የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ወለተ ኢያኢሮስ /4

 

ችግር በራሱ ክፉ ቢሆንም የሚያመጣቸው መልካም ነገሮችም አሉ ። ዓይኑ የበራለት የሚባለው መንፈሳዊ ሰው ከችግር ውስጥ ያለውን መልካም ነገር ያይና ከጉዳቱ ጥቅሙ አመዝኖበት ለምስጋና ይቆማል ። ከመልካም መልካም ማውጣት ያቃታቸው ፣ እንደ ምን አደሩ ነገር የሆነባቸው እንዳሉ ሁሉ ከክፉ ነገርም መልካም ነገርን የሚፈልጉና የሚያገኙ አያሌ ናቸው ። ጠላት የሚጠርበው የመስቀል እንጨት ወደ ዙፋን ይለወጣል ብለው የመርዶክዮስን አምላክ የሚጠባበቁ ፣ የአንበሳው ጉድጓድ የተሴረበትን አውጥቶ ያሴሩትን እንደሚያስቀር በዳንኤል አምላክ የሚያምኑ ፣ ገዳዩን ሄሮድስን ወስዶ ተገዳዩን ጴጥሮስን በነጻ የሚለቅ የወንጌል አምላክ አለ ብለው ለሚጠባበቁ ክፉ ነገር ሙሉ ኀዘን አይሆንባቸውም ። ዓይን ያየውን አይቶ ይፈርዳል ፣ እምነት እግዚአብሔርን አይቶ ጨለማው ይበራል ይላል ። የሚታየው ለማየት ዓይን በቂ ነው ፣ የማይታየውን ለማየት ግን እምነት አስፈላጊ ነው ። አንዳንድ ሰዎች ጠላት ሲነሣባቸው አንድ ዕድገት ሊመጣ ነው ይላሉ ። ሌሎችም ስደት ሲመጣባቸው ለብዙዎች መጠጊያ ልሆን ነው ብለው በዮሴፍ አምላክ ይደገፋሉ ። ጥቂቶችም መገፋት ሲመጣ ከፍታ ፣ ስድብ ሲበዛ ጸጋ እንደሚበዛ ያምናሉ ። እግዚአብሔር የሚሠራው የሰው ስሌት ከሚደርስበት ባሻገር ነው ። የእግዚአብሔር ሥራ ለቀመር አይመችም ። እንደ ጠባዩ እናምነው ዘንድ “እግዚአብሔር ሆይ እርዳን” ማለት ትልቅ ጸሎት ነው ። 

የባቢሎን ምርኮ መቅደስ አሳጥቶ ምኵራብን የሰጠ ፣ አንድ መቅደስን አፍርሶ ብዙ ሺህ ምኵራቦችን ያሠራ ፣ በኢየሩሳሌም ብቻ የተወሰነውን አምልኮ በየአጥቢያው ያንሠራፋ ነው ። የባቢሎን ምርኮ ካመጣቸው ልማዶች አንዱ ከአሥር በላይ ቤተሰብ ባለበት ስፍራ የአጥቢያ የአምልኮ ማዕከል እንዲኖር አድርጓል ። በኢየሩሳሌሙ መቅደስ የእንስሳ መሥዋዕት ሲቀርብ በምኵራብ ግን ለአዲስ ኪዳን ተስማሚ የሆነ መንፈሳዊ መሥዋዕት ይቀርብ ነበር ። የኢየሩሳሌሙ መቅደስ መገኘትን ሲጠይቅ ፣ ምኵራብ ግን የልብ መነሣሣትን የሚጠይቅ ፣ ላመኑ ሁሉ ቅርብ ነው ። በምኵራብ ጸሎት ፣ ቃለ እግዚአብሔር በንባብና በትርጓሜ ፣ መዝሙር ይደረጋል ። በምኵራብ በማለዳና በሠርክ መንፈሳዊ መሥዋዕት ያርጋል ። ኢያኢሮስ የምኵራብ አለቃ ነበረ ። እንደ አለቅነቱ የመጡትንና የቀሩትን ምእመናን እረኛ ሁኖ ይቆጣጠራል ። ጸሎቱ በትጋት እንዲቀርብ ፣ ምስጋናው በተመሥጦ እንዲቃኝ  ፣ ቃለ እግዚአብሔር በጥንቃቄ እንዲተረጎም አገልጋዮቹን ይቆጣጠራል ። የመንፈሳዊ ቦታ አለቆች ሙዳየ ምጽዋትን መቆጣጠር ብቻ ሳይሆን አምልኮው በቅዱስ ፍርሃት እየተከናወነ መሆኑን መቆጣጠር አለባቸው ። የሀብታሞችን የእግር ኮቴ ሳይሆን እግዚአብሔርን የሚያቀርብ ምሕላ እየቀረበ መሆኑን ማረጋገጥ አለባቸው ። በምኵራብ በእንግድነት የተገኘ ካለ የሚጋበዘው ብሉያትን አንብቦ እንዲተረጉም ነው ። በምኵራብ እንግዳ ከመጣ ተረኛው መምህር ለእርሱ ቦታ ይለቃል ። ይህም ትልቅ ትሕትናን የሚያመለክት ነው ። የቃሉ ግብ ትሕትና ከሆነ እኔ ካልተረጎምሁ ብሎ ነገ በሚያገኙት መድረክ እንግዳን መግፋት አይገባም ። እንግዳው በዚያ ቀን በቃል ሲተረጕም ፣ ተረኛው አገልጋይ ደግሞ በሕይወቱ ይተረጕማል ። 

ብቻ በምኵራብ ነፍስን አድራሻ ያደረገ አገልግሎት ይሰጣል ። ያደረው ስሜት እንዳይውልባቸው የማለዳው አምልኮ ቀኑን ያበራል ። የዋለው ድካም እንዳያድርባቸው የሠርኩ አገልግሎት ድካምን ያርቃል ። ማንጋትና ማስመሸት ሥልጣኑ የእግዚአብሔር ነውና ምስጋና ማቅረብ ተገቢ ነው ። ማንጋትንና ማስመሸትን ላልረሳ እግዚአብሔር ምስጋና መርሳት በእውነት እብደት ነው ። ኢያኢሮስ በቤቱ የሚታገለው ችግር ቢኖርም የሰዎችን ነፍስ በመንፈሳዊ አገልግሎት ለማሳረፍ ሲነሣ ራሱንም በርትቶ ያገኘው ነበር ። ግዱን ወደ አገልግሎት ቢሰየምም አገልግሎቱን ሲፈጽም ግን ራሱን በመጽናናት ያገኘው ነበር ። 

የምኵራቡን አገልግሎት እንደ ፈጸመ ወደ ቤቱ የሚወስደውን ጎዳና ሲይዝ ከርቀት አንድ ነገር ተመለከተ ። ብዙ ሰዎችን ያስከተለ ፣ በመካከላቸው ግን እንደ ደማቅ ዕንቈ የሚያበራ መምህርና ጌታ ፣ እረኛና አዳኝ የሆነው ክርስቶስ ሲመጣ ተመለከተ ። ዝናውን በርቀት ቢሰማም ከእርሱ ጉባዔ ለመቀላቀል ግን ምድራዊ ክብሩን የሚያጣ እየመሰለው ብዙ ጊዜ ዘግይቷል ። ከምኩራብ አለቆች እንዳይጣላ ብሎ በልቡ የሚወደውን ጌታ በእግሩ ርቆት ነበር ። እግዚአብሔር ግን ይሉኝታን ሰብሮ የሚያወጣ ችግር ያመጣና ሰዎችን ወደ ራሱ ያቀርባል ። ኢያኢሮስ የልጅ ሕመሙ የሰውን ከበሬታ አስረሳው ። በጨዋ ደንብ የሚጸልዩ ሁሉ ችግር የወጠራቸው ቀን በክርስቶስ እግር ሥር በታላቅ ኡኡታ ይንደባለላሉ ። ኢያኢሮስ ወደ ክርስቶስ ለመገስገስ አሰበ ። ክርስቶስ እግረ መንገዱን የመጣ መሰለው እንጂ እርሱን አድራሻ አድርጎ እንደመጣ አላስተዋለም ። እርሱ ቢያፍርበትም ክርስቶስ ወደ ባሪያው ቤት ለመምጣት አላፈረም ። እንዳፈርንበት ቢያፍርብን ፣ እንደ ከዳነው ቢከዳን ፣ ቆይ እንዳልነው ቆይ ቢለን የዛሬ ሰው አንሆንም ነበር ። ኢያኢሮስ ወደ ልጁ ለመሮጥና ሕመሟን ለማስታመም ጉዞ ጀምሮ ሳለ ወደ ቤቱ የሚሄደው እግር ወደ ባሕር ዳርቻው ወደ ክርስቶስ መገስገስ ጀመረ ። እግሩ ክርስቶስ ጋ ሲያደርሰውና በክርስቶስ እግር ፊት ሲወድቅ ራሱን አገኘው ። የሰገደው በድብቅ አይደለም ፣ በአደባባይ ነውና ለክርስቶስና ለወንጌሉ እውቅና ሰጠ ። ከዚህ ውሳኔ በኋላ ከምኵራብ ሊባረር ይችላል። ክርስቶስን ሲያመልክ ግን የሚመጣውን ውጤት አላመዛዘነም ። በብዙ ሕዝብ መካከል በመስገዱ ስግደት የሚገባው አምላክ መሆኑን መሰከረ ። ከሰዓታት በፊት ብሉይን አገልግሎ አሁን የአዲስ ኪዳን ዘማች ሆነ ። በአንድ ጀምበር ሁለቱንም ኪዳናት አገለገለ ። 

ኢያኢሮስ በጌታ ፊት ወደቀ ። የሚወድቅ ራሱን የሚያዋርድ ትሑት ነው ። የሚወድቅ ሸክም የከበደው ነው ። የሚወድቅ ከዚህ በላይ መራመድ የማይችል ነው ። የሚወድቅ የሚወደቅበትን ጌታ ያገኘ ነው ። ክርስቶስ በትሕትና የተዋረዱትን በክብር ቀና ያደርጋቸዋል ። ሸክም ከብዷቸው ያዘነበሉትን ሸክሙን ተቀብሎ ነጻ ሰው ያደርጋቸዋል ። ያለቀውን ሰዓት አውቆ ፈጥኖ ይረዳቸዋል ። በእርሱ ፊት ለሰገዱት ሁሉ ዙፋን ይሰጣቸዋል ። ሰይጣን እግሩ ሥር የወደቁትን ይረግጣቸዋል ። ክርስቶስ ግን ክብር ያወርሳቸዋል ። ዋናው ነገር መስገዱ ሳይሆን የሚሰገድለትን ማግኘቱ ነው ። ለባከነ ጉልበት ለክርስቶስ ለመስገድ እንቢ ያለው ወገን እንዴት ምስኪን ነው !? ለምድር ሠራዊት ፣ ለዘመን አብዮት ፣ ለፈራሽ በስባሽ ንጉሥ የሰገደ ጉልበት ለክርስቶስ ለመስገድ ማመንታት ሲገጥመው እንዴት የሚያስለቅስ ነው !? ክርስቶስን ያወቁት የሚመስላቸው ነገር ግን የማይሰግዱለት ይበልጥ ይሰቅሉታል ።

ከሚሰቅሉህ ሳይሆን ከሚሰግዱልህ ወገን አድርገኝ ! 

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ታኅሣሥ 5 ቀን 2013 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ