የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ወዳጄ ሆይ

ከሰው ላለመለየት ብለህ ግፍ አትሥራ ። ጊዜ ይልፋል ፣ ትዝብትና ጸጸት ግን ይኖራሉ ። ከሰው መለየትን የሚፈራ ከእግዚአብሔር መለየትን አለመፍራቱ ይገርማል ። ከሰዎች ጋር አብረህ ብትሮጥ በትግሉ ተስማምተህ ግቡ ላይ ትጣላለህ ። “ሌባ ሲሰርቅ ይስማማ ፣ ሲካፈል ይጣላ” እንዲሉ ። የሌሎችን ዝና ቀምተህ ዝነኛ ስትሆን ደቀ መዛሙርትህ ያንተን ዝና መንጠቅ እንዲችሉ ድፍረት እየሰጠሃቸው ነው ። መድረሻህን እግዚአብሔር ካላደረግህ የዚህ ዓለም መድረሻዎች ሁሉ ሲደርሱባቸው የማያሳርፉ ናቸው ።
ወዳጄ ሆይ
ሰዎች ያደረጉብህን ሳይሆን ያደረጉልህን ብቻ አስብ ። ሰዎች አንድ ጊዜ ይወጉሃል ፣ ራስህን በቂም የምትመርዘው ግን አንተ ነህ ። ሰዎች ገንዘብህን እንጂ ጊዜህን እንዲሰርቁብህ አትፍቀድላቸው ። ታውከህ ካልጠበቅኸው የሚያውክህ የለም ። ጠላትህን የገደልከው ዝም ያልከው ጊዜና የረሳኸው እንደሆነ ነው ። ከሰዎች ጋር ተጉዞ የጨረሰ የሚመስለው እንደገና መጀመሩ አይቀርም ። ያለ እግዚአብሔር ከሚኖሩ በእግዚአብሔር አምነው የሚሞቱ ይሻላሉ ። ሰማዕትነት በደጅህ ነውና ክርስቲያን ሆይ እርስ በርስህ አትባላ ።
ወዳጄ ሆይ
ካለህ ስጥ ፣ ከሌለህ አትሰጥምና ። ካለህ አታባክን ፣ ከሌለህ አታባክንምና   ። ካለህ ስጥ ፣ ሞተህ አትሰጥምና ። መድረሻህ ሲጠፋህ ወደ ተነሣህበት ተመለስ ። ፖለቲካ አምላክህ ከሆነ ዕድሜህ አጭር ነው ። እንስሳ ከቅጣቱ ይማራልና ከትላንት የማይማር እጅግ ደካማ ነው  ። የነገ ተስፋ የሌለው እምነቱን የጣለ ነው ። ፈጣሪህ አንተን አልካደህምና አንተ እንዳትክደው ተጠንቀቅ ። መጸጸት የሰው ልክ ነውና በክፉ ሥራህ ልበ ደንዳና አትሁን ። ጽድቅ አስበህ ኃጢአት ብትረግጥ እንደገና ሞክር ፤ ኃጢአት አስበህ ጽድቅ ላይ ራስህን ብታገኝ እንደ ጳውሎስ እግዚአብሔርን አመስግን ።
ወዳጄ ሆይ
እነዚያ ቀኖች ተመልሰው አይመጡምና የመጣውን ቀን በክፉ ትዝታ አትረብሸው ። ሲጸጸቱ መኖር የሰይጣን የዘፈን ባንድ መሆን ነው ። ካሰብህበት ባትደርስም እግዚአብሔር ካሰበልህ ደርሰሃልና ደስ ይበልህ ። አለመሆኑ ሳይሆን ለምን አለመሆኑ ሲረብሽህ ፤ አለመሆንም መሆን ነው ፣ ለምን አልሆነም ማለትም የማይፈታ ቅኔ ነው ።
ወዳጄ ሆይ
መሮጥ ካቃተህ በእውነት መንገድ ላይ ተራመድ ፤ መራመድ ካቃተህ ዳዴ በል ፣ ዳዴ ማለት ቢያቅትህ ተኛ ፤ ክርስቶስ በዚያ መንገድ ሲመጣ ተሸክሞህ ይሄዳል ። ከድንዛዜህ ንቃ ፣ ሞት ጦሩን ስሏልና ። ኃጢአት ሳታቆም መዓት እንዲቆም አትሻ ። አገር በኑዛዜ እንጂ በፖለቲካ ትንታኔ አትድንም ። ያንዣበበ መዓት በታላቅ ንስሐ ይመለሳል ። ሰዎች ያጎደሉትን ሳይሆን አንተ ልትሠራው ሲገባህ ያልሠራኸውን አስብ ።
ወዳጄ ሆይ
ጸሎት ከሌለበት ማሰብ ብቻውን ድንጋይ ከመፍለጥ በላይ ያደክማል ። እውነት ከሌለበት ብዙ ማውራት ያስንቃል ። ፍቅር ከሌለበት ተግባር ከንቱ ልፋት ነው ።
ወዳጄ ሆይ
ነገር እያሰብህ አትተኛ ፣ እሾህ ከሥርህ ማንጠፍ ነውና ። ነገር እያሰብህ መንገድ አትሂድ ፣ ከቆመ ነገር ጋር ትጋጫለህና ። ነገር እያሰብህ አትብላ ፣ በትንታ ትሞታለህና ። ነገር እያሰብህ አትናገር ፣ መራራ ትሆናለህና ። ነገር እያሰብህ ወዳጅህን አታዋራ ፣ ገጽህ ይለወጣልና ። ነገር እያሰብህ አታቅድ ፣ ግብህ ይከፋልና ። ሁሉን ለእግዚአብሔር ተውለት ። እርሱን አልፎ የሚነካህ የለምና ።
ወዳጄ ሆይ
የጀመርከው ቢበላሽም እንደገና ጀምር ። ሁልጊዜ ዝራ የትኛው እንደሚበቅል አታውቅምና ። ትላንት የዘራኸውን ዛሬ እየበላህ ነው ፤ ዛሬ የምትዘራውንም በጎ ነገር ነገ ትበላዋለህ ። ያልዘራ የሚያጭደው የለም ።
ደስ ብሎህ ዋል  
ምክር/ 21
ጥቅምት 13 ቀን 2012 ዓ.ም.
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ