የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ውስጣዊ ቍጣ / ክፍል 5

“የሰው ቍጣ የእግዚአብሔርን ጽድቅ አይሠራምና።” ያዕ. 1፡20።

5- የደከሙለትን ሕዝብ መክሰር

“እኔ የጥቂት ሰው አይደለሁም ፣ የእኔ ሚሊየኖች ነኝ ፣ እኔ የሕዝብ ልጅ ነኝ ፤ እኔ ልኬ ቤት ሳይሆን አገር ነው” ብለው የሚያስቡ ሰዎች አሉ ። መሪነት ተፈጥሮ ነው ወይስ ጥሪ ነው ካልን ጥሪና ተፈጥሮ ሁለቱም አንድ ናቸው ። እግዚአብሔር በተፈጥሮ ሰውን ጠርቶታል ፣ የመሪነት ጥሪም በተፈጥሮ ይሰጣል ። እግዚአብሔር ድምፁን በማሰማት ያንን ጥሪ ያጸናዋል ። በዚህ የተፈጥሮ ጥሪ ውስጥ ሰው መሆን ይቀድማል ፣ መሪነትም ይከተላል ። ሙሴን ያየን እንደሆነ እናቱ ከጡት ጋር የአገርና የወገን ፍቅርን ሞልታበታለች ። ሰውን ለማስተማር አትሮኖስ ብቸኛው መድረክ አይደለም ፣ እቅፍም ከፑልፒት በላይ ሰውን መሥሪያ ነው ። ትምህርት ግን ከጡት ጋር እኩል ሊሰጥ የሚገባው ነው ። አገር ማለት ሕዝብ ነው ። እስራኤል አገር አልባ ቢሆኑም ለእስራኤል ያለው ፍቅር የአገር ፍቅር ነበረ ። ሙሴ ለዚያ ሕዝብ የኖረው የሚሸጥ መሬት ፣ የሚወዳጅበት ወርቅ ስላለው ሳይሆን ያ ወገን በእግዚአብሔር የተጠራ ፣ ያለ ቦታው የሚማስን ሕዝብ መሆኑን ስላሰበ ነው ። ለእግዚአብሔር ያለው ቅንዓት ለእስራኤልም ተረፈ ። ሙሴ በተፈጥሮ ለመሪነት የታጨ ነው ። እናቱም ትልቅ ቅንዓት አሳድራበታለች ። መሪ ለመሆን ከሚያስፈልጉ ነገሮች አንዱ ከማንነት ቀውስ መዳን ነው ። ሙሴ ኑሮው በቤተ መንግሥት ቢሆንም እውነተኛ ማንነቱ ግን ከተጨቋኝ እስራኤል ጋር መሆኑን እናቱ ነግራዋለች ። አልጋ ወራሽና ቀጥሎ በግብጽ የመንገሥ ዕድሉ ሰፊ ቢሆንም ዓለምን ናቀ ። ባለ ራእይ የሆነ ሰው ዓለምን ከነክብሩና ወርቁ መናቅ ያስፈልገዋል ። የወርቅ ወዳጅ የሕዝብ ወዳጅ መሆን አይችልም ።

ሙሴ ስለ ወገኑ ስቃይና መከራ ሕመም ይሰማው ነበረ ። በራሱ ላይ ስደት እስኪጋብዝ ድረስ ከጊዜው በፊት ወጥቶ ነገር አበላሸ ። እንኳን ሕዝቡን ነጻ ሊያወጣ ራሱም ስደተኛና ኮብላይ ሆነ ። ከቤተ መንግሥት ምድረ በዳ ፣ ከልዑልነት እረኝነት መጣ ። ተስፋ ይቁረጥ አይቁረጥ ባናውቅም አርባ ዓመት ይህ ኑሮው ቀጠለ ። ሲመሽ የእግዚአብሔር ጥሪ መጣለት ። የበግ ሳይሆን የሕዝብ እረኛ መሆኑን ነገረው ። የሚሰደድ ሳይሆን ሕዝብን እየመራ ከግዞት ቤት የሚያወጣ ሆነ ። ያን ሕዝብ የሚመራው ደግሞ በምድረ በዳ ነው ። በጀቱም ከሰማይ ነው ። ይህ መሪነት እምነትን የሚፈልግ ነበረ ። አንድ ዘመን ክርስቶስ ፍጹም ድህነትን መርጦ ፣ እርቃኑን ተሰቅሎ ሕዝቡን ከዲያብሎስ ባርነት እንደሚያወጣ እያሰበ እስራኤልን መራ ። መሪው ሙሴ ከአምስት መቶ ሰባ ጊዜ በላይ ከእግዚአብሔር ጋር ተነጋግሯል ። መሪው መሪ ነበረው ።

ያ ሕዝብ ግን በፈርዖን ትዕቢት እንዳላዘነ ፣ በሙሴ ትሕትና ቀለደ ። ረሀብ እንዳላታከተው መና ሰለቸኝ አለ ። የደመና ጥላ ተዘርግቶለት እንደ ልዑል ሲጓዝ ለእግዚአብሔር እኔ ከሌለሁት አይኖርም ብሎ አሰበ ። ከፊቱ ያለውን ሙሴን መስመር ጠብቆ እንደ መከተል ጠልፎ ጣለው ። ሙሴ በመራው ሕዝብ ተሰናክሎ ከታላቁ ግብ ከከነዓን ቀረ ። ከግብጽ ከወጣው ሕዝብ ሁለት ሰው ብቻ ከነዓንን ሲወርስ ሚሊየን ሕዝብ ከነዓንን እያሰበ ሲና ላይ ረግፎ ቀረ ። ሙሴ አዲሱን ትውልድ ተስፈ ሳይቆርጥ ተመለከተ ። ኦሪት ዘዳግምን አስተማራቸው ። እርሱ ባይወርስም የሚወርሱትን መመሪያ ሰጣቸው ። ካለፈው ትውልድ ኢያሱና ካሌብ ሲተርፉ ሌላው ለሙሴም እንቅፋት ሁኖ በምድረ በዳ ቀረ ። ሙሴ የተስፋይቱን ምድር በናባው ተራራ ላይ አይቶ በሩቅ ተሳለማት ። /ዘዳ. 32፡49፤ 34፡1 ።/ ይህ ሙሴ ከነዓንን የተሳለመበት የናባው ተራራ በጆርዳን አገር የሚገኝ ነው ። በዚህ ተራራ ላይ ቆሞ ምድረ እስራኤልን ማየት ይቻላል ። ይህን ተራራ ለማየት እናፍቅ ነበር ። ። በዚህ ተራራ ላይ ለመቆም በቻልኩ ቀን “ጌታ ሆይ ፣ የእኔ መጨረሻ አንተ ያየህልኝ ከነዓን ይሁን” ብዬ ጸልያለሁ ።

ሙሴ አልጋ ወራሽነቱን ቢቀበል ኖሮ የግብጽ ንጉሥ ይሆናል ። የፈርዖን ወንበር እንደ ፈርዖን እንዲያስብ ያደርገዋልና እስራኤልን ይበድል ነበር ። ለወገኑ ራራ እንዳይባል የበለጠ ቀንበር ይጭንባቸው እንደነበር ጥርጥር የለውም ። እግዚአብሔር ከክብር ለይቶ ክብር ሰጠው ።

ውስጣዊ ብስጭትን ከሚያመጡ ነገሮች አንዱ የኖርንለትን ሕዝብ መክሰር ነው ። ሙሴ ግን አልተበሳጨም ። ሕዝቡንም አልረገመም ። የራሱን መቃብር ቆፍሮ በሰላም አንቀላፋ ። ዋጋችን ያለው በመታመናችን እንጂ ሰዎች በተቀበሉበት ልክ አይደለም ። ካለፈው ትውልድ ሚሊየን ብንከስር አዲሱን ትውልድ ተስፋ ማድረግ መልካም ነው ። እኛ ባንወርስም የሚወርሱትን መንገድ ማሳየት ቅንነት ነው ። ውስጣዊ ብስጭት ግን የሰውን ነጻ ፈቃድ አለማክበር ነው ። ትውልድን መርቆ መሄድም የሰላም ዕረፍት የሚሰጥ ነው ። ሙሴ የከበረው ከሕይወቱ በሞቱ ነው ። እስከ ዛሬም ድረስ በክብር ሲነሣ ይኖራል ። ራእይ በሕይወታችን ቀርቶ በሞታችን ያብባል ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በትምህርቱ እስራኤልን ፣ በሞቱ ዓለምን አገለገለ ። የስንዴ ቅንጣት ,ስትሞት በብዙ ፍሬ ትነሣለች ። “ክርስቲያንና ዶሮ በሞቱ ይከብራል” እንዲሉ ። ዶሮ በቁሟ ሁሉም እሽ እያለ ያባርራታል ፣ ስትሞት ግን የንጉሥ የአባወራ የክብር ምግብ ናት ። ክርስቲያንም ሲሞት ሰማዕት ሁኖ ሲዘከር ይኖራል ።

ይቀጥላል

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ጥር 6 ቀን 2015 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ