የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ወለተ ኢያኢሮስ /6

 

ወንጌሉ ስለ ኢያኢሮስ ሲናገር “አጥብቆ ለመነው” ይላል ። አጥብቆ መለመን ምንድነው ? በቤተ ክርስቲያን ጸሎትም “ቍርጥ ልመናችንን ስማ” የሚል ጸሎት ይቀርባል ። አጥብቆ መለመን ማድረግ ትችላለህ ብሎ ማመን ነው ። አጥብቆ መለመን ሰዓት የለኝምና ድረስልኝ ማለት ነው ። አጥብቆ መለመን እጁን ጨብጦ እግሩ ላይ ተጠምጥሞ አላስኬድህም ማለት ነው ። አጥብቆ መለመን ታላቅ ተማጽኖ ፣ የነፍስ መርገብገብ ያለበት ነው ። አጥብቆ መለመን ብቸኛው መፍትሔ አንተ ብቻ ነህ ብሎ ሌሎች በሮችን ዘግቶ መምጣት ነው ። አጥብቆ መለመን በጉዳዬ ላይ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጅበት ብሎ መንግሥታዊ ሥልጣኑን መጠየቅ ነው ። አጥብቆ መለመን ከልማዳዊ ጸሎት የተለየ ፣ “በሰላም ያሳደርገኝ በሰላም አውለኝ” ከሚለው የፊት መታጠቢያ ጸሎት ጠለቅ ያለ ነው ። አጥብቆ መለመን አቅሜ ደክሟል ፣ ጉልበቴ ተሟጧል ፣ ተስፋዬ ላልቷል ፣ ጉዳዬ ሳይሞት እኔ ልቀድም ነው የሚል የመንፈስ ሲቃ ያለበት ጸሎት ነው ። 

እግዚአብሔር እንዲህ ያለውን ልመና ይወደዋል ። ካንገት ሳይሆን ካንጀት የቀረበ ፣ የራስን ደካማነትና የእርሱን ሁሉን ቻይነት ያመነ ነውና እንዲህ ያለው ጸሎት በእርሱ ዘንድ ሞገስ አለው ። እግዚአብሔር ይሰማል ፣ እኛ ግን በትክክለኛ ጸሎት ውስጥ ላንሆን እንችላለን ። ዙሪያው ገደል በሚመስልበት ፣ ቀኑ ጨለማ ሆኖ በሚታይበት ፣ ተስፋ የታጣ መስሎ በሚሳልበት ዘመን አጥብቆ መለመን መልካም ነው ። አጥብቆ መለመን የእግዚአብሔርን ፈቃድ በራስ ፈቃድ ማስለወጥ ፣ እጁን ጠምዝዞ ክርስቶስን መቀበል አይደለም ። አጥብቆ መጸለይ ከነሙሉ ሸክም ክርስቶስ በሚያልፍበት መንገድ ላይ መውደቅ ነው ። እንደ ክርስቲያን ከጸለይን እንደ እግዚአብሔርነቱ ይሰማል ።

ጌታችን ከእርሱ ጋር ሄደ ። ብዙ ሕዝብም ተከተሉት አጋፉትም ። ያ ሕዝብ አጥብቀው የሚጸልዩትን የሚመለከት እንጂ አጥብቆ የሚጸልይ አይመስልም ። እነ እገሌ የጸሎት ጓድ ናቸው የሚል እንጂ እኔም መጸለይ አለብኝ ብሎ የሚያስብ አይመስልም ። ሦስት ነገሮች እየታዩ መጡ ። 

የመጀመሪያው፡- የማይጸልይ በጸሎተኞች ግን የሚቀና ትውልድ ፣

ሁለተኛ፡- ክርስቶስን በልብ የተከተሉትን ቅዱሳን የሚያደንቅ እርሱ ግን በእግር የሚከተል ትውልድ ፤

ሦስተኛ፡- ክርስቶስን በእምነት የማይነካ ነገር ግን የሚያጋፋ ትውልድ ይታይ ነበር ። እንዲህ ያለ ትውልድ ባለመጸለዩ በሰው ኑሮ ሲቀና ይኖራል ። በልብ ባለመከተሉ የቤተ ክርስቲያን አባል ሆኖ የመንግሥተ ሰማያት መዝገብ ግን የማያውቀው ይሆናል ። ክርስቶስን በእምነት ባለመንካቱ የችግሩ ወንዝ ሲፈስስ ይኖራል ። 

ጌታችን ወደ ኢያኢሮስ ቤት እየተጓዘ ሳለ አሥራ ሁለት ዓመት ደም ይፈስሳት የነበረችይቱን ሴት አገኛት ። እርሷን ለመፈወስና የነፍስ አርነት ለመስጠት ከጉዞው ቆመ ። ኢያኢሮስ ግን፡- 

“እኔ ለምኜ እንዴት ሌላ ሰው ይድናል ?” 

“እኔ በአደባባይ ጸልዬ በድብቅ የነካ እንዴት ይፈወሳል ?” 

“የእኔ ችግር ጊዜ የማይሰጥ ሳለ እንዴት አሥራ ሁለት ዓመት ሳይገድል ለኖረ ችግር ቅድሚያ ይሰጣል ?

“ወደ እኔ ቤት እየተጓዘ እንዴት በአንዲት ሴት ይቆማል ?” አላለም ። 

•  ጸሎተኞች ለራሳቸው ብቻ ሳይሆን ፈውስ ለሚያስፈልገው ሁሉ ይጸልያሉ ። 

•  ጸሎተኞች እግዚአብሔር ለሁሉ በቂ መሆኑን ይቀበላሉ ።

•  ጸሎተኞች ሰው እንዲያያቸውና ምላስ ሁሉ ጸሎተኛ እንዲላቸው ጸሎትን ለማስታወቂያ ሥራ አይጠቀሙበትም ። 

•  ጸሎተኞች እግዚአብሔር የዘገየ ቢመስልም በእኔ አቆጣጠር እንጂ እርሱ ከሞትም ልደትን ማውጣት ይችላል ብለው ያምናሉ ። 

•  ጸሎተኞች ሰው ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ክቡር መሆኑን ይቀበላሉ ።

ኢያኢሮስ የቤቱ ሰዎችና ጎረቤቶቹ ወደ እርሱ እየሮጡ መጡ ። ክርስቶስና ሕዝቡ ሲመጡ አይተው ሰዓቱ ረፍዷል ለማለት ገሠገሡ ። ፀሐይን አቁሞ የሚሠራ የኢያሱ አምላክ መሆኑን ዘንግተዋል ። ጊዜን የፈጠረ ለጊዜ የማይገብር መሆኑን ማወቅ ተስኗቸዋል ። በእርሱ ዘንድ የመጨረሻ የሚባል ሰዓት እንደሌለ ፣ ለሞተው ነገር ሕይወት የሚሰጥ ፣ የሌለውንም እንዳለ አድርጎ መቍጠር የሚችል መሆኑን ገና አላወቁም ። “ልጅህ ሞታለች ስለምን መምህሩን ታደክመዋለህ ?” አሉት ። መምህሩ ግን ሰማይና ምድርን ሲሠራ ረክቶ ያረፈ እንጂ ደክሞት የተቀመጠ አይደለም ። መምህሩ ሰውን ለመፍጠር አልደከመም ፣ ሰውን ሰው ለማድረግ ግን ከሰማይ ወደ ምድር ወርዷል ። 

ልዩነቱ ያለው ኢያኢሮስ እንደ ጌታ እነርሱ እንደ መምህር ብቻ መቀበላቸው ነው ። እርሱ በሽተኛን ይፈውሳል ፣ እርሱ የሞተን ያሥነሣል ፣ እርሱ የሚወዱትን በሞት ላጡ ወገኖች መጽናናት ይሰጣል ። እነዚያ መርዶ አርጂዎች የተጨነቁት ለመምህሩ መድከም ሳይሆን ላለቀ ጉዳይ የዕድር ጉዳይን ለማቀላጠፍ ነው ። አሁን የሚያስፈልገው መምህሩ ሳይሆን የዕድር ሊቀ መንበሩ ነው ። ምክንያቱም ነገሩ አልቋልና ባዮች ናቸው ። የሚጠራ ዘመድ እንጂ የሚጠራ መምህር በዚህ ሰዓት የለም እያሉት ነው ። መምህሩን ስለ በሽታ ጠይቆ ጉዳዩ ወደ ሞት ያደገበት ኢያኢሮስ በአደባባይ ማፈር የገጠመው ይመስላል ። የለመነውን ቀርቶ ያለመነውን እንደሚቀበል ግን ቀጥሎ ያውቃል ። የለመነው ስለ በሽታ ፈውስ ነው ። የሚቀበለው ግን የሞት መልስን ነው ። ስለ ሥጋ ጠይቆ ስለ ነፍስ መልስ ያገኛል ። እግዚአብሔር ከለመኑት በላይ አትርፎ ይሰጣል ። አለቀ አበቃ በተባለ ነገር አዲስ ፀሐይ ያወጣል ። ይህን የሚያደርገው እኛ ኢያኢሮስ ስለሆንን ሳይሆን እርሱ እግዚአብሔር ስለሆነ  ነው ። ነገር ግን ቍርጥ ልመና ማቅረብ ይገባል ። ነገሩ ከድጡ ወደ ማጡ ፣ ከበሽታ ወደ ሞት ሊያድግ ይችላል ። እግዚአብሔርን የችግራችን ትልቅነት አይመልሰውም ፣ የእምነታችን ማነስ ግን ይመልሰዋል ። እግዚአብሔር እንደሚችል ማመን እንጂ እንዴት እንደሚችል መመራመር ከፍጡር አይጠበቀም ። 

ጌታችን ለኢያኢሮስ የተነገረውን ለእኔ ብሎ ሰማ ። ኢያኢሮስ የስንፍናም የብርታትም ድምፅ ሳያሰማ ጌታችን ቀድሞ መልስ ሰጠ ። ኢያኢሮስ ስለሞት ሰማ ። ጌታችን ግን፡- “እመን ብቻ እንጂ አትፍራ” አለው ። የሚጠበቀው መውጣት መውረድ ፣ የሚፈለገው አቅምን መፈተሸ ፣ የሚያሻው የጉዳዩን ክብደት ከዕድርተኛ ጋር መምከር አይደለም ። ማመን ብቻ ነው ። እምነት ያስፈለገው የሚታይ ነገር ሲጠፋ ፣ የማይታየውን ለማየት ነው ። እናንተም እመኑ ብቻ እንጂ አትፍሩ ።

በብርሃን ዋሉ!

ይቀጥላል

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ታኅሣሥ 13 ቀን 2013 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ