“አንተ ሠርተኸኛልና ዝም አልሁ አፌንም አልከፈትሁም ።” (መዝ. 38 ፡ 9 ።)
“ሸክላ ሠሪው አይቀድመውም” ብሏል ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ። ሸክላ ሠሪ እንዳለው ይናገራል ። የፍጥረት የጸጥታው ጩኸት “እግዚአብሔር አለ” የሚል ነው ። እግዚአብሔር ቀዳማዊ ተብሎ መወደስ ክብሩ ነው ። የመጀመሪያነቱ መነሻ የሌለው ነው ። ከእርሱ በፊትም ማንም አልነበረም ። ከእርሱ በፊት የነበረ ካለ እርሱ የተገኘ ይባል ነበር ። እርሱ ግን የሁሉ አስገኚ ነው ። ከመልካምነቱ ፍጥረትን አስገኝቷልና ፍጥረት መልካም ነው ። ክፉ የሆነ ብናገኝ እንኳ በምርጫው እንጂ በተፈጥሮው ክፉ አይደለም ። “አረም ምንነትዋ ያልታወቀ ጠቃሚ ተክል ናት” የተባለውን ስናስብ አንድም ፍጥረት በከንቱ እንዳልተፈጠረ እንረዳለን ። ራሱንም ወደ ህልውና ያመጣ ማንም የለም ። ፍጥረት ግኝት ነው ። ግኝት ደግሞ በግድ አስገኚ አለው ። እግዚአብሔር ከፍጥረታት አልቆ ሰውን ፈጥሯል ። ከምድር አፈርም አበጅቶታል ። ሰው የተጠገነ ፣ የተሠራ ፣ የተበጀ ፍጥረት ነው ። ሰው አንድ ጊዜ ያለቀ ፍጥረት አይደለም ። መላእክት ፈተናቸውም ትንሣኤያቸውም አንድ ጊዜ ነው ። ሰው ግን በእንደገና ዕድል የሚኖር ነው ።
ሠሪ አለን ። ዓይን ግንባር ላይ ከሆነ ይፈርጣል ብሎ አምባ ውስጥ ያስቀመጣት ሠሪ አለን ። አፋችን ውስጥ የምናስገባው ምግብ መዓዛው እንዲያውደን ፣ መመረዙ ብክለቱ እንዲታወቀን አፍንጫን አጠገቡ የሠራ ሠሪ አለን ። አራቱ ጣታችን ያለ አምስተኛው እንደማይጨብጥ አውቆ አምስተኛ ጣትን የፈጠረ ሠሪ አለን ። ዝናብ ሲመታን ውኃ ዓይናችን ውስጥ እንዳይገባ አድርጎ ቅንድብ የሚባል በረንዳ የሠራ ሠሪ አለን ። ልባችን የሕይወት መውጫ ነውና ከተፀነስንበት ቅጽበት አንሥቶ እስከ ሞት ድረስ እንዲመታ ያደረገ ፣ ልብን ከብረት በጠነከረ ሳንቃ ውስጥ የሸሸገ ሠሪ አለን ። በሁለት እግር እየሮጥን እንዳንወድቅ አድርጎ የፈጠረን ሠሪ አለን ። ልጁ አባቱን ያውቀዋል ። የእኛ ግኝት ዝንጀሮ ሳይሆን እግዚአብሔር ነው ። ካኮራቸው አንቃወማቸውም ፣ እኛ ግን እግዚአብሔር የሠራን ሰዎች ነን ። የተሠራነው በሚራሩ እጆች ላይ ነው ። ከአፈርነት ያሥነሣን የአፉ መሳም የሆነው ትንፋሹ ነው (ዘፍ. 2 ፡ 7) ። ጠቢቡ ይህን ጥንተ ተፈጥሮ የሚያስታውስ ዝማሬ አቅርቧል፡- “በአፉ መሳም ይሳመኝ ፥ ፍቅርህ ከወይን ጠጅ ይልቅ መልካም ነውና ።” (መኃ 1 ፡ 2 ።)
ከጣኦት ቤት የወጣው አብርሃም “አንተ ሠርተኸኛል” ይላል ። በዝሙት ከተማ የመነነው ኖኅ “አንተ ሠርተኸኛል” ይላል ። በምድረ በዳ ትምህርት ቤት የተማረው ሙሴ “አንተ ሠርተኸኛል” ይላል ። ከእረኝነት ቤት ንጉሥ ሆኖ የተቀባው ዳዊት “አንተ ሠርተኸኛል” ይላል ። ክዶ ንስሐ የገባው ጴጥሮስ “አንተ ሠርተኸኛል” ይላል ። እስጢፋኖስ ሲወገር ድገም ይል የነበረው ጳውሎስ “አንተ ሠርተኸኛል” ይላል ። በመንግሥተ ሰማያት የሚበዙት ምሕረት ያገኙ ኃጢአተኞች ናቸው ። ቅዱስ አውግስጢኖስ፡- “የትላንት ስህተት ያልነበረው ጻድቅ ፣ የነገ ተስፋ የሌለው ኃጥእ የለም” ብሏል ። እግዚአብሔር ሠርቶልናል ብለን የምናመሰግነው ብቻ ሳይሆን ሠርቶናል ብለንም የምንዘምርለት ነው ። በርግጥም በሽተኛው ጳውሎስ ዓለምን አሳመነ ሲባል እግዚአብሔር ሥራውን ሠርቶለት ነው ። በዋሻ ይኖሩ የነበሩ ክርስቲያኖች የሮምን ቤተ መንግሥት ሲወርሱ እግዚአብሔር ሥራቸውን ሠርቶላቸው ነው ። ከዚህ ሁሉ በላይ እግዚአብሔር የሠራቸው ክርስቲያኖች በቤተ ክርስቲያን ይገኛሉ ።
መሠራትን መፍረስ ይቀድመዋል ። እግዚአብሔር ሠሪ ከሆነ ፈርሰናል ማለት ነው ። ተሠርተን ከሆነ የፈረስን ሰዎች ነበርን ማለት ነው ። ዛሬ ለወደቀ ስናዝን ለትላንት ማንነታችን እያዘንን ነው ። ለወደቀው ማንነታችንም እግዚአብሔር እንዳዘነለት ምስክሮች ነን ። የዛሬው ታሪካችን ከትላንት መፍረስ የጀመረ ነው ። የሁላችንም ጀርባ ደኅና አይደለም ። እግዚአብሔር ተስፋ ቢቆርጥብን ኖሮ ዛሬን ፣ “ዛሬ” ብለን ለመጥራት አንበቃም ነበር ። የትዕግሥቱ ፍሬዎች ነን ። ስለዚህ በማንም ተስፋ መቍረጥ አይገባንም ። በየቀኑ በአሳባችን የምንፈርስ ነን ። ወተቱን እያጠቆርን ፣ ማሩን እያመረርን ፣ ንጹሑን እየኰነንን የምንኖር ነን ። በገዛ ግምታችን የጠፋን ፣ ከእውነቱ ይልቅ ለተሰማን ነገር ዋጋ እየሰጠን ትዳራችንን ወዳጅነታችንን የምናፈርስ ነን ። እርሱ እየሠራን ፣ ከአሳብ ውድቀት እያነሣን ለዚህ አድርሶናል ። ውስጣችን ቢታይ ከማን ጋር እንኖር ነበር ። የሚችለን እርሱ ብቻ ነውና የኅሊናን ቁልፍ በእኛ በራሱ እጅ አደረገው ። በዚህም ምስጋናው ብዙ ነው ።
እግዚአብሔር በዝምታ ይመለካል ። ውለታው ሲበዛብን ከመዘመር መደነቅ ፣ ከመመስከር ዱዳ መሆን ይወድቅብናል ። ዝምታም ፣ ጸጥታም ለእግዚአብሔር መገዛት ነው ። ካላውካኩ ፣ ሰፈር ካልረበሹ የሚያመልኩ የማይመስላቸው ሰዎች አሉ ። ይህ የባርነት መንፈስ የሚወልደው ነው ። ነጻ የወጣ ሰው ጽሞናን ገንዘብ የሚያደርግ ነው ። የበታችነት ስሜቶች የበላይነት ስሜት ይወልዳሉ ። ይህም በሃይማኖት ስፍራም ይንጸባረቃል ። ነቢዩ የሠራውን ጌታ አሰበና በመደነቅ ጠፋ ። “አንተ ሠርተኸኛልና ዝም አልሁ አፌንም አልከፈትሁም ።” (መዝ. 38 ፡ 9 ።) ወደማንመለስበት ሳንሄድ የእግዚአብሔርን ሥራ እያስታወስን መመሰጥ ያስፈልገናል ። ባፈረሱን ነገሮች ሳይሆን በሠራን እግዚአብሔር ለመደነቅ ጥቂት ማረፍን ያድለን ! እኛ ገና አላረፍንም ፣ የበቀል በትር እየቆረጥን ነው ። የማንበላውን እየሰበሰብን ነው ። አገር አውድመን ቤት እየሠራን ነው ። ሚሊየኖችን አስርበን ሁለት ልጅ እያሳደግን ነው ። ገና አላረፍንም ። እግዚአብሔር ዕረፍትን ያድለን !
ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ኅዳር 10 ቀን 2016 ዓ.ም.