የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ዐርፍ ዘንድ ተወኝ (12)

“እነሆ ፥ ዘመኖቼን አስረጀሃቸው አካሌም በፊትህ እንደ ኢምንት ነው ። ሕያው የሆነ ሰው ሁሉ በእውነት ከንቱ ብቻ ነው ።” (መዝ. 38 ፡ 5 ።)

አንድ ግጥም ትዝ አለኝ፡-

ሰው አፈር ነው አሉ ታጥቦ የማይጠራ ፣
እድፍ የሞላበት ከጭቃ የተሠራ ፤
ሰው ሸክላ ነው አሉ ድንገት ተሰባሪ ፣
ወድቆ ለመነሣት ምን ይሉኝን ፈሪ ፤
ሰው ሕልም ነው አሉ ታይቶ ማይጨበጥ ፣
ኪዳኑን አፍርሶ በሌላ ሚለውጥ ፤
ሰው ቅጠል ነው አሉ ጠውላጊ ደራቂ ፣
የሱን እልፍኝ ዘግቶ የሰውን አድማቂ ፤
ሰው ዝንብ ነው አሉ ከክፉም ከደጉ ከሁሉ አራፊ ፣
መዘዝን ሰብሳቢ በሽታን ጠላፊ ፤
ሰው እሳት ነው አሉ ለብልቦ ሚያቃጥል ፣
በዓይን ተጋርፎ በግልምጫ ሚጥል ፤
ሰው ጊንጥ ነው አሉ መርዛም ተናዳፊ ፣
በምላሱ ልሶ የሰውን ስም አጥፊ ።

ንጉሥ ዳዊት የዓለምን ከንቱነት ተረድቷል ። እንኳን የሚገዛው አገር የራሱ አካልም ንብረቱ እንዳልሆነ አምኗል። እግዚአብሔር ድሀውን አልዓዛር ብቻ ሳይሆን ባለጠጋውን ሰሎሞንንም ለመንግሥቱ ጠርቷል ። ከፀሐይ በታች ሁሉ ከንቱ መሆኑን የነገረን ንጉሥ ሰሎሞን ነው ። ድሀ ዓለም ከንቱ ነው ቢል ስላላገኘው ነው ይባላል ። ሰሎሞን ግን ጥበብን ለምኖ ሀብትና ሥልጣን የጸኑለት ሰው ነው ። የዓለማችን ትልቁ ምሁር ፣ ትልቁ ባለጠጋ ፣ ትልቁ ንጉሥ ዓለም ከንቱ ነው ሲል የማያምን ማንም የለም ። ዓለም ከንቱ ሁና የምትታየው ላጡት ሳይሆን ላገኙት ነው ። ሲደርሱበት ሁሉም ነገር ባዶ ነው ። በርግጥም ሰው ያለ ክርስቶስ ከንቱ ነው ። ነቢዩ ዳዊት ቤተ መንግሥቱን እንደ ገዳም የኖረበት ትልቅ የእግዚአብሔር ሰው ነው ። ቤተ መንግሥት ሲገባም በገናውን ያልጣለ ፣ በእግዚአብሔር ለመታወቅ ያላፈረ ፣ ሃይማኖት አለው መባልን ያልተሰቀቀ ንጉሥ ነው ፣ በእግዚአብሔር ላይ ያልኮራ ትልቅ ሰው ነው ። ይህ ዳዊት የነገሠ መጨረሻ ሞተ እንደሆነ አረጋግጧል ። ለምለሙ ገላ አንድ ቀን እንደሚጠወልግ ፣ ቆንጆው ቅሪት ሳይኖረው እንደሚረግፍ ተሰምቶታል ።

በርግጥም ያለ እግዚአብሔር የገዛ አካላችንም ፣ መኖሪያ ዓለማችንም ከንቱ ነው ። ሰማይ ባይኖር ኖሮ እንደ ምድር ኑሮ የሚያስፈራ ነገር አይኖርም ነበር ። ቆንጆዎች ለመርገፍ ይቸኩላሉ ። ጀግኖች በትንሽ እንቅፋት ይወድቃሉ ። ዓለም ጠበበን ያሉ ሦስት ክንድ ከስንዝር በምትሆን ሳጥን ይታሸጋሉ ። ሁሉም ሰው ይሸተናል ብለው ይጸየፉ የነበሩ ቶሎ ካልተቀበሩ ይበላሻሉ ይባላል ። ዓለምን በእውቀታችን ፈጠርን ያሉ በብቸኝነት ወደ ጉድጓድ ይጓዛሉ ። እርቅን የጠሉ ከጠላታቸው አጠገብ ይቀበራሉ ። የሚያስተጋቡ የፉከራ ድምፆች በሞት ተግሣጽ ፀጥ ይላሉ ። የድሀውን ጥርስ ያወለቁ እነዚያ ጽኑ ክንዶች “ምን ታመጣላችሁ?” ተብለው በፈትል ይታሠራሉ ። እየነጠሩ መሬት ይረግጡ የነበሩ አፈርን አናታቸው ላይ ዘውድ አድርገው ይተኛሉ ። ቍጣቸው የሚያስፈራ ፣ ጥላቸው የሚያስበረግግ እነዚያ ግርማውያን በመቃብራቸው ላይ እንስሳት ይተፉባቸዋል ። ያለ እኛ ማንም የለም ያሉ ለዘላለም ይተነፍሳሉ ። እነዚያ የተዘፈነላቸው ከብላላ ዓይኖች ይጨልማሉ ። የሰውን አጥንት የሰበሩ ምላሶች ይዘጋሉ ። ለእግዚአብሔር ለመዘመር አሻፈረኝ ብለው ይዘፍኑ የነበሩ አንደበቶች ፣ ወደ ምስጋናው ዓለም ባዶ እጃቸውን ይሄዳሉ ። ሰው ከንቱ ነው ።

ስለ ቀጠሮው እንጂ እቀጠሮው ቦታና ሰዓት ለመድረስ እርግጠኛ ያልሆነ ሰው ባልታሰበ ሰዓት የሚበተን ነዶ ነው ። ጥበብን ችላ ብሎ ገንዘብ ሲሰበስብ የኖረ ወደ ሰማይ ባዶ እጁን ይሄዳል ። ለመብሉ ተጨንቆ ብዙዎችን ያስራበ ለማያውቀው ሰው ሀብቱን ጥሎ ይሄዳል ። ይሳሳለት የነበረው ዕቃው በሚጠላው ሰው እጅ ላይ ይሆናል ። የማያምነውን ቤቱን ዘግቶት ይሄዳል ። ስሜን ያስጠራሉ ያላቸው ልጆቹ በሞተ በሠልስቱ ንብረቱን ስለማውደም ይነጋገራሉ ። ስሙንም በየፍርድ ቤቱ ሲያስነሡት ፣ በሥጋው ጨርሶ በነፍሱ እንዲወቀስ ያደርጉታል ። የሳሳለት ትዳሩን የናቀው ሰው ይወርሰዋል ። ለገዛ ምኞቱ ኖሮ አንድም ረብ ጥቅም ያጣል ። ለማይኖርበት ዓለም ሰብስቦ ወደሚኖርበት ዓለም ባዶ እጁን ይሄዳል ። ይህ ሰው ነው እንግዲህ ለቀጣይ ዓመት የሚጨነቀው ። ለመዋሉ እርግጠኛ ያልሆነው ሰው የሚያከርመኝ ገንዘብ የለኝም ብሎ ይዋትታል ። ተኝቶ ለመነሣቱ ዋስትና ያላጻፈው ሲነጋ እገሌን ገድዬ ይላል ። ሟች ሳለ መግደሉ ይገርማል ። የራሱን ሞት አስቀምጦ በጠላቱ ሞት ይስቃል።

ዘመን ሲያረጅ እጅ ለመጉረስ ፣ እግር ለመራመድ ይከዳል። ዘመን ሲያረጅ ዓይን ለማየት ፣ ምላስ ለማላመጥ ይለግማል ። ዘመን ሲያረጅ ወዳጅ አንሶ ፣ የማያውቀን ሰው ይበዛል ። ዘመን ሲያረጅ እንኳን ባዳው የገዛ አካልም ገሸሽ ይለናል ። አካልም እንደ ኢምንት ይሆናል ። ነቢዩ ይህን አስተዋለና ወደማልመለስበት ሳልሄድ ዐርፍ ዘንድ ተወኝ አለ ። ሞት አይቀርም ። መሰንበት እንጂ በዚህ ዓለም መቅረት የለም ። የምንጠብቃቸው ነገሮች ሊሆኑም ላይሆኑም ይችላሉ ። ሞት ግን አይቀርም ። ባንገዳደልም ሞት መምጣቱ አይቀርም ። ለሞት የቀን ሠራተኛ መሆን አያስፈልገንም ። እኛ የሕይወት መልእክተኞች ነን ።

የሰው ልጅ አስተሳሰቡ ከንቱ ነው ። እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ አእምሮን ካልባረከው እንዲህም ይታሰባል ወይ ? እስኪባል የወረደ ነው ። ሚስት ይዞ ሚስት ያምረዋል ። መኪና እየነዳ መኪና ይከጅላል ። የሚፈልገውንና የሚያስፈልገውን መለየት አልቻለም ። ለእግዚአብሔር ሊኖር ተፈጥሮ ለእልህ ፣ ጠላትን ለማናደድ ይኖራል ። በማይመለስ ጊዜ ላይ ቆሞ ሰዓቱን በዋዛ ፈዛዛ ያባክናል ። በሰማይ በኅብረት እንደሚኖር ረስቶ መለያየትን ይመርጣል ። እባብን እየፈራ እባብ ይሆናል ። ሐሰተኞችን እየጠላ ኑሮውን በውሸት ላይ ይመሠርታል ። ቀይ ባሕርን ተሻግሮ ዮርዳኖስን ይፈራል ። የበላውን ሳይውጥ ሌላ ይከጅላል ። በአንድ አልጋ ላይ ተወስኖ ሊያድር ደሴት ካልገዛሁ ፣ ከተማ ካልገነባሁ ይላል ። ስለ ፀሐይ ሳያመሰግን ሌላ ይከጅላል ። የተቀበለውን ሳያውቅ አዲስ ነገር ይፈልጋል ። ሰው ከንቱ ነው ።

ለሰማይ ተፈጥረን በምድር መቅረት ፣ ለመሻገር ተጠርተን ድልድዩ ላይ ቤት መሥራት በእውነት ከንቱነት ነው ። ያለ ሰማይ የምድር ኑሮአችን ፍርሃት ብቻ ነው ። ወደማንመለስበት ዓለም ሳንሄድ በንስሐ ፣ በአሚነ ክርስቶስ ጥቂት ለማረፍ አሁን እንነሣ። እግዚአብሔር ያግዘን !

ይቀጥላል

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ኅዳር 1 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ