የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ወሰነን

“በበጎ ፈቃዱ እንደ ወደደ ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥራ ለእርሱ ልጆች ልንሆን አስቀድሞ ወሰነን ።” ኤፌ. 1 ፡ 5 ።

ይህን ዘመን እንደ ዓይን እንዳያጠፋው የሚያሰጋው ፣ በማር የተለወሰ መርዛማ ትምህርት አለ ። የመጀመሪያው፡- “በመንፈስህ ጸድቀሃል ፣ በሥጋህ ማንኛውንም ኃጢአት ብትሠራ አትጠየቅም” የሚለው ነው ። ሁለተኛው፡- “የሚጸድቀውና የሚኰነነው አስቀድሞ ተወስኗል” የሚል የስህተት ትምህርት ነው ። የእነዚህ ስህተቶች ጫና ምንድነው ? ካልን ትውልድን መረን የሚያደርግ ፣ የነውር ውድድር ውስጥ የሚከትትና በመጨረሻ ወጣቶች በራሳቸው ላይ አደጋ እንዲያደርሱ የሚያደርግ ነው ። ጌታችን ለሥጋችንም ሞቷል ። ለሥጋችን የሞተው ሥጋችንን ሊቤዠውና መቅደሱ ሊያደርገው ነው ። ሐዋርያው በዝሙት ሥጋቸውን ላረከሱ ሰዎች፡- “ወይስ ሥጋችሁ ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁት በእናንተ የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደ ሆነ አታውቁምን ? በዋጋ ተገዝታችኋልና ለራሳችሁ አይደላችሁም ፤ ስለዚህ በሥጋችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ” ይላል ። 1ቆሮ. 6 ፡ 19-20 ። በዚህ ክፍል ላይ ሥጋችሁ ፣ በሥጋችሁ ይላል እንጂ ነፍሳችሁ አይልም ። እጄ ቢመታህ በሥጋዬ እንጂ በመንፈሴ ወይም በነፍሴ አልመታሁህም የሚል ሞኝ የለም ። ሥጋዬ አርነት ወጥቷል ብሎም በፖሊስ ፊት የሚሰርቅ ጎበዝ አላየንም ። ጌታችን በሥጋው መከራ መቀበሉ ፣ መንፈስ ቅዱስም ቤተ መቅደስ አድርጎ ሥጋችንን መምረጡ ከኃጢአት እንርቅ ዘንድ ነው ።

ሥጋችን ተስፋ የሚያደርገው አዲሱን የትንሣኤ አካል ነው ። የትንሣኤ አካል ሥጋችን የኃጢአት ፈተናና ተግባር የሌለበት የተቀደሰ ማንነት ነው ። ሥጋችን ፍጹም የሆነ ማንነትን እየጠበቀ በሥጋህ የምትሠራው ኃጢአት አያስጠይቅህም እንዴት ሊባል ይችላል ? ሰው መንፈሱ ጸድቆስ ሥጋው እንዴት ሊቀር ይችላል ? ክርስቶስን ያመንነው በሥጋም በነፍስም ተዋሕዶ ሆነን አይደለም ወይ ? ለጌትነቱ የሚሰግደው ፣ ለክብሩ የሚያሸበሽበው ሥጋችን ፣ ላልገዛውና ላላዳነው እንዴት አምልኮ ይሰጣል ? ሥጋና ነፍስ በተዋሕዶ እስካሉ ድረስ ብቻ ደግና ክፉ ይሠራሉ ። ሥጋና ነፍስ ሲለያዩ ግን ተጠያቂነት እንጂ የደግና የክፉ ግብር አጋጣሚ የለም ። በዳግም ምጽአት ሥጋ ከመቃብር ፣ ነፍስ ካለችበት መጥታ በተዋሕዶ የሚቆሙት ለደግነታቸውና ለክፋታቸው ዋጋ ለመቀበል ነው ። ደግሞም ክርስቶስ ሙሉ አዳኝ እንጂ ከፊል አዳኝ አይደለም ። እርሱ ነፍስን አጽቆ ሥጋችንን አይተወውም ። ሥጋችን ላይ ዓላማ ባይኖረው ሥጋችንን አይዋሐደውም ነበር ። የተዋሐደው ሊያድነው ነው ።

ይህ ትምህርት በፕሮቴስታንት ዓለም አደጋ እየፈጠረ ነው ፣ እኛን አያሰጋንም አንልም ። ለዚህም ሁለት ምክንያት እንጠቅሳለን ። የመጀመሪያው የእነርሱም መጥፋት ሊያሳዝነን ይገባል ። ወገኖቻችን ናቸውና ። ሁለተኛው ኦርቶዶክሳዊነትን በፕሮቴስታንት ባሕል ለማጥመቅ የሚሠራ ቡድን በውስጥ አርበኝነት ስላለ ይህ ትምህርት አይነካንም ማለት አስቸጋሪ ነው ።

የሚጸድቀውና የሚኰነነው አስቀድሞ ተወስኗል ማለት ስብከተ ወንጌልን የሚያዳክም ነው ። ወንጌልን ይዞ ወደ አሕዛብ መሮጥ እየቀረ የመጣው ይህ የስህተት ትምህርት ከተስፋፋበት ከ16ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ነው ። ክርስቲያን ክርስቲያንን ማጥመቅ የጀመረው ፣ የበግ ሌብነት የጀመረው ከዚህ የስህተት ትምህርት በኋላ ነው ። በግ የማድረግ አገልግሎት በግ ወደ መስረቅ ያደገው በዚህ ትምህርት ነውና ጸንተን ልንዋጋው ይገባል ። እግዚአብሔር አስቀድሞ ከወሰነ ሐዋርያትን ስበኩ ብሎ ለምን ያደክማቸዋል ? እኛስ ለምን እንጽፋለን ? እግዚአብሔር ሁሉን ያውቃል ። ማወቁ ግን መወሰኑ አይደለም ። የልጃችንን አካሄድ አይተን እንደሚወድቅ እርግጠኞች እንሆናለን ። ለዚህም አስቀድመን ምክር እንሰጣለን ፣ እናስጠነቅቃለን ። ልጁ ግን እንቢ ብሎ ይወድቃል ። ማወቃችን ልጁ እንዲወድቅ መፍቀዳችን አይደለም ። ማወቃችንም መሰናክል ሁኖ አልጣለውም ። ቢያውቅበት ኑሮ ማወቃችን ይጠብቀው ነበር ። እግዚአብሔር አዳም እንደሚወድቅ እያወቀ ለምን ፈጠረው ? የሚሉ ወገኖች አሉ ። ማወቁ ግን መወሰኑ አይደለም ። እንደሚበድለው እያወቀ መፍጠሩ ግን ፍቅር ነው ያሰኘዋል ። አኔ እንደሚበድለኝ አስቀድሜ የማውቀውን አልወዳጀውም ። እግዚአብሔር ግን ከአዳም ቢጎድል ከእኔ እሞላለታለሁ ብሎ ፈጠረው ። ማወቅ መወሰን አይደለም ። እግዚአብሔር አስቀድሞ ከወሰነ ሊፈርድ አይችልም ። ምክንያቱም ሰውዬው እግዚአብሔር የወሰነበትን ሁኗልና ሊጠየቅ አይገባውም ። የትኛውም ሰው ፈቃድ የእግዚአብሔርን ውሳኔ ሊቀለብስ አይችልምና ። እግዚአብሔር ግን የወሰነው ሁላችንንም ለማጽደቅ ነው ። እኛ ለመጽደቅ ብንፈልግ አጽዳቂው ግን ካልፈለገ ተኰናኝ ነን ። ከእኛ የጽድቅ ጥማት እግዚአብሔር እኛን ልጆቹ እንድንሆን መወሰኑ ይገርማል ።

ምስጋና ለጌትነት ክብሩ ፣ ለአስደናቂ ግብሩ !

የኤፌሶን መልእክት ትርጓሜ /7

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
የካቲት 8 ቀን 2014 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ