መግቢያ » ልዩ ልዩ አንድ » ዐሥራ አምስቱ የሕይወት ሕጎች » ዐሥራ አምስቱ የሕይወት ሕጎች -2

የትምህርቱ ርዕስ | ዐሥራ አምስቱ የሕይወት ሕጎች -2

ፍቅርና አክብሮታችሁን ከሚያቃልሉ ሰዎች ራቁ፡-

ሁሉን መውደድና ማክበር እግዚአብሔርን የመውደድና የማክበር ውጤት ነው ። ስትወዱአቸው ምን ፈልጎ ነው ?ስታከብሯቸው ግርማዬ አስደንግጦት ነው ብለው የሚያስቡ ሰዎችን ከማስተማር ይልቅ የበለጠ ባለጌ ታደርጓቸዋላችሁ ። ተበድላችሁ ይቅርታ ብትጠይቁ እሳቱን ለጊዜው ማብረድ ይቻል ይሆናል ። እውነት ላይ ያልተመሠረተ ነገር ዕድሜ የለውም ። ደግሞም እነዚያ ሰዎች ሳይለወጡ በብልግናቸው እንዲጸኑ ታደርጋላችሁ ። ፍቅርና አክብሮታችሁ ዋጋ በሌለው ቦታ ላይ አትቆዩ ። ግን ሁሉን ውደዱ ፣ አክብሩ ።

እኔ የማስፈልገው ለማን ነው በሉ፡-

ሰው ያለ አገሩ አይከብርም ፣ ያለ ቦታውም ውጤታማ አይሆንም ። ሁሉን አውቃለሁ ፣ ሁሉም ቦታ መገኘት አለብኝ የሚል ምንም የማያውቅና የትም ቦታ ሳይደርስ የሚቀር ነው ። ኃይለኛና ቍጠኛ የምትሆኑት ስንፍናችሁንና ባዶ ፕሮግራማችሁን ሰዎች አይተው እንዳይንቁአችሁ ፈርታችሁ ነው ። እኔ ዛሬ ላይ በትክክል የማስፈልገው ለማን ነው ? ማለት ቀኑን ይቀድሰዋል ። ሰው የሚበድለው ያለ ቦታው ሲውል ነው ። ያለ ቦታው ሲውልም ውርደትን ያስተናግዳል ። ዛሬ ላይ በትክክል የማስፈልገው ለማን ነው ? ማለት ጊዜን ይቆጥባል ። ያለ ቦታችሁ የሆነ ውሎ መጨረሻ በጠላትነት የሚጠናቀቅ ነው ። ከሚቀናባችሁ ሰው ጋር መኖርና ያለ ቦታችሁ መገኘት ዕድሜን ያሳጥራል ። ቀናተኛው ወደ እናንተ ሲመጣ እናንተ ደግሞ የምትሄዱት ባልተሾማችሁበት ስፍራ ነው ። ባልተሾመበት ስፍራ የሚያዝዝ ታዛዥ አያገኝም ።

መጀመሪያ ተነጋገሩ፡-

እንደ ፈላ ጠጅና እንደ ደረሰ ጠላ ሌሊትና ቀን ስትብላሉ መኖር ተገቢ አይደለም ። ሥራ ከመጀመራችሁ በፊት ዋጋ ተነጋገሩ ፤ ወዳጅነትን ከመጀመራችሁ በፊት አቋማችሁን ግለጡ ። ወደ ትዳር ከመግባታችሁ በፊት “እኔ ይህን አሟላለሁ እገሌስ ምን ያሟላል?” ብላችሁ ተወያዩ ። ሰውን ከመሾማችሁ በፊት በጣም አሳብ ስብስቡ ። አሊያ ቁጭ ብለው የሰቀሉትን ቆሞ ማውረድ ይቸግራልና ። መሐል መንገድ የሚጣሉ ፣ መሐል ባሕር ላይ መቅዘፊያውን ጥለው የሚደባደቡ መጀመሪያ ያልተነጋገሩ ናቸው ። ዋናው ፍቅሩ ነው አትበሉ ፣ መጀመሪያ ተነጋገሩ ። ስሜት ያልቃል ፣ እውነቱ ይቀራል ። እርሱም በሃይማኖቱ እኔ በሃይማኖቴ የሚባለው የሚዘልቅ አይደለም ። ስትሰለቻቹ የመጣያ ርእስ ሆኖ ይመጣል ።

ካለቀ በኋላ ንግግር አታብዙ፡-

ምክንያቱም አልቋልና ። ካለቀ በኋላ ክፉ ቃል መነጋገር ባለፈ ክረምት ላይ ቤት ካልሠራሁ ብሎ መታገል ነው ። መዋደድ እንዳለ መጣላት አለና ራስን ማዘጋጀት መልካም ነው ። ዞር ባለ ጊዜ እንዳትወድቁ በጣም ሰው ላይ አትደገፉ ። ሚስትህን ብትፈታት የቀድሞ ሚስቴ ትላታለህ ፣ ለልጅህ ግን የቀድሞ እናት አትባልምና ለልጅህ ሞራል ስትል ዝም በል ።

ሕሊናህን ከሚቆረቁር ነገር ጠብቅ፡-

“ማንም ሰው በውስጡ የማይነገር ምሥጢርና የማይመለስ ጸጸት አለው” ይባላል ። ምሥጢርህን ለሃይማኖት አባትህ ግለጥ ፣ ጸጸትህን በንስሐ ዝጋው ። ለወደፊት የሚያጸጽት ነገር ውስጥ አትግባ ። ካበደ ዘመን ጋር አብረህ አትበድ ። ከጠበኛው በላይ ጠበኛ ሆነህ አትሳደብ ። ኢትዮጵያ ለራሽያ ወግና አሜሪካንን ከራሽያ በላይ ትጠላ ነበር ። ራሽያና አሜሪካ ግን ያልተዘጋ የጥቅም ግንኙነት ነበራቸውና “ከእኛ በላይ አትጣሉ ፣ በረድ አድርጉት” ይሉን ነበር ። ዛሬም ከተጣዪው በላይ የሚጣሉ ፣ አንዱን ለማስደሰት ብዙውን የሚያስከፉ ፣ ራሳቸውን የሚያስገምቱ ብዙዎች ናቸው ። ለሚያልፍ ቀን የማያልፍ ንግግር ተናግረው ዛሬ ዱዳ የሆኑ አያሌ ናቸው ።

ጌታ ሆይ በዚህ አጭር ዘመን ብዙ ዓይነት ሰው ከመሆን ጠብቀን !

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሰኔ 12 ቀን 2017 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ