የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ወዳጄ ሆይ

ወዳጄ ሆይ
መሥራት ቢያቅትህ የሚሠሩትን አትበጥብጥ ። ማፍቀር ቢያቅትህ የሚያፈቅሩህን አትናቅ ። ማመን ቢያቅትህ የሚያምኑትን አትስደብ ። መኖር ቢያቅትህ መልካሙን የመረጡትን አትንቀፍ ። ማግባት ቢያቅትህ ያገቡትን አትተች ። መመንኮስ ቢያቅትህ የመነኮሱትን አታውግዝ ። መጻፍ ቢያቅትህ የሚጽፉትን አታቃልል ። የማይሠራ የሚሠራን ፣ ያልተማረ የተማረን ፣ ያላመነ የሚያምንን ፣ የማይጽፍ እጅ የሚጽፍ እጅን እንዴት ይተቻል ?
ወዳጄ ሆይ
የምትሰማውን ደግና ክፉ ውስጥህ ለመሆን ሲፈልግ በጸሎት አርቀው ። አደርግልሃለሁ ያለህ ባያደርግልህ ምናልባት አልቻለምና ስለ አሳቡ አመስግነው ። በበላይህ የነበረ የበታችህ ሲሆን ላንተ ማስተማሪያ ነውና በትሕትና እንደ ቀድሞው አገልግለው ። መሆን መሞከርን ደግሞም ማስመሰልን የሚያርቅ ቀላል የኑሮ ዘዴ ነው ። በነጻ ማፍቀር ካልቻልህ ጥቅመኛ ነህ ማለት ነው ። ቀን ሁልጊዜ ቀን አይሆንምና ለሌሊቱም ክፍለ ጊዜ ተዘጋጅ ። በብርሃን ለጨለማ ፣ በጨለማም ለብርሃን ተሰናዳ ፤ ሁሉም ነገር ይለወጣልና ። ሰዎች ሁሉ ይወዱኛል ከማለት እወዳቸዋለሁ ማለት የተሻለ ነው ። አድርገህላቸው የሚጎዱህ ፣ አጉርሰሃቸው የሚነክሱህ ከመጡ እግዚአብሔር ዋጋህን ሊከፍል ነውና ደስ ይበልህ ።
ወዳጄ ሆይ
ልብህ እየሸፈተ ከጸሎት መስክ ሲወጣብህ ጸሎትህን በዜማ አድርገው ። ሥጋህ መረን ወጥቶ እንዳይገለብጥህ ኑሮህን መጠነኛ አድርገው ። ጾም የትሕትና መሠረት ፣ የእንባም እናት ናትና ውደዳት ። እውነተኛ ኀዘን ጥቁር ልብስ መልበስ ሳይሆን ለቀረው ወገንህ መልካም ማድረግ ነው ። ወታደርም ልብሱን ሲያወልቅ እንደ አንተው ዜጋ ነውና አትፍራው ። ብዙ ሁነህ ስትሰበሰብ የእኔ ፍላጎት ብቻ ካልሆነ አትበል ። ፍላጎቱን ያልገደለ ኅብረትን ያፈርሳል ። በልጅህ ፊት ሚስትህን አትንቀፍ ። በሠራተኞችህ ፊትም ወዳጅህን አትገሥጽ ። ሚስትህን ለመምታት እጅህ ሲፈተን እየሳትህ ነውና የሥነ ልቡና አማካሪዎችን ፈጥነህ አግኝ ። አደርጋለሁ ብለህ ቃል የገባኸውን አድርግ ። ቃል እግዚአብሔር ወልድ የሚጠራበት የኩነት ስሙ ነውና ቃል ከባድ ነው ። ካልተቸገርህ በቀር የስለላ ሠራተኛ አትሁን ። አገርህን ለመጠበቅ ግን ራስህን እንደ ዘብ ቊጠር ።
ወዳጄ ሆይ
ክፉ አሳብ ሲዋጋህ ያንን ለመርሳት አትታገል ፤ አሳብ የሚሸነፈው በአሳብ ነውና ስለ እግዚአብሔር ማሰብ ጀምር ፤ መጻሕፍትንም አንብብ ። ያዘዝከውን ሰዎች ባይፈጽሙ አቅም አንሷቸው ሊሆን ይችላልና ራስህ ፈጽመው ወይም ለሚሠራ ለሌላ ሰው ስጠው ። መንደሮች የሚያስቡት በመንደራቸው መጠን ነውና ከመንደር ይልቅ ልብህን አስፋው ። አቅምህ እንጂ እምነትህ አናሳ አይሁን ። ኑሮህ እንጂ ፍቅርህ ድሀ አይሁን ። በእጅህ የወደቀ ምርኮኛህ ነውና አቅም አለኝ ብለህ ምንም አታድርግበት ። ተቀምጠህ የምታየውና ቆመህ የምታየው ልዩነት አለው ። ስትቀመጥ ትልቅ የመሰለህ ስትነሣ ትንሽ ነው ። አንድ እርምጃ መራመድም ወደ ግቡ መቃረብ ነው ። እውነተኛ አጥር የሰው ፍቅር ነውና ከአጥር ይልቅ ፍቅርን ገንባ ።
ወዳጄ ሆይ
በዙሪያህ ስላሉት አታስብ ፣ በልብህ ያለውን እምነት ግን አሳድግ ። የምትወድቀው ዙሪያው ደግፎህ ልብህ ሲከዳህ ነው ። ልብህ ከልቡ ጋር ሳይሆን ልብህ ከእግዚአብሔር ጋር ይምከር ። ስምህን ጠርተው ሰላም የሚሉህን ስማቸውን ጠርተህ ሰላም በል ። ከሰዎች ጋር እውነተኛ ግንኙነት ለማድረግ ስማቸውን ከመያዝ የበለጠ መነሻ የለም ። የፈለግኸውን ሳይሆን የሚያስፈልግህን እንዲሰጥህ እግዚአብሔርን ለመን ። እርሱ ሰጥቶ የማይሰለች አምላክ ነው ። ነፋስን ከናቅኸው ዐውሎ ነፋስ ሁኖ ይመጣል ፣ አስቸጋሪ ሰውን በጊዜ ካልገደብከው ፈቃድ ያለው ይመስለዋል ። አለቃ ለመሆን ስታስብ በጨለማ ወጥተህ በጨለማ ለመግባት መወሰን አለብህ ። ከሠራተኛው በፊት የማይገባ ፣ ከሠራተኛው በኋላ የማይወጣ አለቃነት አይኖርም ። ታዝዞ እንደ መኖር ያለ በረከት የለም ።
በብርሃን ዋል !!!
ምክር 17
ዲአመ ሚያዝያ 14 ቀን 2011 ዓ.ም.
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ