የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ወለተ ኢያኢሮስ / 7

 

ጌታችን መርዶ የገጠመውን ኢያኢሮስን ፣ የልጁን ሞት እንደ ዋዛ የሰማውን አባት ፣ በአደባባይ “ልጅህ ሞታለች” ተብሎ በሕዝብ ፊት የተረዳውን የምኵራብ አለቃ፡- “እመን ብቻ እንጂ አትፍራ” አለው ። አዳኝ አገኘሁ ፣ ያስጨነቀኝን በሽታ የሚያስጨንቀውን ወደ ቤቴ ይዤ መጣሁ እያለ እያንዳንዱን እርምጃ እንደ ኪሎ ሜትሮች እየቆጠረ ፣ ቅርብ የነበረው እልፍኙ ርቆበት ፣ ደቂቃው ዓመት ሁኖበት ፣ አምላኩን ሊያሳይ ፣ ያመንኩት ትልቅ ነው ብሎ ሊመካ የጎመዠውን ሰው ወሽመጡን የሚቆርጥ ፣ እምነቱን የሚጋፋ ነገር ተናገሩት ። ጌታችን ግን እነርሱን ትቶ ላመነው የእምነት ድምፅ አሰማው ። ጌታችን ከከሀድያን ጋር አይከራከርም ፣ አማንያንን ግን ያሳምናል ። “እመን ብቻ እንጂ አትፍራ” አለው ። ለበሽታ ስጸልይ ሞት መጣብኝ ብለህ በመጸለይህ እንዳትደነግጥ “እመን ብቻ እንጂ አትፍራ ።” በቤቴ የምስጋና መሥዋዕት ላቀርብ ነው ስል የልቅሶ ዜማ ሊያስተጋባ ነው ብለህ አትፍራ ፤ በአደባባይ ለምኜ በአደባባይ ላፍር ነው ወይ ? ድሮስ ክርስቶስን የተከተለ ምን ያገኛል ? ብለው የምኵራብ ባልደረቦቼ ሊያላግጡብኝ ነው ወይ ? ብለህ አትጨነቅ ፤ “እመን ብቻ እንጂ አትፍራ ።” የቤቴን ገበና አደባባይ አውጥቼ ራቁቴን ቆሜ ልቀር ነው ወይ ? ብለህ ለሰው እንደ ነገርህ አድርገህ እንዳትሸማቀቅ ፤ “እመን ብቻ እንጂ አትፍራ ።” 

ኢያኢሮስ በዚህ ሰዓት ከማመን ውጭ ምንም ነገር የለውም ። ባለ መድኃኒት ጋ የሚሄድበት ፣ ቅጠል የሚበጥስበት ፣ መላ የሚሞክርበት ጊዜ አይደለም ። የሞት ሐኪም ፣ የሞትም መድኃኒት በዓለም ላይ የለም ። ያለው ዕድል ማመን ብቻ ነው ። የእናንተ ጉዳይ ያለቀ ነው ሲባል የሚቀረን ነገር ማመን ብቻ ነው ። የምታስታምሙት ጉዳይ ሞቷል መቅበር ብቻ ነው ብለው ሲያረዱን የሚቀረን እምነት ብቻ ነው ።  ታሪካችሁ መክኗል ፣ ሕይወታችሁ ወይቧል ሲሉን የሚቀረን ማመን ብቻ ነው ።  የደበቅነው በሽታውን ቢሆንም ሞት ግን አደባባይ ያወጣል ። ሁሉ ይሰማዋል ። የተዘጋው ደጅ ሁሉ ሞት ሲመጣ ይከፈታል ። ብቻውን ያስታመመ ብቻውን አይቀብርም ። ሞት አጋላጭ ነው ። ባስታመምነው ቍጥር የባሰበት ፣ በጸለይን ቍጥር የሞተ ጉዳይ ካለ ደስ ይበለን ። ብቻ ክርስቶስን ወደ ቤታችን ይዘን እንገስግስ ። እርሱ ሲገባበት ቤታችን እንደ ቅድሙ አይሆንም ። ልቅሶ በደስታ ዜማ ይለወጣል ። ቃሬዛ የሚሠሩ እንጨቱን ይሰብራሉ ። አቃብሩኝ ተብለው በዕድር ጡሩምባ የመጡ በመዝሙር በእልልታ ይውላሉ ። አሳሳቢው የጉዳዩ መሞት ሳይሆን ክርስቶስን አላደክመውም ብሎ እየመጣ ያለውን ጌታ ቆይ ማለት ነው ። በትሕትና የመጣው ጌታ በጌትነት ይሠራል ። 

ፍርሃት ያጠላበት ኑሮ ውስጥ የሰው ልጆች ያልፋሉ ። ፍቅርን ይፈራሉ ፣ ቀጥሎ መካሰስ ቢመጣስ ብለው ይጨነቃሉ ። ጠብን ይፈራሉ ፣ የጅል ጠብ ከገጠመ ማለቂያ የለውም ብለው ይደነግጣሉ ። ቸርነትን ይፈራሉ ፣ ደግ ሲጠቃ ያያሉ ።  ንፍገትን ይጠላሉ ፣ ካልቀቁ ከሰማይ እንደማይለቀቅ ይሰማቸዋል ። ሁሉን የፈራን ነንና “አትፍሩ” ይለናል ። 

ጌታችን ወደ ኢያኢሮስ ቤት ሲገሰግስ የምሥጢር ደቀ መዛሙርቱን ሦስቱን ጴጥሮስን ፣ ዮሐንስንና ያዕቆብን ይዞ ነው ። ከልጅም ልጅ አለው ። ከደቀ መዛሙርትም ሁሉን እንዲያውቁ የሚፈቀድላቸው የምሥጢር ደቀ መዛሙርት ያስፈልጋሉ ። ሁሉም ልጅ ቢሆንም አባት ለይቶ እናቴ የሚላት ልጅ አለች ። ሁሉም ልጅ ቢሆንም አባቴ እየተባለ የሚጠራ የልጅ አዋቂና መካሪ አለ ። ሁሉን መጋበዝ የመምህርነት ወግ አይደለም ። የምሥጢር አገልጋዮች ያስፈልጋሉ ። ወደ ኢያኢሮስ ቤትም ከእነዚህ የምሥጢር ደቀ መዛሙርት በቀር ማንም እንዳይከተለው ጌታ አደረገ ። ወደ ኢያኢሮስ ቤት ሲቃረብ ብዙ ጫጫታና ልቅሶ ይሰማል ። እንደ ነዋሪነቱ ፣ እንደ አለቅነቱም ፣ እንደ ሕዝብ አገልጋይነቱም የእርሱ ቤት ልቅሶ ደማቅ ነው ። አልቃሾቹም ጌታንና ተከታዮቹን ሲያዩ ተጨማሪ ለቀስተኛ የመጣ መስሎአቸው በእንባ ለመራጨት ፈልገዋል ። ጌታ ግን እንባን ሊገድብ መጥቷል ። ሁሉንም ደቀ መዛሙርት መያዝ ያልፈለገው እንደ ማርታ ቤት አይደለምና ቤቱ እንዳይጨናነቅ አስቦም ነው ። ሐኪም እንኳ በሽተኛ መጥቶለት ያክማል ። እርሱ ግን ራሱ የመጣ ነው ። የሞት መድኃኒት በእጁ አለና በትሕትና ገባ ። የሚታበዩ የሞት መድኃኒት የሌላቸው ናቸው ። የበሽታ መድኃኒት ያላቸው በሚታበዩበት ዓለም ፣ የሞት መድኃኒት ያለው በትሕትና ተጓዘ ። መታበይ እንዳለን እርግጠኛ አለመሆን የሚወልደው ነው ። 

ጌታችን ለቀስተኞቹን ፡- “ስለ ምን ትንጫጫላችሁ ታለቅሳላችሁም? ብላቴናይቱ ተኝታለች እንጂ አልሞተችም” አላቸው ። መንጫጫት ካለ የልጅቱ ነፍስ የወጣው በቅርብ ሰዓት ነው ። ማዜም ካለ ደግሞ ሲረጋጉ የሚቀርብ ሙሾ ነው ። የቅርቡ ሲንጫጫ ፣ ብዙም የማይደነግጠው የሩቁ ያዜማል ። የሚንጫጩ ልቅሶው አይወጣላቸውም ፣ በዜማ የሚያስነኩት ግን እፎይ ይላሉ ፣ ኀዘኑ ይወጣላቸዋል ። ማልቀስ በተገቢው ሰዓት አስፈላጊ ነው ። ያልተገለጠ ኀዘን ቆይቶ ጭንቀት ይሆናል ። የሰለጠነው ምድር የጭንቀት በሽታ ኀዘናቸውን በሳቅ ስለሚያሳልፉት ፣ በቡና ስለሚሸነግሉት ነው ። ብዙ እየቀበርን የማናብደው ኀዘንን የምንገልጥበት ሥርዓትና ዜማ ስላለን ነው ። አይብዛ እንጂ ኀዘን መገለጥ አለበት ። ራስን በመግዛት ፣ ሰውን ባለማስቸገር ፣ የምንናገረውን በመምረጥ ማዜም ማልቀስ አስፈላጊ ነው ። ጌታችን እንኳ እንደሚያሥነሣው እያወቀ በአልዓዛር መቃብር ላይ አልቅሷል ። አለማልቀስ የክርስቲያንነት ሳይሆን የአረመኔነት ምልክት ነው ። ኀዘን በወጉ እንዲገለጥ መጽሐፍ ይነግረናል ። 

ጌታችን አልሞተችም ሲል በርግጥ ነፍስዋ አልወጣም ማለቱ አይደለም ። ለእናንተ ያበቃ ነገር ለእኔ ገና ነው ማለቱ ነው ። ሁሉም ነገር በፊቱ ማለዳ ነው ። ሠርክ የሌለበት አምላክ አለን ። እነዚያ ሲንጫጩ የነበሩ አልቃሾች በጣምም ሳቁበት ። ይህ ሳቅ ከስድብ በላይ ነው ። ሰዎች ሁኔታንና ራሳቸውን በማየት ለነገሮች ድምዳሜ ይሰጣሉ ። እግዚአብሔር ራሱን አይቶ ሲናገራቸው ማመን ይቸገራሉ ። ጌታ ያደረገው ነገር ቢኖር ሁሉንም አስወጣና የብላቴናይቱን አባትና እናት ፣ ሦስቱን ደቀ መዛሙርት አስከትሎ ሬሳው ያለበትን እልፍኝ በሩን ዘጋ ። ሲናገር ሙትም ይሰማዋልና እጅዋን ይዞ “ጣሊታ ቁሚ አላት ። ፍችውም ብላቴና ማለት ነው ።” ለሞተች ልጅ ዓይንሽን ግለጪ ማለትም በቂ አይደለም ወይ ? ቢሉ ጌታ ሲፈውስ ከበሽታው በፊት ወደ ነበረው ማንነት ሳይሆን ከዚያ ወደ በለጠ ኃይል ይመልሳል ። ብላቴናይቱም የአሥራ ሁለት ዓመት ልጅ ነበረችና ወዲያው ቆማ ተመላለሰች ። እነዚያ የሳቁ ሁሉ ደነገጡ ፣ መገረም ሞላባቸው ። ጌታችን ይህን ማንም እንዳያውቅ ብሎ አዘዘ ። የምትበሉአትም ስጡአት አላቸው ። ሩቅ አገር ደርሶ ለመጣ እንኳ ምግብ ያሻዋል ። ሰማይ ደርሳ ለመጣች ሩቅ መንገደኛ ምግብ ስጡአት አለ ። የዳኑና ከሞት ያመለጡ ምግብ ያስፈልጋቸዋል ። ሕይወት ቀጣይ የሚሆነው በምግብ ወይም በቃሉ ነውና ። ብዙዎች ከሞት ድነዋል ፣ የቃሉን ምግብ ስላላገኙ ግን ሕይወታቸው ጭል ጭል እያለ ነው ።

ጌታ ለማንም እንዳይናገሩ ማዘዙ  ኢያኢሮስ የምኵራብ አለቃ እንደመሆኑ ብዙ ጠላት እንዳያፈራ ፣ እምነቱ እስኪጠነክር ድረስ ከነፋስ ሊጠብቀው ነው ። ጌታችን ለአቅማችንም ይጨነቃል ። ጌታችን በአንድ ፈውስ ውስጥ ብዙ ፈውስ ይሰጣል ። የሥጋ ፈውስ ወደ ነፍስ ፈውስ ያደርሳል ፣ የነፍስ ፈውስም ወደ ሥጋ ፈውስ ያደርሳል ። ሁለንተናን የሚፈውስ ጌታ ክርስቶስ ነው   ። 

እመኑ ብቻ እንጂ አትፍሩ ።

እግዚአብሔር ልመናችሁን ይፈጽምላችሁ ። 

ተከታታዩ ጽሑፍ ተፈጸመ

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ታሕሣሥ 15 ቀን 2013 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ