋዮች አገልጋይ ግን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ኢያኢሮስ አቅጣጫ ሲመጣ ኢያኢሮስ በቁሙ ወደቀ ። የሚያነሣው ጋ ወደቀ ፣ የሚያጽናናው ጋ አለቀሰ ፣ ሸፋኙ ጋ ተገለጠ ። “ስለ ወዳጅ እሬት ይላሳል ፣ ስለ አንተ ስል ማገልገል ይቻላል” ያለ ይመስላል ። 

የልጅ ሕመሙ ሳይሆን ከባድ እንቅልፉም ያስጨንቃል ። ልጃቸው መኝታው ላይ ሲያረፍድ ትንፋሹን የሚያዳምጡ ፣ ሲወጣ በእግሩ ሳይሆን በሸክም የሚመለስ የሚመስላቸው ፣ ደህናውን ልጅ ማሳመም ፣ ሕያውን ገድሎ ማልቀስ የሚቀናቸው ኢያኢሮስን ይረዱታል ። ደጁ ቢያደክምም ወደ ቤት ጉዞ ሲያደርጉ የማረፍ ስሜት ይሰማል ። የአልጋ ቍራኛ በቤት ውስጥ እንዳለች ማሰብ ግን ሰው የገዛ ቤቱን እንዲፈራ ያደርገዋል ። ኢያኢሮስ አገልጋይነት ፣ ወንድነት ፣ አባትነት ፣ የኑሮ ልምድ ጠንከር አላደረጉትም ። እንደ ቀጤማ መቆም ያቃተው ፣ ፍሬ እንዳዘለ የጤፍ አገዳ በቁም ልደፋ ልደፋ የሚል ሁነት ውስጥ የገባ ነው ። ከታማሚው ያስታማሚው በሽታ ይበረታል ። ሰው ግን አያውቅምና የታመመውን እግዚአብሔር ይማርህ ሲል አስታማሚውን ግን እግዚአብሔር ይማርህ አይለውም ። አስታማሚ ግን ሲጸልይ “እኔን ማረኝ” ይላል ። የልቡን ዝለት ያውቀዋልና ። ኢያኢሮስ ቀልቡ ከከዳው ፣ የሰማውን ሳይሆን የሚያስበውን መናገር ከጀመረ ቆይቷል ። የልጅ ሳቅ ወደ ማቃሰት ሲለወጥ ማየት ከባድ ሆኖበታል ። ቀኑን ውሎ የመሸበት ማመስገን አለበት ። ያች ልጅ ግን ማለዳው ሠርክ የሆነባት ፣ በጅምር ልለቅ ልለቅ የምትል ነበረች ። የአማካሪዎች አማካሪ ካልሆነ ኢያኢሮስን የሚያህል የምኵራብ አለቃ ማን ይችለዋል ? መከራ ወደ ሰው ይገሰግሳል ፣ ክርስቶስም ለማዳን ይበረታል ። የተቆረጠውን ሰዓት ፣ እያለቀ ያለውን አቅም ያውቀዋልና ጌታ በሰዓቱ ይደርሳል ። ዓለም ማለዳውን ምሽት ስታደርግብን ክርስቶስ ግን ሠርኩን ንጋት ሊያደርገው ይፈጥናል ።

አቤቱ ሆይ አገልጋዮችህን ሞገስ አልብስ ። የመረጥካቸውን በጎነትና ዕድገታቸውን አሳየን ።

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ታኅሣሥ 3 ቀን 2013 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ