የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ወንጌል ምንድነው ?


“እኔም ለዚህ ነገር አዋጅ ነጋሪና ሐዋርያ በእምነትና በእውነትም የአሕዛብ አስተማሪ ለመሆን ተሾምሁ ፤ እውነት እናገራለሁ ፤ አልዋሽም ።” 1ጢሞ. 2፡7
የኬንያው መሪ የነበሩት ጆሞ ኬኔያታ፡- “ፈረንጆቹ ጌታን ተቀበሉ አሉን ፣ እኛም እሺ ብለን ተቀበልን ፤ ዓይናችሁን ጨፍናችሁ ጸልዩ አሉን ፣ እኛም ዓይናችንን ጨፍነን ጸለይን ፤ ዓይናችንን ስንገልጥ ግን መሬታችንን ወስደውታል” በማለት ተናግረዋል ። ወንጌልን የቅኝ ግዛት መሣሪያ አድርገው አፍሪካን የወረሩ አያሌ ናቸው ። ዛሬ ታሪካቸውን ሳያጣሩ ለአፍሪካ ዋጋ የከፈሉ ሰማዕታት በማለት በአገራችን ወንጌላውያን ሳይቀር የሚሞገሱት አፍሪካን ያዋረዱ ፣ ታሪኳን ያጠፉ ፣ ቅኝ ገዥዎችን መንገድ መርተው ያመጡ ፣ “እነዚህን እንስሳ ሕዝቦች ማሰልጠን ከእግዚአብሔር የተሰጣችሁ አደራ ነው” ብለው በአውሮፓ ቤተ መንግሥት የሰበኩ ናቸው ። “እመት ስመኝ ለማያውቅሽ ታጠኝ” ይባላል ። ታላቁ ንጉሠ ነገሥት ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግ የታገሉ ዐፄ ተዎድሮስ ሚስዮናውያኑን አልቀበልም ብለው ሲናገሩ፡- “መጀመሪያ ወንጌል የሚሰብክ ትልካላችሁ ፣ ቀጥሎ እርሱን የሚረዳ ብላችሁ ቆንሲል ታመጣላችሁ ፤ በመጨረሻ የጦር መሪ ልካችሁ አገር ትወርራላችሁ” ብለዋል ። ያሉት አልቀረም መጀመሪያ ወንጌል ሰባኪ ፣ ቀጥሎ ቆንሲል በመጨረሻ ጀነራል ናፒር ተልኮ የእርሳቸውም ሕይወት በመቅደላ አምባ አለፈ ። ዐፄ ዮሐንስም ወንጌል ልንሰብክ መጥተናል ያሉትን ሚስዮናውያን፡- “የአይሁድን አገር እስራኤል ፣ የእስላምን አገር ምድረ ዐረብ አልፋችሁ እንዴት እኛ ጋ ወንጌል ልትሰብኩ መጣችሁ ፣ እኛ በወንጌል እናምናለን” በማለት አባርረዋል ።  

አፍሪካን የማጥ ጉዞ ውስጥ የከተታት በወንጌል ስም የመጡባት ወራሪዎች ናቸው ። ወጣሁ ስትል የምትያዘው ፣ በአጉል የአምልኮ ልምምድ የጠፋችው አፍሪካ የዚህ ገፈት ቀማሽ ሁና ነው ። ወንጌል የምሥራችንና የእግዚአብሔርን አሳብ ይዞ የሚጓዝ እንጂ ባሕልና የኢንዱስትሪ አብዮት ይዞ የሚጓዝ አይደለም ። በአገራችን ወንጌል ሲሰበክ ነጠላውን እንዲተውና የፈረንጅ ሙሉ ልብስ እንዲለብስ ተደረገ ። በዚህም የአገራችን ሸማኔ ሥራ አጣ ። ምዕራባውያን ወንጌሉን የተጠቀሙበት የኢንዱስትሪ አብዮታቸውንም ለማስተዋወቅ ነው ። “አፀድ የሌለው ደብር ፣ ጢም የሌለው መምህር አይከብድም” በሚባልበት ባሕል ሰባኪዎቹ ጢምን ሙልጭ አድርገው ከባሕል ውጭ እንዲመጡ ተደረገ ። በአገራችን የሚሠሩ የፕሮቴስታንት አብያተ ክርስቲያናት የተገለበጠ የእንግሊዘኛው V ፊደል የሚመስሉ ናቸው ። ይህ አሠራር በረዶ ላለባቸው አገሮች ለማንሸራተት የሚውል ነው ። በረዶ በሌለበት አገር በረዶ የሚያንሸራትት ቤተ ክርስቲያን መሥራት ወንጌል ሳይሆን የሌሎች ባሕል እየተጫነን ለመሆኑ ማሳያ ነው ። በምድሪቱ ላይ ያለች ፣ በኢትዮጵያ ስም የምትጠራ ቤተ ክርስቲያን እያለች ሌላ ቤተ ክርስቲያን ማቋቋም ተገቢም አልነበረም ። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ለማገዝና ለመርዳት ሳይሆን ለማፍረስ ለዘመናት ተሠርቷል ። ውጤቱ ምን ሆነ ? ሃይማኖቱን ወዝ የለሽ አድርገውት የቀረውን አገር ደግሞ ለመናድ ጉዞ ላይ ያሉ ይመስላል ።
ወንጌል ተብሎ የተሰበከው ሰውን ከእናት ቤተ ክርስቲያኑ ማፈናቀል ነው ። በዚህም ሥርዓት የለሽ ትውልድ ፣ ተዋረድ የሌለው መዋቅር ፣ መከባበር ያጣ ክርስትና ፣ ሌላውን መናቅና መኰነን ያለበት ስብከት ተወለደ ። ወንጌል እየተባለ የሚሰበከው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንንም እንደ እርግጠኛ ጠላት ማየት ፣ የገዛ ልጆቿን እየመለመሉ የውስጥ አርበኛ አድርጎ ማፍረስ ነው ። ውጤቱ ግን ለማንም የማይሆን ራሱንም የከሰረ ትውልድ ማፍራት ሆነ ። ይህ ብቻ አይደለም የበታችነት ስሜት የሚሰማውና ጥላቻን የተሞላ ትውልድ በወንጌል ስም ስለ ተመረተ ጸሎቱ ፉከራ ፣ ስብከቱ ነቀፋ ፣ ከሰው ጋር ያለው መቀራረብ ወገናዊ ፣ የተለየ አሳብን አውጋዥ ሆነ ። ኢየሱስ የግሌ ብቻ ማለት ፣ እንደ እኔ የማያምን ሰው ርኩስ ነው ብሎ መደምደም ፣ አውቄአለሁ ብሎ ጨርሶ መኖር የበታችነት ስሜት የሚወልደው ነው ። እገሌ ያልዳነ ነው ፣ ያልበራለት ነው እያሉ መሳለቅ ያው የበታችነት ስቃይ የሚወልደው ነው ። እግዚአብሔርን ግን በጅምላ ገዝቶ በችርቻሮ የሚያከፋፍል ማንም የለም ። እርሱ የሁሉ አምላክ ነው ። ወንጌል ፍቅር እንጂ ጥላቻ አይደለም ። ወንጌል ሕይወት እንጂ ቃል አይደለም ። እነርሱ ሳይወዱኝ ኢየሱስ ይወድሃል ቢሉኝ እየዋሹኝ ነው ። አምላካቸው እንደሚወደኝ የማውቀው እነርሱ ሲወዱኝ ሳይ ነው ።
ወንጌል አሉታዊ ስብከት አይደለም ። ሐዋርያት ሙሴ አያድንም ፣ ምኵራብ አይጠቅምም ብለው አላስተማሩም ። በምኵራቡ ሰበኩበት ፣ ኦሪቱን ጠቅሰው አሳመኑበት ። “ያልተማረ ሁሉን ያረክስ ፣ የተማረ ሁሉን ይቀድስ” ይባል የለ!
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፡- “እኔም ለዚህ ነገር አዋጅ ነጋሪና ሐዋርያ በእምነትና በእውነትም የአሕዛብ አስተማሪ ለመሆን ተሾምሁ ፤ እውነት እናገራለሁ ፤ አልዋሽም” ይላል 1ጢሞ. 2፡7
ሐዋርያው የተላክሁት ወንጌልን ልሰብክ ነው ይላል ። ወንጌል የእግዚአብሔር ማዳን ፣ የእስረኞች ነጻ መውጣት ፣ የዕዳ መከፈል ዜና ነው ። አብዛኛው ሰው ወንጌሉን ሳይሆን የተሰበከበትን መንገድ ተቃውሟል ። ሁሉም ሰው የራሱ ክብር አለው ፣ ወደ ሌላው ግዛት የሚገባ የሌላውን ባሕልና ታሪክ ካላከበረ ጠላትነትን ያበዛል ። ወደው ባመጡት እሳት የሚቃጠሉ ባለጌዎች እንጂ ሰማዕታት አይባሉም ። ሐዋርያው ለወንጌል አዋጅ ነጋሪ ነኝ ይላል ። አዋጅ ንጉሣዊ ድምፅ ፣ የሰማ ላልሰማ የሚያሰማው ፣ የማይጣስ ቀይ መስመር ነው ። ወንጌል የእግዚአብሔር ልጅ ለዓለም ቤዛ ሁኖ መሞቱን የምትናገር ናት ። የመንግሥቱ አዋጅም ናት ። መስማት ይገባል ፣ ላልሰማም ማሰማት ግድ ይላል ። ወንጌልን የሚሰብኩ ሰዎች ተራ ሥራ እየሠሩ ሳይሆን ንጉሣዊ መልእክትን ይዘው እየተጓዙ ነው ። በጥንት ዘመን የንጉሥን መልእክት የያዘ ሰው በደረሰበት ሁሉ አክብረው ይቀበሉት ነበር ። መልእክተኛውን መናቅ የላከውን መናቅ ነው ። ከመልእክቱ ጀርባ በረከትና ቅጣት አለ ። ወንጌል የእግዚአብሔር የምሥራች ነው ። የተሰበከበት መንገድ ግን የመርዶ ድምፅ የሰሙ እስኪመስላቸው ብዙዎችን አስደንግጧል ።
ቅዱስ ጳውሎስ ራሱን ሐዋርያ በማለት ይጠራል ። ሐዋርያ ማለት በሥልጣን የተላከ ማለት ነው ። ራሱን የቀባና የላከ ሳይሆን በእግዚአብሔር ተጠርቶ የተላከ ማለት ነው ። በዚህ ዘመን ሐዋርያዊ ሥራ አለ ። የሐዋርያትንም መንበር ጳጳሳትና ቀሳውስት ተረክበዋል ። ሐዋርያ የሚል ሹመት ግን የለም ። ሐዋርያ ለመባል ጌታን ፊት ለፊት ማየትና በቀጥታ ከእርሱ መላክ ያስፈልጋል ። /የሐዋ. 1፡21-26/ በኤፌሶን መልእክቱ ቅዱስ ጳውሎስ፡- በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል፥ የማዕዘኑም ራስ ድንጋይ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው” ይላል ። /ኤፌ. 2፡20 ።/ ሐዋርያት የመሠረት አገልግሎት አገልግለዋል ። ሕንጸቱ ግን በወንጌላውያን ማጽናናት ፣ በአስተማሪዎች ማጽናት ፣ በእረኞች ስምሪት ይቀጥላል ። /ኤፌ. 4፡11 ።/
ሐዋርያው ጳውሎስ ለአሕዛብ የተሾመ አገልጋይ ነው ። አሕዛብ በጣዖት ፣ በሥርዓት የለሽነት መደዴ ሁነው የኖሩ ናቸው ። ጳውሎስን የሚያህል ረቢ ፣ በአይሁድ ባሕል የኖረ ሰው ፣ ፈሪሳዊ የነበረ ወግ አጥባቂ ከአሕዛብ ጋር ሲውልና ሲያስተምር ሕይወቱ በፍጹም ፍቅር እንደተለወጠ እንረዳለን ። የማይወዱትን ሰው ከመስበክ ዝም ማለት ይሻላል ። ቅዱስ ጴጥሮስ የአይሁድ መምህር ፣ ቅዱስ ጳውሎስ የአሕዛብ መምህር ነው ። የብሉይ ኪዳን እውቀት በጥልቀት የነበረው ሐዋርያው ጳውሎስ ነው ። መዳቢዎቹ እኛ ብንሆን ጳውሎስን መምህረ አይሁድ ፣ ጴጥሮስን መምህረ አሕዛብ እናደርግ ነበር ። እግዚአብሔር አይሳሳትም ።
ሐዋርያው በእውነት ያለ ሐሰት የአሕዛብ አስተማሪ ነኝ ማለቱ ለእናንተ የተላክሁ በረከት ነኝ ተቀበሉኝ ፣ አዳምጡኝ ማለቱ ነው ። እኛስ የተላክነው ለማን መሆኑን አውቀን ይሆን ? ሰው ያለ ቦታው ትርፍ ፣ በቦታው ግን ዋና ነው ።
1ጢሞቴዎስ 28
ታህሣሥ 27 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲ.አ.መ.
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ