ቁመህ ስትሄድ የተቀመጡ ሰዎች ይተቹሃል ። የማይሠሩ እጆች ያሏቸው የሚሠሩ አፎች አሏቸው ። የሚሮጥ መስመሩን ያያል ፣ የተቀመጠ ዙሪያውን ያማትራል ። አንድ ብቻዬን ነኝ ምን ይመጣብኛል አትበል ፤ መከራ የመጣ ቀን አንድ ራስህ ከሚሊየን በላይ ያስጨንቅሃል ። ጠቃሚዎችህን ስታመሰግን ያልጠቀሙህ የመሰሉህን አትርገም ። ለሺህዎች እየተናገርህ ለአንድ ሰው መልእክት አታስተላልፍ ፣ አሽሙር የሚባለው ይህ ነውና ። አሽሙር ለማይሰማ ሰው የሚሰሙትን ልቦች ማደፍረስ ነው ። ያልመሰለህ ነገር ያልሆነ ነገር አይደለም ፣ ድርጊትን በስሜትህ አትለካው ። ዋሽተህ ከመከበብ እውነት ተናግረህ በዱር ማደር ይሻላል ። በዓለም ላይ ትልቁ ቅዠት ዓለምን የግልህ ለማድረግ ያሰብህ ቀን ነው ። ትልቅ መሳሳት ሁሉ ይወደኛል ብሎ ማሰብ ነው ። ትልቅ ድፍረት ሁሉን አውቃለሁ ብሎ መፎከር ነው ። ትልቅ ውድቀት አዋቂን ትቶ ከቢጤ መምከር ነው ።
ወዳጄ ሆይ
ጽጌረዳ ከእርሷ የሚበልጡ እሾሆች አሉባት ፣ አንተም ጠላቶቼ በዙ ብለህ አትደንግጥ ። ብርቱካን ጣፋጭ ነው ፣ ቆዳው ግን መራራ ነው ፣ የምትወዳቸው ሰዎችም በአስቸጋሪ ሰዎች መካከል ይኖራሉ ። አንድ ነገርን በሚያስገኘው ጥቅም ከለካኸው ነጋዴ ነህ ፣ በሚያመጣው ዝና ከተመንከው ቲያትረኛ ነህ ። አስመሳዮች የውሸት አልቅሰው የእውነት የሚያስለቅሱ ናቸው ።
ወዳጄ ሆይ
ሰዎች የሚወዱህ ስለወደድሃቸው ነው ፤ የሚርዱልህ ግን ስላስደነበርካቸው ነው ። የሥጋ በሽታ ፈውስን ሲፈልግ የነፍስ በሽታ ግን የበለጠ በሽታ ላይ ይውላል ። ማብረጃው የማይሠራ መኪና የሚያምርበት ሲሄድ ሳይሆን ሲቆም ነው ። ለስልሶ መናደፍ እባብነት ነው ። ሁለንተናው የማይመች ሰው ጊንጥ ነው ። ሁሉ በሽተኛ ከሆነ ሐኪም ፣ ሁሉ ተናጋሪ ከሆነ አድማጭ ፣ ሁሉ ዘማች ከሆነ አዝማች ፣ ሁሉ መሪ ከሆነ ተመሪ ሊጠፋ ነው ። የትላንት ሕመም ዛሬ ላይ እንዳይደገም ጥንቃቄ ጠባቂ ነው ። ማመስገን ባለ ዕዳነትን ማውረድ ነው ። የታሠረ ሰው ሲሄድ የሚደርስ ይመስለዋል ። ፍቅርን ወደ ኋላ የጣለና የገፋ ወደፊት አያገኘውም ። መገኘት ማለት መኖር አይደለም ፣ ድንጋይ ዕድሜው ከእኛ ቢበልጥም እየኖረ አይደለም ። ሰውን ስለ ልብሱ እንጂ ስለ ልቡ አስተያየት አትስጥ ፤ ልቡን የሚያውቀው እግዚአብሔር ነውና።
ወዳጄ ሆይ
ቃል የሰበረውን መረቅ አይጠግነውም ፤ እጅ የሰበረውን ግን ቃል ይጠግነዋል ። ሰዎች እንዲያውቁህ የምታደርገው ጥረት ባለማወቅ ይደመደማል ። ደም ስታፈስ የልጅ ልጆችህ የሚከፍሉትን ዕዳ ታኖራለህ ። እውቀትን እንጂ ደምን የሚያወርስ ባይወልድ ይሻለዋል ። እንባ አምላክ እንዳለው አትርሳ ። እንባ ሲወርድ ውኃ ፣ ሲመለስ እሳት ነው ፤ እንባ ሲወርድ ይበርዳል ፣ ያረፈበትን ግን ያቃጥለዋልና ሰዎች እንዳያለቅሱብህ ፍራ ።
ወዳጄ ሆይ
የቀኑ ትኩሳት ለፍላፊ አያድርግህ ፣ “ጊዜ የሰጠው ዘፈን እንቅርት ያፈርጣል” የተባለውን አትርሳ ። ኃጢአቴ በዛ ፣ ጽድቄ አነሰ የሚል ጠፍቶ ጽድቄ በዛ ፣ ኃጢአቴ አነሰ የሚል ትውልድ ምንነቱ ባልታወቀ ደዌ ይማስናል ። የሌላውን ቤት የሚያፈርስ የእርሱ ቤት ነገ እንዲፈርስ ሰይፍ ያቀብላል ። ባለቀው ነገር አትዘን እርሱን ለመጨረስ ዕድሜ የሰጠህን ጌታ አመስግን ። ጭር ባለው መንገድ መሄድ ስትፈራ የሚርመሰመሰው ሰውም ጠቃሚህ እንደሆነ ተረዳ ። ሰይፍ በሰገባው ይያዛል ፣ እግዚአብሔር በሰጠው ኪዳን ይለመናል ።
ምክር /24
ጥቅምት 22 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲአመ