የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ወለተ ኢያኢሮስ /5

 

የሰገደ ሰው ቁመቱ ሜትር ከሰማንያ አይደለም ። እጅግ ያነሰ ነው ። የሰገደ ሰው ሰማይንና አካባቢውን ለማየት ድፍረት የሌለው ተነሣሒ ነው ። የሰገደ ሰው መንገዴን ጨርሻለሁ አዲስ ጅምር ስጠኝ ባይ ነው ። የሰገደ ሰው ፊቱን ለሰጠው አምላክ ፊቱን የሚሰጥ ነው ። የሰገደ ሰው የበረከት ናፍቆት ያለበት “ካልባረከኝ አልለቅህም” የሚል ተማጻኝ ነው ። የሰገደ ሰው ይህችን ዓለም አላይም ብሎ በጌታው ለመታየት ዓይኑን የጨፈነ ነው ። የሰገደ ሰው ራሱን እንደ እንግጫ ዝቅ ዝቅ ያደረገ ፣ እኔ ትቢያና አመድ ስሆን ከጌታዬ ጋር ለመነጋገር እንዴት ደፈርሁ ? የሚል የእግዚአብሔርን ትልቅነት የተረዳ ነው ። የሰገደ ሰው ትልቅ ምስጋናና ልመና ያለው ነው ። የሰገደ ሰው የእግዚአብሔርን አምላክነት የተቀበለ ፣ አላሳልፍህም ብሎ መንገድ የዘጋ ነው ። ኢያኢሮስ በዚያ ሁሉ ክብሩ የትልቆች ትልቅ ለሆነው ክርስቶስ ዝቅ አለ ። 

ብዙ ሕዝብ ሲንጫጫ ይሰማል ፣ ኢያኢሮስ አይደለም ወይ ? የሚሉት ወሬ አጣሪዎች የሚሰነዝሩትን የነገር ፍላጻ ያዳምጣል ። የጥብርያዶስ የባሕሩ ሞገድ በጆሮው ያስተጋባል ። እርሱ ግን ክርስቶስን እሺ ለማሰኘት ያነባል ። ክርስቶስ እሺ ሲለን ሁሉም ነገር ሺህ ይሆንልናል ። 

ኢያኢሮስ፡- “ታናሽቱ ልጄ ልትሞት ቀርባለችና እንድትድን በሕይወት እንድትኖር መጥተህ እጅህን ጫንባት” ብሎ አጥብቆ ለመነው ። ታናሽቱ ልጅ የመጨረሻዋ ፣ ታናሽቱ ልጅ የዕድሜ ድሀዋ ፣ ታናሽቱ ልጅ ጨዋታ ያልጠገበችው፣ ታናሽቱ ልጅ መወለድና መሞት ምን ማለት መሆኑን ያለየችው ልትሞት ቀርባለች አለ ። ታናሽቱ ልጅና ኢያኢሮስን የሚያመሳስላቸው ነገር አለ ። ሁለቱም ጥግ ላይ ያሉ ነዋሪዎች ናቸው ። እርስዋ የልደት ፣ እርሱ የሞት ጥግ ላይ ያሉ ናቸው ። እርሷ የልደት በር ላይ እርሱ የሞት ደጃፍ ላይ ቆመዋል ። እርስዋ ለመጀመር እርሱ ለመጨረስ ትግል ላይ ናቸው ። ነገር ግን ታሪክን የሚለዋውጥ ክስተት መጣ ። ነዋሪዋ ወደ ሞት ፣ ሟቹ ኀዘን ወዳየለበት ኑሮ ለመሄድ ጉዞ ጀመሩ ። ስለማደጓ ሲያስብ ስለሞቷ ማሰብ በመጀመሩ ማሰብን ጠላው ። 

ታናሽቱ ልጅ በየዘመናቱ ለሞት ቀርባለች ። ሕፃናቱ ያለ ተንከባካቢ በጎዳና ቀርተው ፣ ልጆቹ ያለ መሪ በራሳቸው መንገድ ጠፍተው ፣ ብላቴኖቹ ያለ ሥነ ምግባር በሱስ ቀንበር ተይዘው ፣ ወጣቶቹ የሚያዝንላቸው ጠፍቶ ለጦርነት ሲታጩ ይታያሉ ። ታናናሾች ልጆች ለሞት ተቃርበዋል ። የሚበሉትን ምግብ እንጂ የሚኖሩበትን ዓለም አልገነባንምና ለሥጋና ለነፍስ ሞት ተቃርበዋል ። ኢያኢሮስ በየዘመናቱ ያስፈልጋል ። በክርስቶስ እግር ሥር ወድቆ ለትውልድ የሚያምጥ ያሻል ። 

ኢያኢሮስ ለሞት መቃረቧን ተናገረ ። እርሱ ጠዋት ወደ ምኵራብ ሲወጣ የነበረውን ክስተት ተናገረ እንጂ እውነቱ ታናሽቱ ልጅ ሞታለች ። ጉዱን አልሰማም ። ስለ በሽታ የሚያነባው ሞት እንደመጣ ፣ ስለሞት ዋዜማ የሚናገረው መቃብር ሊወርሰው መሆኑን አላስተዋለም ። ያለ መስማት መጽናናት ፣ ያለ መስማት ደስታ ብዙ ነው ። ካልሰሙት አያውክም ። የልጅ ሕመምና ሞት ግን እንዳልሰማ ለመሆን የሚጥሩበት አይደለም ። ለሕመምዋ ብቻ ሳይሆን ለዕድሜዋ ታናሽነት እንዲያዝን ጌታን ተማጸነው ። ለአንዳንድ ሰው የሚለቀሰው ለዕድሜው ብቻ ሳይሆን ለጅምርነቱ ነው ። ሞት ወግ ነው ፣ ያለ ወጉ የሞቱት ግን ያሳዝናሉ ። ደግሞም ሕፃናት የየትኛውም አገር ዜጋና የየትኛው ወገን ጎሣ አይደሉም ፤ የሁሉም የሰው ዘር አባልና ወገን ናቸው ። ሕፃናት ጎሣና ብሔር የላቸውም ። የቀለም ጦርነት የለባቸውም ። የሀብት ውድድር የሥልጣን መጠፋፋት አይታይባቸውም ። ክንፎቻቸው የተደበቁ መላእክት ናቸው ። ስለ ሕፃናት ሞት ፣ ስለ ወጣቶች በጅምር መቅረት የማያሳዝነው ሰይጣን ብቻ ነው ። 

ኢያኢሮስ ለሞት የተቃረበችውን ታናሽቱን ልጅ እንዲፈውስለት ለመነው ። የሚሰሙትና የሚያነብቡት ክፉ የሆነባቸው ፣ በታወከ ቤተሰብ የሚገሥጽ ባጣ መንደር የሚኖሩ ፣ ሁሉም ነገር ለሰውዬው ትክክል ነው በሚል ባሕል የተጠመቁ ወጣቶች ታናናሽ ልጆች ለሞት እየተቃረቡ ነው ። የሚያዩትና የሚሰሙት የሚመርጡትን ነው ። በዚህ የመረጃ ዘመን ላይ ያሉ ወጣቶች በዚህ ሥልጣኔ ውስጥ ተደብቀዋል ። ሰው የሚፈልገውን ብቻ እያየ የሚኖር ከሆነ የሕይወትን ተግዳሮት አያውቀውም ። ከሰው ጋር የሚኖር የማይፈልገውን ያያል ፣ ይሰማል ። በዚህ ምክንያት ይናደዳል ፣ ይበሳጫል ፣ መልስ ለመስጠት ከራሱ ጋር ይታገላል ። እነዚህ ነገሮች የሰውዬውን ሁለንተና ስለሚያነቃቁት ከጭንቀትና ከድባቴ እየወጣ እንዲመጣ ይረዱታል ። የመንደሩ ፍጭት ፣ የጎረቤቱ ጉንተላ በመልካም ለሚጠቀምበት የሚያነቃቃው ብዙ የሰውነት ክፍል  አለ ። በኢንተርኔት ጫካ መሽጎ ያለው ትውልዳችን ግን የሚፈልገውን ብቻ ስለሚያይ የሕይወትን ተግዳሮት የማያውቅ ፣ አቅመ ቢስ ትውልድ ነው ።

ኢያኢሮስ እንድትድንና በሕይወት እንድትኖር ለመነ ። ድኖ በሕይወት መኖር ክብር ነው ። ድኖ የሚሞት ፣ ድኖ የሚበድል ፣ ድኖ ያዳነውን በጥፊ የሚመታ ፣ ድኖ ጌታውን “ይሰቀል” የሚል ፣ ድኖ ያዳኑትን ላጥፋ የሚል ብዙ ነው ። ገመድ ያስጣሉአቸውን አገልጋዮች በሸምቀቆ የገደሉ ፣ ያጽናኑአቸውን ካህናት ቀሚስ ገልበው የሰደቡ ፣ ያጠመቁአቸውን አባቶች አላመናችሁም ያሉ ፣ እያመሰገኑ መጥተው እየተራገሙ የወጡ ፣ ድነው የሚያበላሹ ብዙዎች ናቸው ። የኢያኢሮስ ልመና አስገራሚ ነው ። ለሞቱት ብቻ ሳይሆን ለዳኑት መጸለይ በእውነት ይገባል ። ታምሞ የተነሣ እግዚአብሔርን ረሳ እንዲሉ ። ቆመው ያገለገሉአቸውን አገልጋዮች ቁጭ ብለው እናውርድ የሚሉ ፣ የበሉበት የቃለ እግዚአብሔር ገበታ ላይ ምራቃቸውን የሚተፉ አሉና በሕይወት መኖር እጅግ አስፈላጊ ነው ። በሕይወት መትረፍ የአንድ ቀን ሲሆን በሕይወት መኖር ግን የዘለቄታው ነው ። 

ኢያኢሮስ “መጥተህ እጅህን ጫንባት”  አለው ። የክርስቶስ እጆች ወደ ሞት የሚሄዱትን የሚመልሱ ፣ በሞትና በእነርሱ መካከል አንድ እርምጃ የቀራቸውን የሚታደጉ ፣ በሕይወት ለመኖር የሚረዱ ናቸው ። ብዙዎች ለሞት ኖረዋል ፣ ለሕይወት መኖር ግን አልቻሉም ። ለመጠጥ ኑረው ለቅዱስ ቍርባን አልኖሩም ። ለዝሙት ኑረው ለእውነተኛ ፍቅር መኖር አልቻሉም ። እጅ መጫን ኃላፊነት መስጠት ነው ። ከሞት ማምለጥ ኃላፊነት ነው ። በሕይወት መኖር ኃላፊነት ነው ። ኢያኢሮስ ልጁ ከሞት መንጋጋ እንድትወጣ ብቻ ሳይሆን በሕይወት እንድትኖር ለመነ ። ይህንንም በልማድ እንደ ሆነላት ሳይሆን በእግዚአብሔር እቅድ እንደተፈጸመላት ፣ ዳግመኛም መኖር ኃላፊነት መሆኑን እንድታውቅ “መጥተህ እጅህን ጫንባት” አለው ። 

ከሞት መትረፍ ፣ በሕይወት መኖር ኃላፊነት መሆንን ተረድተን ይሆን ? 

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ታህሣሥ 11 ቀን 2013 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ