የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ዋጋ መስጠት

 

የሰውን ልብ ብሩህ የሚያደርጉ አራት ነገሮች አሉ ይባላል ። የመጀመሪያው ግን ብሩህ ፊት ነው ። ብሩህ ፊት የሚያሳዩን ልባችንን ያበሩልናል ። ፀሐይ የማይደርስበትን ፣ አምፑል የማይሰካበትን ልባችንን የሚያበሩ ብርሃናዊ ፊት የሚያሳዩን ናቸው ። ብሩህ ገጽ ለሚያሳዩን ሰዎች ዋጋ መስጠት አለብን ። ትንሽ የሚመስለውን ነገር ካላከበርን ትልቁ አይሰጠንም ። “ከፍትፍቱ ፊቱ” ይባላል ። ደግሞም ፊት የልብ አደባባይ ነው ። ልባቸውን በፊታቸው ላይ ስላሳዩን ሰዎች ለእግዚአብሔር ምስጋና ማቅረብ አለብን ። ችግራቸውን በፊታቸው አደባባይ ሳያሳዩ በጥንካሬ አሸንፈው ብሩህ ፊት የሚያሳዩን የጽናት አስተማሪዎቻችን ናቸው ። ደስታ ገጠመኝ ሳይሆን ምርጫ ነው ። የእግዚአብሔርን ደስታ ሌባ እንደማይሰርቀው እነዚህ ሰዎች ምስክሮች ናቸው ። አራዊት ፊታቸው አይፈታም ፣ እንስሳት ገራምነት ይታይባቸዋል ፣ ሰዎች ፈግግ ይላሉ ። ብሩህ ፊት የሰውነት መለኪያ ነው ። ባለሥልጣን ብሩህ ፊት ሲያሳይ ሕዝቡን ያሳርፋል ፣ ሐኪም ታካሚውን ይፈውሰዋል ። የትኛውም ችሎታ ቢኖረን የሰውን ስሜቱን ገድለን ሥጋውን እንጠግን ይሆናል ። አሊያም በስሜት እየገደልን በአካል ለመጠገን መሞከር ከንቱ ድካም ነው ። 

ብሩህ ፊት ከምክንያት በላይ ነው ። አንተን ወንድሜን ፣ አንቺን እኅቴን ከማግኘት በላይ ትርፍ የለኝም ብሎ ማመን ነው ። በምንሸጥበት አገር የሚገዙን ብሩህ ፊት የሚያሳዩን ናቸው ። ስሜታችን ማንም የላችሁም እያለን ሰው እንዳለን የሚነግሩን ብሩህ ፊት የሚያሳዩን ናቸው ። የሚስቅልን ፣ ፈገግ የሚልልንም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው ። እግዚአብሔር ከሚሰጥን ትልቅ በረከት ብሩህ ፊቱ ነው ። ትልቁ ቡራኬ እንዲህ ይላል፡- “እግዚአብሔር ፊቱን ያብራልህ” ዘኁ. 6፡24 ።

ፀሐይ ወጥታ የሚጨልምብን ክፉ ፊት ስናይ ነው ። በክፉ ሰዎች እየተማረርን ደጎቹን መያዝ አለመቻል በራስ ላይ ክፉ ሠራዊት መጋበዝ ነው ። ብሩህ ፊት የሚያሳዩን ቀናችንን ያበሩልናል ፤ ፀሐይ የማትደርስበትን ውስጠኛውን ልባችንን ያሞቁልናል ። ብሩህ ፊት የሚያሳዩን የቀኙን መንገድ ያመለክቱናል ። ፊት የልብ እንደራሴ/አምባሳደር ነው ። ብሩህ ፊት የሚያሳዩን የደስታዬ ምንጭ አንተ ነህ ማለታቸው ነው ። መኖርህ ለእኔ ዋጋ አለው እያሉን ነው ። ዕድሜ ቀጥል ሐሴቶቻችን ናቸው ። በሰማይ ፀሐይ የለችም ፣ ሌሊትና ቀን የሚያበራው የታረደው በግ ክርስቶስ ነው ። የሚያበራው በዘላለም ፍቅሩ ነው ። ብሩህ ፊት የዘላላም ብርሃን ምሳሌ ነው ። ክርስቶስን ወክለን የምንኖር ነን ካልን ብሩህ ፊት ለማሳየት ነው ። 

እኛን ሲያዩን ፊታቸውን የሚያዞሩ ፣ ጋሪ ተከራይተው ተሸፋፍነው የሚያልፉ ፣ ያልተደወለ ስልካቸውን አንሥተው ጆሮአቸው ላይ የሚሰኩ ፣ ዓይተው እንዳላየ የሚሆኑ ፣ እንደ ኮሶ መራራ የሆነ ገጽ የሚያሳዩን ባሉበት ዓለም ላይ ብሩህ ፊት ለሚያሳዩን ዋጋ መስጠት አለብን ። ከመቃብር በላይ በመዋላችን የሚደሰቱ ካሉ ብሩህ ፊት የሚያሳዩን ናቸው ። በእውነተኛ ፍቅር ላይ የተመሠረተ ብሩህ ፊት ኃይል አለው ፣ የሞተን ልብ ማሥነሣት ይችላል ። ተአምር ማድረግ የምንፈልግ ከሆነ ፍቅርን በመስጠት ሙት ማንሣት የሚያስችል ተአምር አሁን አለ ። ኀዘናችንን የሚወስዱልን ፣ ከሁኔታ በላይ የመደሰት መብታችንን የሚጠቁምን ብሩህ ፊት የሚያሳዩን ናቸው ። ፊት ይናገራል ፣ ፊት ሳሎን ባይኖረንም እንግዳን የምንቀበልበት ትልቅ ሳሎን ነው ። 

ብሩህ ፊት ለሚያሳዩን ዋጋ እንስጥ ። ብሩህ ፊት ያሳያችሁኝ እንዳበራችሁ ኑሩ ፣ ፀሐያችሁ አይጥለቅ !

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን 

ሐምሌ 24 ቀን 2013 ዓ.ም.

እውነት 4

ለልባችሁ የቀረላችሁን አሳብ እስቲ ግለጡ ። እግዚአብሔር ፊቱን ያብራላችሁ !

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ