የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ዐርፍ ዘንድ ተወኝ (10)

“ለበጎ እንኳ ዝም አልሁ ፥ ቍስሌም ታደሰብኝ ። ልቤም በውስጤ ሞቀብኝ ከማሰቤም የተነሣ እሳት ነደደ ፥ በአንደበቴም ተናገርሁ።” (መዝ. 38 ፡ 2-3 ።)

ማሽላ በእሳት ሲጠበስ ይስቃል ። ነጭ ጥርሱ ይታያል ። የማሽላ መሳቅ ግን እያረሩ ነው ። አንዳንድ ዝምታም በውስጥ እያወሩ ነው ። እውነተኛ ዝምታ እግዚአብሔርን መጠበቅ ያለበት ነው ። ብዙዎች የሆዳቸውን በሆዳቸው ይዘው ፣ ማንም ሳያውቅላቸው አርረው ሞተዋል ። መናገር ባያስፈልግ ኖሮ እግዚአብሔር አንደበትን አይፈጥርም ነበር ። መጽሐፍም አትናገሩ አላለም ። ብዙ ማዳመጥ ጥቂት መናገርን ልመዱ ብሎናል ። ተፈጥሮ ራሱ እንደሚያስተምረን ሁለት ጆሮ አንድ አፍ ተሰጥቶናል ። ከንግግር ብዛት መሳት አይቀርም ። ደግሞም፡- “ተናጋሪ ሰው በምድር ውስጥ አይጸናም” ይላል ። (መዝ. 139፡11።) ወጥተው የቀሩ ሰዎችን አስታውሱ ፣ የጥይት እራት ሆነው በሚኖሩበት ዕድሜ ያለፉትን አሰላስሉ ። ተኳሾች አልነበሩም ፣ ተናጋሪዎች ነበሩ ። ሰዎች የጥይት አረርን በይቅርታ ያልፋሉ ፣ የንግግር አረርን ግን ማለፍ ይቸገራሉ ። ለዚህ ነው፡- “አጥንት የሌላት ምላስ አጥንት ትሰብራለች” የሚባለው ።

ተናጋሪ ሰው በምድር ውስጥ መጀመሪያ በክብሩ አይጸናም ። ብዙ የሚናገር ይናቃልና ። ደግሞም አንደበት የጉልበት መውጫ ነውና የመሥራት አቅሙን በመናገር ይጨርሰዋል ። ሁለተኛው ተናጋሪ የሆነ ሰው አያኖረንም ብሎ ሁሉም ሊቀጨው ይነሣል ። አንዲት እኅት በካንሰር በሽታ ተይዛ ባሏም ፣ ልጇም ፣ ቤተሰቦቿም ሳያውቁ ከስምንት ጊዜ በላይ ለዚህ በሽታ መርጃ የሚባለውን መድኃኒት ወስዳለች ። ፍጹም አቅም አጥታ በወደቀች ጊዜ ግን ሁሉም አወቁ ። ይህች እኅት ዛሬ ሞታለች ። ሞቷን የተቀበሉ ቤተሰቦቿ ሕመሟን የማይቀበሉ መሰላት ። እንዲህ ዓይነት ዝምታዎች ጉዳት አላቸው ። ሰው መናገር አለበት ። “ካልተናገሩ አይገኝ ብልሃቱ ፣ ካልታረደ አይታይ ስባቱ” ይባላል ። ካልተናገርን ፣ ድርግም ስንል አፋችን ሳይቀር መጥፎ ጠረን ያመጣል ። መጥኖ መናገር ፣ የሚናገሩትን ማወቅ ፣ አስቦ መሰንዘር ተገቢ ነው ። በዝምታ ዘመን መናገር ግን ለጥፋት ነው ። ለሰነፎች መናገርም ማባከን ነው ።

ለበጎ እንኳ ዝም የሚባልበት ጊዜ አለ ። ቤታችን ሥርዓት ሲያጣ ፣ መናገራችን እንደ ተራ መለፍለፍ ሲታይ የሚበልጠውን መከፋፋት በማሰብ ዝም እንላለን ። ልጆቻችንን ለማቅናት ስንጣደፍ የትዳር አጋራችን በፉክክር ልጆቹን ወደ ገደል ሲከትት ፣ እኛን ለማናደድ ብሎ ልጆቹን በምግባር ሲያራቁት ያን ጊዜ ዝም እንላለን ። እንዳንናገር ገደብ ፣ እንዳንታመን ስም ሲሰጠን ፣ እኛን ለማድመጥ ጆሮ ሁሉ ዝግ ሲሆን ለበጎ እንኳ ዝም የምንልበት ጊዜ አለ ። የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ሲወድቅ ፣ በዘላለማዊ ነገር መቀለድ ሲጀመር ፣ ያልተማሩ በድፍረት ሲያወሩ ፣ ለሊቁ ጥቅስ ሲጠቅሱ ዝም ብለው የሚያዩ አዋቂዎች አሉ ። አገር ቅርጫ ፣ ቤተ ክርስቲያን የጥቂቶች ዐጽመ ርስት ስትሆን ብንናገር ጠላት ፣ መንገዱን ብናሳይ መናፍቅ እንባላለን ብለው ለበጎ እንኳ ዝም ያሉ አያሌ ናቸው ። ደፋር ደንቆሮ ስንሆን አዋቂዎችን ዱዳ እናደርጋለን ። በአባቶች ፊት ከመስማት መናገር ሲቀናን መካሪዎችን ዝም እናሰኛለን ። ይህችን ዓለም ከክፉዎች ክፋት በላይ የደጎች ዝምታ ጎድቷታል ። ክፋት ራሱን የሚያሳድግ ፣ ከችግኝ ወደ ግንድነት የሚለወጥ ነውና ዝም በማለታችን ብዙ ነገሮች ጠፍተዋል ።

እግዚአብሔርን መጠበቅ የሌለበት ዝምታ እንደ ነቀዝ ውስጥ ውስጡን የሚበላን ፣ እንደ ፍም የሚያጋየን ነው ። ጸሎት የሌለው ዝምታ ፣ ጊዜውን ያልቃኘ ዱዳነት ፣ የምን ቸገረኝ መለጎም በውስጣችን ድንጋጤ እየፈጠረ ይመጣል ። አንድ ቀን የታመቀው ስሜት ይፈነዳል ። ለብዙ ዘመን እነርሱ ብቻ ተናጋሪ የሆኑ ሰዎች አንድ ቀን ዝም ያለው ወገን ሲያፈነዳው መድረሻ ያጣሉ ። በጊዜው ያልተነፈሰ ነገር መጨረሻው ፍንዳታ ይሆናል ። እሳተ ጎሞራው ሲተነፍስ ሙቅ ውኃ ይሆናል ። በሽተኛን ይፈውሳል ። በጊዜው ማረም ከተቻለ እኛም እናርፋለን ፣ ያም ሰው ከስህተቱ ይመለሳል ። እሳተ ጎሞራ ከፈነዳ ግን ተራራን ያቀልጣል ፣ ከተሞችን ያፈርሳል ።

አንዳንድ ሰው በውስጡ ዝም ብሎ ነዶ ያልቃል ። ለበሽታ ይዳረጋል ። “ተናዳጅ እንጂ አናዳጅ አይሞትምና” ዕድሜው ያጥራል ። ሌላው ሰው ደግሞ ይናገራል ፣ ተመልሶ ይበሳጫል ። ብዙዎቻችን ስናገር ይቀለኛል ብለን ዶፉን እናወርደዋለን ። ሰዎቹን ማስደንገጥ እንችላለን ፣ መለወጥ ግን አንችልም ። ኃይለኛ የሆኑ ንግግሮች ቍስልን ከመፈወስ እንደገና እያደሱት ይመጣሉ ። አንድ ቀን ይህ አንደበት እንደሚታሰር በማሰብ እውነትን በፍቅር መግለጥ እርሱ የፈረሰውን ይገነባል ።

ሊቁ እንዲህ ብለዋል፡-

ጥበብ የሌለበት አነጋገር ስንፍና ፣
ማሰብ የሌለበት ዝምታ ድንቁርና ።

ይቀጥላል

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ጥቅምት 24 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ