የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ዐርፍ ዘንድ ተወኝ (1)

“ወደማልመለስበት ሳልሄድ ዐርፍ ዘንድ ተወኝ ።” (መዝ. 38፡13) ።

ነቢዩ ዳዊት በሕይወቱ ብዙ ውጣ ውረድ አስተናግዷል ። ግን እግዚአብሔር እንደ ልቤ ያለው ሰው ነበር (የሐዋ. 13 ፡ 22) ። በእግዚአብሔር መወደድ ላለመፈተን ዋስትና አይደለም ። እንደውም እግዚአብሔር ለታላቅ ዓላማ የጠራቸው ሰዎች ብዙ የሕይወት ውጣ ውረድ አለባቸው ። እስራኤል በእግዚአብሔር የተወደዱ ናቸው ። ከመንፈሳዊ በረከት በቀር ሥጋዊ ጥቅም ያላገኙ ለአራት ሺህ ዓመታት እየተፈተኑ ያሉ ሕዝቦች ናቸው ። “እግዚአብሔርን ካመንህ አትታመምም ፣ ድሀ አትሆንም” የሚል ትምህርት ከየት ምንጭ እንደ ተቀዳ አይታወቅም ። በዘመነ አበው ኢዮብ ብዙ መከራ ተቀበለ ፣ በዘመነ ኦሪት ነቢዩ ዳዊት በፈተና ሰፌድ ላይ ተንቀረቀበ ፣ በዘመነ ሐዲስ ቅዱስ ጳውሎስ በብርቱ ሕመም ተሰቃየ ። የሚገርመው ጻድቁ ኢዮብ ብዙዎችን አጽናንቷል ፣ የእርሱ መከራ ግን አጋር አልነበረውም ። ነቢዩ ዳዊት ለብዙዎች ዘመድ ሆኗል ፣ እርሱ ግን ከወዳጅ እስከ ልጅ ጠላት የሆኑበት ነው ። ቅዱስ ጳውሎስ በጥላው ድውያንን ፈውሷል ፣ እርሱ ግን በሕመም የሚንገላታ ሰው ነው ። ልብ አድርጉ ጻድቅ ፣ ነቢይ ፣ ሐዋርያ ይንገላቱ ነበር ።

ነቢዩ ዳዊት ብዙ ሀብታት ወይም ጸጋ እግዚአብሔር ነበረው ። የፈውስ ሀብት ነበረው ። ሳኦልን በገና እየደረደረ ከስቃዩ ያሳርፈው ነበር ። ሀብተ ስብሐት ነበረው ፣ እግዚአብሔርን በብዙ ዝማሬ አክብሯል ። ሀብተ መዊዕ (የማሸነፍ ጸጋ) ነበረው ፣ ጠላቶቹን ሁሉ ረትቷል ። ሀብተ ትንቢት ነበረው ፣ ብዙዎችን አስተምሯል ፣ ባሻገር ስለ ክርስቶስ ሰው መሆን ተናግሯል ። ሀብተ ቸርነት ነበረው ፣ በተሰጠው ልክ ይለግስ ነበር ። ሀብተ ሥልጣን ነበረው ፣ አርባ ዓመት እስራኤልን አስተዳድሯል ።

ይህ ዳዊት ከልደት እስከ ሞት ብዙ ፈተና ያሳለፈ ሰው ነው ። አንዳንድ ጊዜ የገዛ ዘመዶቹ ጠልፈው ይጥሉት ነበር ። ሌላ ጊዜ እነ ሳኦል ና ብለው ዕዳ ውስጥ ይከቱት ነበር ። አልፎ አልፎም የራሱ እግሮች እየተማቱ ይወድቅ ነበር ። ነቢዩ ዳዊት በልጆች ተፈትኗል ፣ ልጆቹ እርስ በርስ ሲጋደሉ አይቷል ። አልቃሽም ዳኛም መሆን ከባድ መሆኑን አስተውሏል ። ወዳጅ ሲንሸራተት ፣ አጠገብ የነበረ ርቆ ሲተኩስ ተመልክቷል ።

በኀዘንም በደስታም ፣ በሸለቆም በተራራም ፣ በጉምም በጠራራም በገናውን ያነሣ ፣ መሰንቆውን ይገዘግዝ ነበር ። በክፉ ቀን ቢዘምሩ እግዚአብሔር ማንጋት ሥልጣኑ መሆኑን ማመን ነው ። በደግ ዘመን ቢያመሰግኑ እግዚአብሔር የበጎ በረከት ምንጭ ስለሆነ ነው ። ነቢዩ የዕንባ ሀብት ነበረውና በቀንና በሌሊት ያለቅስ ነበር ። አእምሮውን ያልከሰረውም በሁለት ነገር ይሆናል፡- በዕንባና በዝማሬ ። መናቁ በክብር ፣ መገፋቱ አገር በመውረስ ቢለወጥም ፈተናው ግን በሌላ መልክ ይመጣ ነበር ። አልከዳ ያለው ወዳጁ መከራ ብቻ ነበር ። ነቢዩ ዳዊት በዚህ ሁሉ ፈተና ፣ በአባትና በጠላት ቤት ፣ በእረኝነትና በንጉሥነት ፣ በደሳሳ ጎጆና በቤተ መንገሥት ብዙ ውጣ ውረድ አይቷል ። በጌታችን ልደት እረኞችና ነገሥታት ተገኝተዋል ። እጅግ ዝቅ ያሉትና እጅግ ከፍ ያሉት የልደተ ክርስቶስ ታዳሚዎች ነበሩ ። ዳዊት እረኛም ንጉሥም ነበር ። ሁለቱንም የሕይወት ጽንፍ የነካ ፣ ለመምከር የሚበቃ ነበር ። ባለ ቅኔው፡-

እንግዲህ አልደግምም ዳዊት ይበቃኛል ፣
ንግግሩ ሁሉ ጸጸት ሆኖብኛል”

ብሏል ። ዳዊትን ዳግም አላነሣውም መከራው ያሳዝነኛል ማለቱ ነው ። ምሥጢሩ ደግሞ መዝሙሩ ቃለ ንስሐ ፣ የዓለምን ከንቱነት የሚያወሳ ነው ማለቱ ነው ። ዳዊት መከራ እንደ መጠጥ አስክሮታል ። ከሰው ጋር መኖር ፈትኖታል ። ለሰው የቱ ይሻል ይሆን ? የሚለው ምርጫ አናውዞታል ። ሲናገር ሰው እየተቀየመው ፣ ዝም ሲል ፍርደ ገምድል የሆነ እየመሰለው ቢጨነቅ ዝም ለማለት ቃል ገብቷል ። “እም ተናግሮ ይኄይስ አርምሞ- ከመናገር ዝም ማለት ይሻላል” የሚል አሳብ ውስጥ ገብቷል ። ሊቁ፡-

እመ ተናገርኩ ጽድቀ ሰብአ ዛቲ ዓለም ይጸልዑኒ ፤
ወከመ ኢይንብብ ሐሰተ ኵነኔ ዚአከ ያፈርሀኒ ፣
እምኵሉሰ አርምሞ ይኄይስ ወይሤኒ ።

ትርጉም፡-

እውነት ብናገር የዚህ ዓለም ሰዎች ይጠሉኛል ፣
ሐሰትም እንዳልናገር የአንተ ፍርድ ያስፈራኛል ፤
ከዚህ ሁሉስ ዝምታ ይበልጥብኛል ፣ ይሻለኛል ።

ዳዊት አስቀድሞ ይህን ቅኔ ተቀኝቷል (መዝ. 38፡1 ።) በዚህ ሁሉ ውስጥ ዐርፍ ዘንድ ተወኝ ብሎ ለመነ ። ጥቂት የዕረፍት ዘመንን ተመኘ ።

ይቀጥላል

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ጥቅምት 5 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ