የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ወዳጄ ሆይ /18

ወዳጄ ሆይ
ፈገግታ የነፍስ ስጦታ ነው ። ፈገግታ በብርሃን ላይ የሚታይ ብርሃን ነው ። ፈገግታ ካማሩ ሳሎኖች ይልቅ እንግዳ ተቀባይ ነው ። ፈገግታ የእኔ ሀብት ሰው ነው ብሎ ማመን ነው ። ፈገግታ ለቀጣይ ግንኙነት በር መክፈቻ ነው ።ፈገግታ ወደ ሌላው ሰው የሚጋባ ደስታ ነው ። ፈገግታ ትልቁና የመጀመሪያው ግብዣ ነው ። ፈገግታ እንኳን ሰው እንስሳም የሚሰማው ቋንቋ ነው ። ፈገግታ ልብን ለደስታ የሚያነቃቃ ዜማ ነው ። ፈገግታ ብርሃን ለብሶ መታየት ነው ። ፈገግታ በትንሹ የፊት ሜዳ ላይ ቢገለጥም መላውን ዓለም የሚወርስ ነው ። ፈገግታ ያለ ችግር የመኖር ምልክት ሳይሆን ከችግር ፍቅር ይበልጣል የሚል መልእክት ነው ። ፈገግታ ለቆዳ ጤንነትና መነቃቃት ትልቅ ስፖርት ነው ። እባክህ ምንጊዜም ፈገግ በል ። ሁሉም ነገር ፈገግ ይልልሃል ።
ወዳጄ ሆይ
ያንተን ድርሻ በቅጡ ከተወጣህ ዓለም ድኗል ማለት ነው ። እንደ ሕፃን አጠገብ ያለውን እያየህ ሥራህን አትሥራ ። ያለችግር ካለህ መፍዘዝ ትጀምራለህ ፤ ተግዳሮትም መነቃቃትና እልኸኛ ያደርግሃል ። አዝነው ወዳንተ የመጡትን በንጹሕ ፍቅር ተቀበላቸው ፣ ሊነግሩህ የፈለጉትን ችግር ንቀውት ይተውታል ። መድኃኒት ላላቸውና ለሌላቸው በሽታዎች ትልቁ ፈውስ ፍቅር ነው ። ፍቅር ከተራራው በላይ ያራምዳል ። የአቅምህን ያህል ተራመድ እንጂ መንገድን ሁሉ እጨርሳለሁ ብለህ አታስብ ።
ወዳጄ ሆይ
በትንሽ ምክር የሚያረጋጋህ የእግዚአብሔር መንፈስ ዛሬም ካንተ ጋር ነው። ደፋር ኃጢአተኞች ፣ በፈሪ ኃጢአተኞች ፊት እንደ ጻድቃን ይንጎማለላሉ ። ያላየኸው ብዙ መልካም ነገር ከቦሃልና ጌታ ሆይ ዓይኔን ክፈት በለው ። የአልማዝ ጉድጓድ ላይ ተቀምጠው ስለተራቡ ሰዎች ብዙ ኀዘን ተሰምቷል ፤ ከዚያ ይልቅ በጸሎት የማይጠቀም ክርስቲያን ምስኪን ነው ።
ወዳጄ ሆይ
ብርሃን እንጂ ጨለማ ጥላ የለውም ፣ የሚከተልህን ጉድለት ያወቅኸውም በሌላ ሙላት ውስጥ ስላለህ ነህ ። ፍጹም ባዶ ሰው ፣ ፍጹምም ሙሉ ሰው የለም ።ከተሰበረ እጅ ይልቅ የማይሰጥ እጅ የተጎዳ ነው ። እጅ የተፈጠረው ለመቀበል ብቻ ሳይሆን ለመስጠትም ነው ። የማይሰጥ ድሀ የለም ፣ የማይቀበልም ባለጠጋ የለም ። በልብህ ውስጥ ያለውን በሙሉ ከተናገርህ ልብህ ልብ መሆኑ ቀረ ማለት ነው ። የተሰማህን ሳይሆን ያመንህበትን ኑር ። ዛሬ እየቻልህ ነገ አደርገዋለሁ የምትለውን ነገም አታደርገውም ፣ ምክንያቱም ነገ የዛሬ ውጤት ነውና ። ከሌላ የሚመጣውን ሳይሆን ካንተ የሚወጣውን ክፋት ተጠንቀቅ ።
ወዳጄ ሆይ
ሥሩ የበሰበሰ ዛፍን ከመውደቅ የሚያድነው የለም ። አስተሳሰቡ የተበከለም መጨረሻው አሳዛኝ ነው ። መለወጥ የሌለበት ጸጸት ጭቃ ላይ ተቀምጦ መታጠብ ነው ። ደስታን ስትከተል ይርቅሃል ፣ እግዚአብሔርን ስትከተል ደስታ አንተን ይከተልሃል ። ሰዎች ችግራቸውን የሚነግሩህ እንድትፈጽምላቸው ሳይሆን በአብዛኛው እንድታዳምጣቸው ነው ። በሕይወትህ ትልቅ ባለውለታዎችህ የገፉህ ሰዎች ናቸው ፣ ባትገፋ ኑሮ ይህ እውቀትና ኑሮ አይኖርህም ነበር ። መውደድህንና ምስጋናህን ቀጠሮ አትስጠው ፤ የምትወደውና የምታመሰግነው ሰው ያለው ቀን ዛሬ ብቻ ሊሆን ይችላልና ። ሥልጣን ካላዘዙበት የደነዘ ቢላዋ ነው ። ሥልጣን ካላዘዙበት ባለሥልጣኑን መቃብር የሚከትት ነው ። እሺ ካሉህ ይልቅ በጊዜው እንቢ ያሉህ ትልቅ ሰዎች ናቸው ። አንድ ካላልህ ሁለት አትልም ። ምቹ ጊዜ የምትጠብቅ ከሆነ ምንም አትሠራም ፣ ምቹ ጊዜ የመሥራት ውጤት ነውና ።
በደስታ ዋል !!!
ምክር 18
ዲአመ ሚያዝያ 15 ቀን 2011 ዓ.ም.
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ