የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ወደምንኖርባት ከተማ

በሁከት ውስጥ ጸጥታ ፣ በጦርነት ውስጥ ሰላም ፣ በመክነፍ ውስጥ ጽሞና ፣ በሽብር ውስጥ መረጋጋት ፣ በድንጋጤ ውስጥ ብርታት ፣ በኀዘን ውስጥ ደስታ ፣ በጥዝጣዜ ውስጥ ዕረፍት ፣ በኑሮ ውስጥ ክብረት ፣ በሞት ውስጥ ሕይወት የምትሰጥ የዓለሙ ፈጣሪ ፣ የዘላለሙ ቅዱስ አንተ ነህ ። ሁሉን አውቃለሁ የሚል ትውልድ ፣ ሁሉም የእኔ ነው የሚል ወገን ፣ ሁሉ ሞቶ እኔ ልኑር የሚል ሕዝብ ፣ ሁሉም ከንቱ ነው ከእኔ ውጭ የሚል ፖለቲከኛ ፣ ሁሉም ፈሪ ነው የሚል የተደበቀ አዋጊ በበዛበት ዘመን ፤ እኛ ስንናገር ያንተን ድምፅ መስማት አቅቶን  ፣ የራሳችንን መንገድ ስንከተል ካንተ መንገድ ወጥተን አንተ ግን በትዕግሥት ታየናለህ ። የሚያስጨንቀው እያሳቀን ፣ ባልበደልነው መናዘዝ ሲያምረን ፣ ግብዝነት መሬት ጥሎን ስንንፈራፈር ፣ ለእግዚአብሔር ነገ ለገንዘብ አሁን ስንል ፣ የሰማነውን መቋቋም አቅቶን ሌላ ለመስማት ስንፋጠን ፣ ከዓይናችን መጠን በላይ አይተን ሌላ ለማየት ስንንቀዠቀዥ እያየኸን ዝም ብለሃል ። ጌታ ሆይ ወደ ልባችን ስንመለስ ሰላም እንልሃለን ።
ሽማግሌዎች ብላቴና ለመሆን ሲያምራቸው ፣ ወጣቶች የቤትህን ትቢያ ሲልሱ ፣ ሕፃናት ያወቁ መስሎአቸው ሁሉንም ሲታዘቡ ፣ የሙት ልጆች እያሉ ሌላ ትውልድ ሲያምረን ፣ የጠራነውን ሳናስተዳድር ሌላ ሲናፍቀን አንተ ታየናለህ ። እንቢ ስንልህ ዛሬም ትጠብቀናለህ ። የወሬ ነፋስ ቤታችንን ሲነቅለው ፣ የሐሜት ማዕበል አገራችንን ሲያፈርሰው ፣ መለያየት ቤተ ክርስቲያንን ሲያሳንሳት እያየህ ነው ። ለፍላጎታችን አትተወን ። ጥንስሱ እንዲህ ያሰከረን መጠጡ እንዴት ሊያደርገን ነው ? እባክህ መልሰን ። የተቀበለንን ወዳጅ ስንገፋ ፣ አገር ያላመደንን አገር ስናሳጣ ፣ የፈረደልን ላይ ስንፈርድበት ፣ የሸፈነንን ስንገልጥ ፣ የሾመንን አርባ ስንገርፍ እያየኸን ነው ። ጠላትን አይደለም ወዳጅን መውደድ አቅቶን ፣ ወርቅ ላበደረን ጠጠር እየመለስን ነው ። አዎ እያየኸን ነው ። የምንሠራውን እናውቀው ዘንድ እርዳን ።
ለነቢያት የትንቢትን መንፈስ የሰጠህ ፣ በመምጣትህ ዜና ሕዝብህን ያረጋጋህ ዛሬም እመጣለሁ ብለህ አረጋጋን ። ያንተ መልእክተኞች እያነሱ ሰው ሠራሽ ሰባክያን እየበዙ እንዳይመጡ እባክህ እርዳን ። ሁሉም ነገር ጥያቄ ሲሆንብን የሁሉም ነገር መልስ እኔ ነኝ በለን ። ድምፅህን ነፍሳችን ታውቀዋለች ። በልብ ስትናገራት ትሰማሃለች ። ማዕበሉን ስትገሥጽ ማዕበሉም ላንተ ቃል ጆሮ አለው ። ነፋሳት የሚገዙልህ የሚናወጠውን መርከብ ጸጥ አድርገው ። ነገሬ አይሰማም ፣ ቃሌ ክብር አላገኘም ለሚለው ወዳንተ ቢጸልይ እንደምትሰማው አሳውቀው ። ወደማይሰሙን የጮህንበት ዘመን ያብቃና ወደምትሰማን መጸለይ ይሁንልን ። ወደማይሰሙን ነገሥታትና አለቆች የጮህንበት ዘመን ይብቃና ወደ ዘላለሙ ንጉሥ መጮህን አስተምረን ። የክለሳ ኑሮ ሲያደክመን ፣ የረገጥነውን መልሰን ስንረግጥ ፣ የበረሃ አዙሪት ሲገጥመን ፣ የተፋነውን ዳግም ስንልስ እባክህ መንገዱን አሳየን ። ወደምንኖርባት ከተማ በሰላም ፣ በቶሎ አድርሰን ።
ብዙ ዘርቶ ጥቂት አለማጨድ ፣ ብዙ ወድዶ ምንም አለመወደድ ፣ ብዙ ሠርቶ ትንሽ አለመመስገን ፣ ብዙ ሰጥቶ ብዙ መሰደብ የገረመው ትውልድ አለና ሰው አደባባዩን ሲያይ አንተ ግን ወደ ጓዳዎች ተመልከት ። አዋቂና ሰላምን ሰደን ከማሳደድ እባክህ ጠብቀን ። ስምህ ቡሩክ ይሁን ፣ የማይጠገብ ዝማሬ ለውለታህ ይቅረብ ። ለዘላለሙ አሜን ።
የነግህ ምስጋና /6
የካቲት 21 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ