ድሀ ፊደሉም ሁለት ነው፣ ሀብታም ግን ፊደሉም አራት ነው። አፍ ተከፍቶ የሚነገሩ ቃላት፣ አፍ እየከደኑ የሚነገሩ ቃላት አሉ። ድሀ የሚለውን ቃል ለመናገር አፍ ይከፈታል፣ ሀብታም ብለው ሲናገሩ ከንፈር ይዘጋል። በድሀ ላይ የማይላቀቅ አፍ ፣ ለሀብታም ዝም የማይል ከንፈር የለም። ድሀ ጥበብ ቢናገርም የሚሰማው የለም። ጥበብ ከድሀ ነበርሽ ፣ ማን ቢሰማሸ! ይባላል። ባለጠጋ ወዝም ጣዕምም የሌለው ነገር ቢናገር እንደ ጥቅስ ይወራል፣ በማስታወሻ ይያዝለታል ። የሰው ልጅ ምንም ይዞ ያልመጣ ምንም ይዞ የማይሄድ ነው። ነገር ግን ይኮራል፣ ድሀ ብሎ ለመሳደብ ይቸኩላል፣ ሀብታም ብሎ እጅ ለመንሣት ይሯሯጣል። ድሀ በትክክል የሚጠላውን ያውቃል፣ ሀብታም ግን ወዳጅና ጠላቱን ማወቅ አይችልም። ባለጠጎች ቁምነገርን ከድሀ ፣ ድሆችም በረከትን ከሀብታም እንዲካፈሉ ተወስኗል።
ድሀ ነገሩ መራራ ነው። ባለጠጋው ታሞ ድሀው ተመላልሶ ቢጠይቅም ማንም ልብ አይለውም። ድሀው ግን ታሞ የሚጠይቀው አጥቶ፣ የተሻለው ቀን ባለጠጋው ቤት ሄደ የጠፋኹት ታምሜ ነው ብሎ ሪፖርት ያደርጋል። ስላልጠየቁት የመቀየም መብት የለውም። ተሽሎት የጠፋበትን ምክንያት ለማሳወቅ ይተጋል። ድሀ ይሉኝታ ኣለው። ሥርዓት የሌለው ባለጠጋ እንዳለ ሁሉ የጠባይ ምስኪን የሆነ ድሀም አለ። ገንዘብ አመል ይዞ ይመጣልና የድሀ ልጅ ያገኘና የተሾመ ቀን ምድር ትጨነቃለች። ድሀ ወርቅ አይግዛ ከገዛም አያብዛ ይላሉ። የድሀ ልጅ ወርቅ አይለምድም ይባላል። የሞል በሽታ የሚይዘው የድሀ ልጅን ነው። ድህነቱ ሄዶለት እንኳ ተመልሶ ቢመጣስ እያለ የሚባንን፣ የሚያግበሰብስ ብዙ ነው።
የገንዘብ እንጂ የዕድሜ ድሀ ባትሆንም ሁሉ ይልክሃል። ነገርህ መራራ ይሆናል። ስትስቅ አስመሳይ፣ ስታለቅስ ብሶተኛ ይሉሃል። ስታጣ ለምን ድሀ ሆነ ? ብለው ጥናት ያላደረጉ አሁን ስታገኝ የገንዘብ ምንጩ ይጠና ይሉሃል። ድሀ ስትሆን ሃይማኖተኞች ተጠራጣሪ ብለው ያወግዙሃል፣ ታጣቂዎች ይገርፉሃል። አንቱ ተብለህ ሳትጠራ ታረጃለህ። ያገኘህ ቀን ለሁሉ ቆንጆ ሆነህ ትታያለህ። ስህተት ብትናገር ንግግርህን በወጌሻ የሚያስተካክልልህ አፈ ቀላጤ ታገኛለህ። ታሪክ ባይኖርህም ዜና መዋዕልህን ልጻፍ የሚል ደራሲ ይንጋጋልሃል። የሚያወግዝህ የለም፣ እንዳንተ ያለ ቆንጆ እንደሌለ ምለው ይነግሩሃል። ለምን መሰለህ ? ወርቅና ጨዋ አስታራቂ ነው! አንተን ክፉ ማለት ብዙዎች ይከብዳቸዋል። ስህተትህን በአጉሊ መነጽር እንዳላዩ ዛሬ በካባ ይሸፍኑታል።
ባልዋ የበደላት፣ ወደ ሌላ ሴት ሄዶ ያሳዘናት ሚስት ወርቅ ይካሳት ተብሎ ትታረቃለች። ጨዋም አስታራቂ ነው። ተው ባይ፣ ገላጋይ፣ እሳት አጥፊ ፣ ድልድይ ሠሪ ነው። አግድም አደግ ነገር ያባብሳል፣ በሌሎች ሁከት ይደሰታል። “የእብድ ገላጋይ ድንጋይ አቀባይ” እንዲሉ።
ሁሉ የሚረባረብብህ ድሀ ስትሆን ነው፣ ነገሩ አይጥመኝም የሚሉህ ያለ ጉርሻ የማይስቁት ናቸው።
የአሜሪካ ፕሬዝዳንትና የዩክሬን ፕሬዝዳንት በፖፕ ፍራንሲስ ቀብር ላይ አመርቂ ውይይት አደረጉ ተባለ። ወዲያው በውድ ማዕድናት ዙሪያ ዩክሬን ፈረመች። የሞቱት ፖፕ ግን በድህነት እንደኖሩ ድሆች በሚቀበሩበት ሳንታ ማሪያ ቤተ ክርስቲያን እንደ ተቀበሩ ፣ ምንም የግል ሀብት የሌላቸው መቶ ዶላር ብቻ የተገኘባቸው እንደሆኑ ተነግሯል።
እግዚአብሔር ግን ያለ ወርቅ ይታረቅሃል !
ክብር ለሥላሴ !
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሚያዝያ 24 ቀን 2017 ዓ.ም.