የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ውስጣዊ ቍጣ / ክፍል 8

“የሰው ቍጣ የእግዚአብሔርን ጽድቅ አይሠራምና ።” ያዕ. 1 ፡ 20 ።

9- ሌሎች ባላቸው ነገር ሲኮሩብን

ይህ ዓለም የማገልገልና የመገልገል ዕድል ያለበት ዓለም ነው ። ያገለገሉ መገልገልን ይፈልጋሉ ። ሁልጊዜ አገልጋይ ሁልጊዜም ተገልጋይ መሆን የለም ። እግዚአብሔር ብዙ ጸጋውን ለብዙ ሰዎች ናኝቷል ። ጸጋን ሁሉ ጠቅልሎ የያዘና ምንም ጸጋ የሌለው ሰው የለም ። የመስጠት ብቻ ሳይሆን የመቀበልም ተራ አለ ። የአንድ ዘመን ኃያል የሌላ ዘመን ደካማ ነው ። ደካማ የነበረውም ይበረታል ። ሁልጊዜ መታመም ሁልጊዜ ጤና መሆን የለም ። ከጤናችን ቀን ለበሽታችን ቀን ማሰብ መልካም ነው ። ይህ ምን ማለት ነው ? ካልን በጥንቃቄ መኖር ፣ ለታመሙ ሰዎች ቸርነት ማድረግ ነው ። የመዝራትና የማጨድ ሕግ ቋሚ ነው ። ያሳደግናቸው ልጆች ይጦሩናል ። የደከምንለት መንግሥት ጡረታችንን ያስከብራል ። በወጣትነታችን ለሽማግሌዎች ቅድሚያ ሰጥተን ከነበረ ፣ እኛም በሽምግልናችን ወጣቶች ቅደሙ ይሉናል ። ዓለም በየዕለቱ ትለዋወጣለች ። የትላንት ጎበዝ ዛሬ ደክሞት አድሯል ። ሥራውን በኃይል ሲሠራ የነበረው ዛሬ ማለዳ መነሣት ተስኖታል ። ሕያው የነበረው ይሞታል ፣ ያልታየው ጽንስ ልጅ ሁኖ ይወለዳል ። ተገዥው ወደ ዙፋን ይወጣል ፣ ንጉሥ ወደ ወኅኒ ይወርዳል ።

መሬት ትዞራለች ሲባል ብቻዋን ሳይሆን እኛን ይዛ ትዞራለች ። እኛ ዞርን ላለማለት ፀሐይ በምሥራቅ ወጣች ፣ በምዕራብ አማረች እንላለን ። ሐቁ የዛሬ እንጂ የነገ ጎበዝ አለመሆናችን ነው ። ጸሎተ ሐና ነቢይት ፣ ጸሎተ እግዝእትነ ማርያም ይህን የሚናገር ነው፡-

“አትታበዩ ፥ በኩራትም አትናገሩ እግዚአብሔር አዋቂ ነውና ፥ እግዚአብሔርም ሥራውን የሚመዝን ነውና ፥ ከአፋችሁ የኵራት ነገር አይውጣ ። የኃያላንን ቀስት ሰብሮአል ፥ ደካሞችንም በኃይል ታጥቀዋል። ጠግበው የነበሩ እንጀራ አጡ ተርበው የነበሩ ከራብ ዐርፈዋል መካኒቱ ሰባት ወልዳለችና፥ ብዙም የወለደችው ደክማለች ። እግዚአብሔር ይገድላል ያድናልም ወደ ሲኦል ያወርዳል ፥ ያወጣል ። እግዚአብሔር ድሀ ያደርጋል ፥ ባለጠጋም ያደርጋል ያዋርዳል ፥ ደግሞም ከፍ ከፍ ያደርጋል። …” 1ሳሙ. 2፡3-7 ።

“በክንዱ ኃይል አድርጎአል ፤ ትዕቢተኞችን በልባቸው አሳብ በትኖአል ፤ ገዥዎችን ከዙፋናቸው አዋርዶአል ፤ ትሑታንንም ከፍ አድርጎአል ፤ የተራቡትን በበጎ ነገር አጥግቦአል ፤ ባለ ጠጎችንም ባዶአቸውን ሰዶአቸዋል ።” ሉቃ. 1፡51-53 ።

አቅላቸውን ስተው በመንገድ የወደቁ ምሁራንን ተመልከቱና በእውቀታችሁ አትኩሩ ። እጅ እግራቸው ታስሮ እቤት የቀሩትን ባለሙያዎች አስታውሱና በሙያችሁ አትኩሩ ። ሰውን ለማስደሰቻ የተሰጣችሁን ሥልጣን ለማስለቀሻ አትጠቀሙበት ። ለሌላው የመሸ ቀን ለእኔም ይመሻል ብላችሁ ፈሪሀ እግዚአብሔርን ገንዘብ አድርጉ !

ውስጣችን ብስጩ ከሚሆንባቸው ነገሮች አንዱ ሌሎች በሙያቸው ሲኮሩብን ነው ። በውስጣችን ከተጻፈው ሕግ ተነሥተን ቍጡ ሁነናል ። በውስጣችን የተጻፈው ሕግ እግዚአብሔር እውቀትና ተሰጥኦ የሚያድለው ሌሎችን በትሕትናና በትጋት ለማገልገል እንጂ ራስን ለመከመር አለመሆኑን ይነግረናል ። ሌሎች በሙያቸው ሲኮሩብን ሦስት ነገሮችን ማሰብ አለብን ። የመጀመሪያው፡- እኔስ በተሰጠኝ ነገር ትሑት አገልጋይ ነኝ ወይ ? ብለን ራሳችንን መጠየቅ አለብን ። ሁለተኛው፡- ማድረግ የምንችለውን ትንሽ ነገር ከሰው ከመጠበቅ ራሳችን ለማከናወን ማጥናትና መሞከር ያስፈልገናል ። ሦስተኛ ሁሉን ልንማርና ልናውቅ አንችልምና ትዕግሥትን ማዳበር ይገባናል ። ጸሎተ ሃይማኖት ድንቅ የሃይማታችን አቋም ነው ። ጸሎተ ሃይማኖት እንዲረቀቅ ምክንያት የሆኑት ግን መናፍቃን ናቸው ። አርዮስና መቅዶንዮስ ይህ ጸሎት እንዲገኝ ምክንያት ሁነዋል ። ረቂቅ ሃይማኖታዊ ምርምሮች ፣ ነገረ እግዚአብሔርን የሚመለከቱ ትምህርቶች በመናፍቃን ጥያቄና ፍልስፍና ምክንያት ቤተ ክርስቲያን የተጋችባቸው ምሥጢራት ናቸው ። “ምቀኛ ጎረቤት ዕቃ ያስገዛል” እንዲሉ ።

ሙያን የጠባይ ምትክ ያደረጉ ወገኖች ብዙ ናቸው ። በቂ እውቀትና ጥሩ ሙያ ያላቸው ሰዎች የጠባይ ድሆች ሁነው በአብዛኛው ይታያሉ ። የዚህ ምክንያቱ የመጀመሪያው ዲያብሎሳዊ ትዕቢት አድሮባቸው ነው ። ሁለተኛው፡- በሕይወታቸው እርካታ ማጣታቸው ነው ። ሌላውን የሚያስቁ ኮሜዲያን በሕይወታቸው ኀዘነተኞች ናቸው ። ለሌላው የሚኖሩ ለራሳቸው የሚኖርላቸው ያለ ስለማይመስላቸው ብስጩ ይሆናሉ ። በዚህ ምክንያት ሙያቸውን ጠባያቸው ይጋርደዋል ። ጠባይ ሲቀድም ሙያ ሲከተል መልካም ነው ። ሌላው አማራጮችን ማብዛት በሙያቸው ከሚያበሳጩን ሰዎች ለመዳን ይረዳናል ። በሰለጠነው ዓለም ብዙ አማራጮች ስላሉ ደምበኛ ንጉሥ ነው ። እኛ አገር ደግሞ ነጋዴ ንጉሥ ነው ። እግዚአብሔር አምላክ ለሁሉም መክሊት ሰጥቶታል ። እውቀትም የሚመነዘር ገንዘብ ፣ ሙያም መክሊት ነው ። ገንዘብ ስለያዙ ጥጋብ የለም ። የሚገዛው ነገር መኖር አለበት ። ባለሙያም ፈላጊውን ማክበር አለበት ። የጨጓራ በሽታ ከምድር ላይ ቢጠፋ በዚህ መስክ ያጠናው ባለሙያ ድካሙ ከንቱ ይሆናል ። እኛን ልክ ያደረጉን ፣ ተፈላጊ እንድንሆን የረዱን የምንንቃቸው ወገኖች ሊሆኑ ይችላሉ ። “ማን ላይ ተቀምጠሸ ማንን ታሚያለሽ ?” ይባላል ።

አዎ ሌሎች በሙያቸው ሲኮሩብን ውስጣዊ ቍጣ ይሰማናል ። ሁሉን ነገር ሰው ያድርግልኝ ከማለት ፣ ለጥቃቅኑ ነገር ሰው ከመፈለግ ጎበዝ መሆን ይገባናል ። ሕይወት እንደ ወታደር ቁፍጥንናን ፣ እንደ መንገደኛ ወገብ ማሰርን ትጠይቃለች ።

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
የካቲት 1 ቀን 2015 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ