ውሸት ይወገድ
“ስለዚህ ውሸትን አስወግዳችሁ ፥ እርስ በርሳችን ብልቶች ሆነናልና እያንዳንዳችሁ ከባልንጀሮቻችሁ ጋር እውነትን ተነጋገሩ ።” ኤፌ. 4 ፡25 ።
“ቆሻሻ በአግባቡ ከተወገደ ሀብት ነው” የሚል አባባል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይሰማል ። ቆሻሻ በራሱ ሀብት አይደለም ። በአግባቡ ከተወገደ ግን ለጥቅም ይውላል ። በዚህ ምክንያት የተደራጁ ወጣቶች ቆሻሻችንን ከየቤታችን ይወስዳሉ ። እኛ እንኳ የምንጸየፈውን የራሳችንን ቆሻሻ ለሚያነሡልን ወጣቶችና ሠራተኞች ክብር መስጠት ፣ አብረናቸው እንጀራ መቍረስ ይገባናል ። ባለውለታዎቻችን ናቸው ። እነዚህ ሠራተኞች ለአንድ ወር ዘወር ቢሉ ከተማዋ ከተማ አትሆንም ። በሁሉም አገር ቆሻሻ አለ ። በሁሉም አገር ሠራተኞች አሉ ። በሠለጠነ አገር ግን ዝቅ ብለው ለሚሠሩት ክብር ይሰጣቸዋል ። ደመወዛቸውም ላቅ ያለ ነው ። ሥልጣኔው ቆሻሻችን ሀብት ነው ብሎ መጥቷል ። በዚህም ሁሉንም ቆሻሻ በአንድ ላይ በማድረግ ሳይሆን በየመልኩ በማስቀመጥ እንድናሰናዳ ያበረታታናል ። ቆሻሻ ከተቀላቀለ ሀብት አይሆንም ፣ በየመልኩ ሲቀመጥ ግን ሀብት ይሆናል ። ንስሐችንም በአግባቡ ከተወገደ ሌላውን ለማነጽ ሀብት ይሆነናል ። ቆሻሻ በመቀመጡ ሳይሆን በአግባቡ በመወገዱ ሀብት ነው ። በመቀመጡ ግን በካይ ነው ። እንዲሁም ስህተታችንን አፍነን በመኖራችን ፣ ካባ አልብሰን በመንከባከባችን ሳይሆን በትክክለኛው መንገድ ንስሐ በመግባታችን ፈውስ ይሆናል ። ቆሻሻ ምንም ወርቀ ዘቦ ግምጃ ቢያለብሱት ቆሻሻ መሆኑ አይቀርም ። ቢሸፈን ሽታው ያውካል ፣ በበሽታነቱ ጤናን ያቃውሳል ። ስህተትንም ቢቀባቡት ጥቅም የለውም ። ቢያስወግዱት ግን ከመሳሳት በላይ ነው ። በመልኩ ማስቀመጥም መልካም ነው ። ለስህተታችን መነሻውንና ጉዳቱን መመዘን መቻል ፣ ኃላፊነት መውሰድ ፈውስን ያፈጥናል ።
ቆሻሻ መወገድ አለበት ። በዚህ ዓለም ላይ ካሉ ቆሻሻ ነገሮች አንዱ ውሸት ነው ። ቆሻሻ ዓይንን ፣ አፍንጫን ያውካል ። ውሸትም ሰላምን ያሳጣል ። ቆሻሻ ያቆሽሻል ። ውሸትም ይበክላል ። ቆሻሻ ሰው እንዲርቀን ያደርጋል ፤ ውሸትም ወዳጅ ያሳጣል ። ቆሻሻ ካለ ሰው እቤታችን ባይመጣ እንወዳለን ፣ ውሸትም የድብብቆሽ ኑሮ ያመጣል ። ቆሻሻን ማስወገድ አለብን ። ያቆሸሹትን ልጆቻችንን ግን አናስወግድም ። እንዲሁም ውሸትን ማስወገድ እንጂ ውሸታሞችን መግደል አይገባንም ። የውሸታሞች መሞት የውሸት መሞት አይደለም ። የውሸት መሞት ግን የውሸታሞች መሞት ነው ። ውሸት ኃያል አይደለችም ። ጨለማ በሻማ ብርሃን ይጠቃል ፣ ውሸትም በትንሽ እውነት ይሸነፋል ። ብርሃን በሰፋ ቍጥር ጨለማ ይሸሻል ፣ እውነትም ሲገዛ ውሸት ድል ይነሣል ። የብርሃን አለመኖር የጨለማን መኖር ያስከትላል ። የእውነት አለመኖርም ውሸትን በግድ ያመጣል ።
የእኛን ዘመን ስንመለከተው ውሸት እንደ እውነት የሚታይበት ፣ ውሸታሞች ከእውነተኞች ይልቅ አጋፋሪና ጋሻ ጃግሬ ያገኙበት ነው ። ከመቀመጫቸው ሳይነሡ ፣ ከቤታችው ሳይወጡ ለሚዋሹ ሰዎች ብዙዎች አለሁ ብለው ይቆሙላቸዋል ። የውሸት ደጋፊ እየበዛ ይመስላል ። እውነት ከውሸት በላይ የሚያበሳጨው ትውልድ ከመጣ ውሸት እየገዛን እንደሆነ ማሳያ ነው ። ውሸት ብዙ ዘርፎች አሉት ። ፖለቲካ የሚወልደው ዓይናውጣነት እርሱ ውሸት ነው ። እውነት ብለን የነገርነውን እውነት ብሎ ይቀበላል ብለው ሕዝብን እንደ ፈጠሩት የሚያስቡ ፖለቲከኞች ውሸትን የመንገዳቸው ስልት ያደርጓታል ። ሽንገላም የውሸት ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤት ነው ። ሽንገላ በአፍ ያኑርልኝ እያሉ በልብ ደግሞ በመብረቅ ያንድድህ ማለት ነው ። “እባብ በአንድ ራስ ሁለት ምላስ” እንዲሉ ሸንጋይም እንዲሁ ነው ። ሸንጋይ እንደ እባብ በጣም ለስላሳ ፣ በጣም መርዛም ነው ። ኃይለኛና ቍጡ ሰውን እንጠላዋለን እንጂ ብዙ ጊዜ ውስጡ ሐቀኛ ነው ። ሰሚ ስላጣ ግን ቍጠኛ በመሆኑ እናወግዘዋለን ። ሸንጋይ አይቆጣም ፣ ረጅም ሞት እንድንሞት ግን ያደርገናል ።
የሰጡትን ቃል ማፍረስ ፣ መሐላን በገንዘብ መለወጥ እርሱ ውሸት ነው ። ምክንያተኝነትም የውሸት አካል ነው ። የዲፕሎማሲ ቋንቋና አካሄድም ለውሸት ያደላ ነው ። ዲፕሎማሲ ሁሉም ትክክል ነው ብሎ ማለፍና ያለመፍረድ አካሄድ ነው ። ፍርድ መስጠት ካልተቻለ ሰላም ሊመጣ አይችልም ። የቤትና የደጅ አመል መያዝ ሁለት ዓይነት ሰው መሆን ውሸት ነው ። ለውዳሴ ከንቱ መጾምና መጸለይ ውሸት ነው ።
ውሸት በሰማይ ርስትን ፣ በምድር ክብርን ያሳጣል ። “አፍና ቅብቅብ ሁልጊዜ አያበላም” እንዲሉ ውሸትም ሁልጊዜ አያኖርም ። ውሸትን ማስወገድ ይገባል ። ምንም ካባ ቢያለብሷት ፣ ንግግርን ቢያሰማምሩላት ውሸት ውሸት ናት ። ውሸት እንደ ጥላሸት የምታቆሽሽ ፣ የነካነውንም ሰው የምታረክስ ናት ። ውሸት ሚዛናዊነትን መጣል ነው ። የሚዋልል ሚዛን እርሱ ውሸታም ነው ። ውሸት ፍርድ እንዲዛባ ፣ ጨዋዎች አንገት እንዲደፉ ፣ አገር እንዲታወክ ያደርጋል ። “ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው” እንዲሉ ። ዐፄ ቴዎድሮስ “እንኳን በጦርነት በወሬም አልተሸነፍንም” አሉ ይባላል ።
እርስ በርሳችን እውነትን መነጋገር ይገባናል ። ምክንያቱም ግራ እጅ ቀኝ እጅን አይዋሸውምና እኛም እርስ በርሳችን እውነት መነጋገር ይገባናል ። አካል ነንና ።
ለውሸት ጊዜ ከመስጠት ፣ ውሸትን ከማራገብ ፣ ሳናጣራ ከማውራት ፣ ሰማሁ ብሎ ከመለፍለፍ መራቅ ይገባናል ። ውሸታም አይደለሁም ብሎ ውሸታን ማድነቅና መርዳት እርሱ ውሸታምነት ነው ።
እውነትን እንለማመድ ።
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ኅዳር 10 ቀን 2014 ዓ.ም.