መግቢያ » ልዩ ልዩ አንድ » ዐሥራ አምስቱ የሕይወት ሕጎች » ዐሥራ አምስቱ የሕይወት ሕጎች -3

የትምህርቱ ርዕስ | ዐሥራ አምስቱ የሕይወት ሕጎች -3

ብዙ አትናገሩ፡-

ብዙ በተናገራችሁ ቍጥር ተደማጭነታችሁና ክብራችሁ እየቀነሰ ይመጣል ። ሰዎችም ንግግራችሁን እንደ ዜማ መስማት ይጀምራሉ ። ልባችሁን በሙሉ አውቀው የጨረሱት ስለሚመስላቸው ምንም አያመጡም ብለው ይንቁአችኋል ፣ ይጋጠሙአችኋል ። ብዙ በተናገራችሁ ቍጥር የሚያበሳጭ ንግግር ትሰማላችሁ ፣ ከዚያ በኋላ መልስ እሰጣለሁ ስትሉ በራሳችሁ እሳት እየነደዳችሁ ትሰቃያላችሁ ። ንግግራችሁ የተመጠነ ፣ ቃላትን የመረጠ ፣ አክብሮት ያለው ፣ እንደ ደረጃችሁ ትእዛዝን የያዘ ይሁን ። ድምፃችሁን ከፍ አድርጋችሁ አትናገሩ ፣ ልምጥምጥ ያለ ንግግርም የራሳችሁን ንግግር ዋጋ የለሽ ያደርገዋል ። እርምጃ የማትወስዱ ከሆነ አታስፈራሩ ፣ ማስጠንቀቅን ግን አትርሱ ። “የማትናከስ ከሆነ ጥርስህን አታሳይ” ይባላል ። “ብዙ ቢያወጉ ይዘነጉ ፣ ብዙ ቢተቹ ይሰለቹ” እንዲሉ ንግግር ሲበዛ ሰዎች የፊቱን እየረሱ የኋላውን ይይዛሉ ፤ ትችት ሲበዛም ሰውዬው ገና ሳይጀምር ደግሞ ስለ ማን ሊያወራ ነው ? ተብሎ ጆሮ ይነፍጉታል ።

ለሚያንሰው ነገር አትቆጩ፡-

በሕመም አሳልፋችሁ ከሆነ አትበሳጩ ፣ ሞት ስለቀረላችሁ አመስግኑ ። መኪናችሁ በአደጋ ተጎድቶ ከሆነ ሕይወት በመትረፉ ምስጋና አቅርቡ ። ነገ ጥላችሁት የምትሄዱት ንብረት ዛሬ ቀድሟችሁ ከሄደ ደስ ይበላችሁ ። አዲስ ልብስ ተገዝቶ እንዲሁ አይለበስም ፣ ሽማግሌ ይመርቃል ። ሽማግሌውም፡- “በውኃ ይለቅ ፣ ቀድሞህ ይለቅ” ብሎ ይመርቃል ። ንብረት ቀድሞ ሲያልቅ የሚወደድ ነው ። በዚህ ምድር የትኛውም ነገር ከእናንተ የሚያንስ ነው ። “ዓይኗን ቢያጠፏት ቅንድቤን አደራ” አለች ይባላል ። ለሚያንሰው ነገር የሚቆጭ ፣ ትልቁን ሸኝቶ በትንሹ የሚያብድ ብዙ ሰው አለ ። ስንት ሕይወት ከአጠገባችሁ ሲጠፋ እያያችሁ ትልቁን አይታችሁ በትንሹ አትበሳጩ ።

አዳምጣችሁ ተናገሩ፡-

አዳምጦ የማይናገር ሰው ፣ ጫፍ ይዞ የሚሮጥ ጠብንና ፍርድን ያበዛል ። ንግግሩን ሳይጨርስ “እንዲህ ለማለት ፈልጎ ነው” በማለት ድምዳሜ አትስጡ ። እንኳን ንግግሩን ሳይጨርስ ጨርሶም ከተረዳችሁት ትልቅ ነገር ነው ። ውሳኔ የሚያስፈልግ ነገር ስትሰሙ ሦስት ቀን አሳድሩት እንጂ ፈጥናችሁ መልስ አትስጡ ። ሰዎች ሲያዳምጡአቸው ይረካሉ ። የሚሰማቸው ወዳጅ ፣ ሹም ፣ ዳኛ ፣ ሐኪም ፣ አበ ነፍስ ይፈልጋሉ ። ሰዎች ሲያዳምጧው ከሕመማቸው ይድናሉ ። “እህልን አላምጦ ፣ ነገርን አዳምጦ” ይባላል ። ያላላመጡት እህል ያንቃል ፣ ያላዳመጡት ነገር ያጣላል ። ሰዎች ምንም ቢናገሩ ዓመት ሙሉ አያወሩምና አዳምጡ ። ደግሞም መነጋገር የፈለገ ሰው መፍትሔ ፈላጊ ነው ። ጠላትማ በርቀት ይተኩሳል ። ማዳመጥ መልካም ነው ፣ ሰዎች የሚያውቁት የቅንነታችሁን መልክ ብቻ ይሆናል ፣ በማስፈራራት ወደ እናንተ ሲመጡ ሌላኛውን ውስጣዊ ብርታታችሁን ያውቁታል ።

ቃል አትግቡ፡-

ቃል መግባት መልካም ሊሆን ይችላል ። ሲናደዱ አለመናገር ፣ ሲደሰቱ ቃል አለመግባት ግን መልካም ነው ። የዮሐንስ አንገት የተቆረጠው ሄሮድስ ፈጥኖ ቃል በመግባቱ ነው ። ቃል በመግባት አንገት ቆራጭ እንዳትሆኑ ተጠንቀቁ ። በጣም ስትደሰቱ ወይም ስሜታዊ ስትሆኑ ቃል ገብታችሁ እቤታችሁ ስትደርሱ መፈጸም አለመቻላችሁን ባሰባችሁ ጊዜ በራሳችሁ ታፍራላችሁ ። በዚህ ዘመን “ቀኑ ሲደርስ ንገሩኝ ፣ ሁሉንም ወጪ እሸፍናለሁ” ብለው የሰርጉ ቀን ሲደርስ ሄደው ሲጠይቁአቸው፡- “ጫት ቅሜ ይሆናል እንጂ እኔ እንዴት ይህ ቃል እገባለሁ?” የሚሉ ሰዎችን እየሰማን ነው ። ቃል መግባት በሱስ ውስጥ ሲሆኑ በጣም ይበዛል ። ሱስ የሌለውን ጀግንነትና ባለጠግነት እንዳለ የሚያስመስል አታላይ ነው ።

አልችልም ማለትን ልመዱ፡-

አልችልም በማለታችሁ የምታተርፉት ምንም ዓይነት ጠላት የለም ። ራሳችሁን ካልተረዳችሁት ማንም ሊረዳችሁ አይችልም ። ተበድራችሁ ሰርግ አትደግሱ ፣ በይሉኝታ ግንብ ካልዘለልሁ አትበሉ ። ሰዎች እንደምትችሉ ለማረጋገጥ ጠየቁአችሁ እንጂ ካልቻላችሁ ብለው ወኅኒ ሊያወርዱአችሁ አልመጡም ። በጊዜው የሆነ እምቢታ የእሺታ ያህል ነው ። ብዙ ሰዎች ወዳጆቻቸውን በር ላይ አቁመዋል ፣ አልችልም ማለት የሚያሳንስ መስሎአቸው ራሳቸውንም ያንንም ሰው ጎድተዋል ። አልችልም ስትሉ ያ ሰው የሚችል ሰው እንዲያይ ታደርጉታላችሁ ። ሰዎች ስለገባው ገቢ ያውቃሉ ፣ ስላወጣችሁት ግን አያውቁም ። ማንም አልተረዳኝም ብላችሁ መራቆት አያስፈልጋችሁም ። በቻላችሁ ቀን ደግሞ ደራሽ ሁኑ ። እናንተ እሑድ ላይ ፋሲካ እየበላችሁ ከሆነ እነዚያ ደግሞ ዓርብ ላይ እሬት እየበሉ ይሆናል ። ቀኑ ሲለወጥ የእናንተ ዓርብ ይመጣልና በዙር ዓለም ላይ አትጨካከኑ ።

ፈጸምን !

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ሰኔ 13 ቀን 2017 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ