የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ወዳጄ ሆይ

መጮህ ሳይያዙ ነው ፣ ከተያዙ በኋላ መጮህ ቀባሪ ለመፈለግ ነው ። ዛሬ ስለ እውነትና ስለ ፍቅር ካልጮህን ነገ እየሞትን እንጮኻለን ። ደካሞችን ለማጥቃት ብርቱ አትሁን ። የሚያንሰውን ረግጦ ጀግና የተባለ ማንም የለም ። እሳት ቆስቋሹን ፣ ወሬም አራጋቢውን ይፈልጋል ። የኑሮ ጥያቄ ሳይመለስ የመኖር ጥያቄ እንዳይመጣ ጸልይ ። ጠባይህ የሚከብደው እንጂ መኖርህ የሚከብደው ከጠላትም በላይ ነው ። አውሬ ከጠገበ አይገድልም ፣ ክፉዎች ግን የሰውን ሥጋ በልተው አይጠግቡም ። አውሬ የሚገድለው ሊበላ ነው ፣ ሰው ግን የማይበላውን ይገድላል ።

ወዳጄ ሆይ
ነቅተህ የምትሞቀው እሳት ስትተኛ ያቃጥልሃል ። ትላንት ለጆሮ የከበደህ ዛሬ ለዓይንህ ይቀልሃል ። ሲታሰብ ያልተገሠጸ ፣ ሲነገር ያልታረመ ክፉ ነገር ሲደረግ ይቀላል ። በዓለም ላይ ከባዱ ማድረግ ሳይሆን ማሰብ ነው ። ሰውን ሰው የሚያሰኘው እንዴት እኔ ይህን አስባለሁ ? ብሎ ክፋትን ሲጸየፍ ነው ።
ወዳጄ ሆይ
ዓለምን ገነትም ሲዖልም የሚያደርጋት የእኛው ምርጫ ነው ። ትዕግሥት ተስፋን ሲያሳጣ ትዕግሥት መሆኑ ይቀራል ። ፖለቲከኛ መሆን ማለት በዓይን እያለቀሱ በልብ መሳቅ ነው ። ቁልፍ በራሱ ላይ ሲቆልፍ በር ይሰበራል ፣ ወንድም ወንድሙን ሲገድል አገር ይደፈራል ። ያልበደለውን የገደለ የበደለውን ምን ሊያደርግ ነው ? እውነተኛ ዱርዬ ባለበት ዓለም እውነተኛ ጨዋ መጥፋቱ ፣ ክፋት የምትጓደደውን ያህል ደግነት መድረሻ ማጣቱ ያሳዝናል ። የፖለቲካ ጆሮ የተገጠመለት የሚሰማው የሚያስበውን ነው ። የሚጨሱ ነገሮች ማለቃቸው ፣ የሚያጨሱ ሰዎች ማልቀሳቸው አይቀርም ።
ወዳጄ ሆይ
በግድ የገባ ቤቱን ያፈርሳል ። ዝምታን የመረጠውን በግድ ተናገር ስትለው ያዋርድሃል ። አጥንት አጥንትን ይሰብራል ፣ በክፉ ቀንም ያሳደጉት ይገድላል  ። የሩቅ ጠላትን የሚገዛው የቅርብ ወዳጅ ነው ። ደግም መካሱ ክፉም ማልቀሱ አይቀርም ። ውስጥህ የሌለውን ለመሆን መሞከር ቲያትር ነው ። የተከፈተለት የሚዘጋ ፣ ይቅር የተባለ የሚበቀል ፣ የዳነ የሚገድል መሆን የለበትም ። እሳቱ መከራ ፣ ድስቱ ምድር ፣ የምትበስለው አንተ ነህ ። እሾህ ሲቃጠል እንጀራ ይጋግራል ፣ የሚያደሙ ሲቀጡ በረከት ይመጣል ።
ወዳጄ ሆይ
ፈረሱ ጠፍቶ ኮርቻን መፈለግ ከንቱ ነው ። ክብር ጠፍቶ በረከት መሻት ልፋት ነው ። ሰነፍ በጉልበቱ ለግሞ በአፉ ይሠራል ። ሥራውን የፈጸመ መኖርን ይጠግባል ። ያልደረስከው ልቅሶ ሁልጊዜ ትኩስ ነው ፣ ያልገለጥከው ኀዘንም ሲያቃጥልህ የሚኖር ነው ። ያልገዛኸው ስሜት ይገዛሃል ። የስሜት ሎሌ ጌታ ሳይሆን ይሞታል ። ተኝተህ ለሚያዙህ ቁመህ አትሙትላቸው ።  ሌቦች ሐቀኛ ለመምሰል የሚያጠልቁት ጭንብል መኮሳተር ነው ። መጎዳትህን ከሚነግርህ የሚረዳህ እርሱ ወዳጅህ ነው ።
ወዳጄ ሆይ
የሚያውቅህ ሲደፍርህ የማያውቅህ ያከብርሃል ። ዓለም ስድብ ላይ በነበረችበት ዘመን ቤተ ክርስቲያን ጸሎት ላይ ነበረች ፤ ቤተ ክርስቲያን አውጋዥ ስትሆን ዓለም መግደል ላይ ደረሰች ። እኛ ስንደፍር ዓለሙ በእጥፍ ይደፍራል ። መጻሕፍት ሲቃጠሉ ቀጥሎ ሰው ይቃጠላል ። ወንጌል ካልተሰበከ ወንጀል ሥራ ይሆናል ። ወንዝ የሚወስደው ሰው የተዘረጋውን እጅ ሁሉ ይይዛል ፣ የተቸገረም ትውልድ አሳብ አይመርጥም ። በእግዚአብሔር ልብ ያለህን ስፍራ ስታውቅ የሰዎች ንቀት አያስፈራህም ። ገመናን መክደን የሚገባት አገር ስትገልጥ እየፈረሰች መሆኑን አስተውል ። እግዚአብሔር አንድ ነገር አያውቅም ፣ የፈጠረውን ትንሽ ሰው ።
ወዳጄ ሆይ
የናቁት ያስረግዛል ፣ ሞኝም ባናት ይመጣል ፣ ጨካኝም ካሰበው ይደርሳልና ማንንም አትናቅ ። ሲያገኝ የማያመሰግን ሲያጣ ለማማረር ሞራል የለውም ።መራብን እንደ ጠላኸው መጥገብንም ጥላው ። ለሰው ልጅ በሕይወቱም በሞቱም የሚሰጠው አበባ ነው ። ብዙ የሚሠራ እጅ ብዙ ያፈርሳልና እጅህን ቀድስ ።
ምክር /22/
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ