የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ዐርፍ ዘንድ ተወኝ (17)

“መቅሠፍትህን ከእኔ አርቅ ፥ ከእጅህ ብርታት የተነሣ አልቄአለሁና ።” (መዝ. 38 ፡ 10 ።)

ኃያል እጅ ከያዘን ከዚያ ውስጥ ፈልቅቆ መውጣት የማይቻል ነው ። አጉል ትግል እጃችንን ከሚሰብረው እስኪለቀን መጠበቅ የተሻለ ነው ። ከተሸነፉለት ጨካኝ የሚባለው ሰው እንኳ ይራራል። እግዚአብሔር ኃያል ነው ። በቍጣው ከመጣ ማንም አይመልሰውም ። በጉልበት ከወጣ ማንም አያሸንፈውም ። በኃይል ከዘመተ ማንም አይመክተውም ። እርሱ ግን ሲሸነፉለት የሚሸነፍ ፍቅር ነው ። አንዳንድ ነገሮች እንደሆነ እንጂ ለምን እንደሆኑ በቂ እውቀት የለንም ። ችግር ያልሠሩትን ኃጢአት የሚያናዝዝ ነው ። ምን ሠርቼ ይሆን ? እያሉ የሚያማርሩበት ነው ። አንዳንድ ጊዜ ለዛሬው ችግራችን የአስተዳደጋችንን ሁኔታ በማሰብ ወላጆቻችንን እንቀየማለን ። ሌላ ጊዜም የትምህርት ቤት መምህራችን ያለ ጥፋታችን ስለ ቀጣን ለዚህ ሁሉ የተዳረግን መስሎ ይሰማናል ። በተፈጥሮዬ ችግር ሳይኖርብኝ አይቀርም ። እኔ ስወለድ ጀምሮ የተረገምሁ ነኝ በማለት ብዙ መላ እንመታለን ። ሥጋችንን ከስረን ነፍሳችንን ለማትረፍ ስንነሣ ደግሞ መልሰን በኃጢአት እንወድቃለን ። በሚያዳልጥ ስፍራ እንደሚሮጥ ሰው ደጋግመን መውደቅ ይሰለቸናል ። እኛ ለተሸከምነው ጓደኞቻንን ስለ ችግራችን እናፍራለን ። የቤታችን ገመና የታየ እየመሰለን ከመጠን በላይ ተሽቀርቅረን እንወጣለን ። የቤቱን ቅባት ዘቅዝቀን እንቀባለን ።

ልጆቻችን የጎዱንን ፣ በመሥዋዕትነት አሳድገናቸው በጭካኔ ዓይን ያዩንን ለማን እንደምናወራው ምጥ ይይዘናል ። ለፍቶ መና የመሆን ስሜት ያንገላታናል ። ጤናችን እንደ ማታ ጀምበር እያዘቀዘቀ ሲመጣ ከመታመማችን “ማን ያስታምመኛል?”ሰ እያልን እንፈራለን ። ማራኪ ፈገግታችን ከራቀ ዓመታት ተቆጥረው ይሆናል ። አገር እንደ በድን ሆኖ እየታየን መብረር መጥፋት ያምረናል ። ጥቂት ቀን እንኳ ለማረፍ ፈልገን እርሱም እንደ ሰማይ መራቁ ፣ እንደ አድማስ መወርወሩ ግራ ይገባናል ። ለዚህ ያበቃኝ የትዳሬ ተጽእኖ ነው ፣ የፖለቲካው እድፈት ነው እያልን ብዙ ማመካኛ እንፈልጋለን ። የካብነው ሁሉ እስከ መሠረቱ የተናደ እየመሰለን የመሞከር ተስፋችን ይሟጠጥብናል ። ልባዊ የሆኑ ወዳጆች ትላንት ላይ እንጂ ዛሬና ነገ ላይ አልታይ ሲሉን ጭልም ይልብናል ። መንገዶች ሁሉ ወደ ፍላጎታችን እንደማያደርሱን ሲሰማን ከመጀመሪያው ለመጀመር እንፈልጋለን ። የኖርነውን ኑሮ ግን በዜሮ ማባዛት እንቸገራለን ።

ሁሉም ነገራችን ያለቀ መስሎ ይሰማናል ። እግራችን ደኅና ቢሆንም ለመራመድ የዛለ ፣ ለመቆም የሰለለ መስሎ ይሰማናል ። ጉንፋንን በካንሰር ልክ ፣ ሳልን በሞት ሠረገላነት እናየዋለን ። ደቃቁ ነገር እኛ ጋ ሲመጣ ተራራ ሆኖ ይታየናል ። አለማመን ረቂቁን ተራራ ሲያደርገው ፣ ማመን ደግሞ ተራራውን ደልዳላ ሜዳ አድርጎ ያየዋል ። አንድ ቀን ባደርን ቍጥር ጉልበትና የማስታወስ አቅም እየደከመ ይመጣል ። በዚህም ፈሪ እንሆናለን ። እግዚአብሔር ሰብሮኛል ማንም አይጠግነኝም የሚል ኀዘን ውስጥ እንጠመቃለን ። አእምሮአችንም እውቀትን ለመቀበል ይሰንፍብናል ። ትምህርቶች የቅንጦት ወሬ ይሆኑብናል ። ችግር ላይ በማፍጠጥ ችግር እንደማይወገድ እንዘነጋለን ። ጨለማን ቁራጭ ሻማ እንደሚያሸንፈው ረስተን ለጨለማው እናዜማለን ። መርሳት እየደጋገመ ያላግጥብናል ። እየቀለዳችሁ ነው ወይ ? እስክንባል የቅርብ ክስተቶችን ሳይቀር እንረሳለን ። ችግሩ የፈጠረብን ጭንቀት የአእምሮ ብቃታችንን ይጋፋዋል ። በግዴለሽ ሰው እንቀናለን ። አንዳንድ ጊዜም በዓለማውያን ሳይቀር ምነው እንደ እነርሱ በሆንኩኝ እንላለን ። እነርሱ ደግሞ በእኛ ኑሮ ይቀናሉ ።

ጸሎት ርቆኛል የምንልበት ጊዜ ጥቂት አይደለም ። “በእግዚአብሔር ፊት ወድቄ ምን እንዳወራሁ ሳላውቀው እነሣለሁ ፣ አንዳንዴ ዝም ብዬ እቆያለሁ ። ለመጸለይም ቃላትና ጉልበት አጥቻለሁ ። አንዳንድ ጉዳዬ ስጸልይ እየባሰ መጣ እንጂ ምንም ለውጥ አላገኘሁም” በማለት ጸሎትን ለመተው እንዳዳለን ። ወደ እግዚአብሔር ቤት በመሄድ የውሸት ፈገግታ የምንሰጥ እየመሰለን መቅረትን እንመርጣለን ። አገልጋዮቹን እንቀየማለን ። ለሌላው ችግር ሲሮጡ የእኔ ነገር ምንም አይሰማቸውም እንላለን ። እዚህ ነኝ ለማለት ስልክ አጥፍተን ለምን አልፈለጉኝም? በማለት ድብብቆሽ እንጫወታለን ። ሁለመናችን ያለቀ መስሎ ይሰማናል ። ከዚህ በኋላ የምንመኘው ቢሆን እንኳ ልብሱ በየትኛው ገላ ይለበሳል ? ትምህርቱ በየትኛው ጭንቅላት ይያዛል ? አገልግሎቱ በየትኛው አትሮኖንስ ይቀጥላል እንላለን ። ኑሮን መኖር ስላቃተን ሞትን የምንኖርበት ጊዜ አያሌ ነው ።

ሽሮና በርበሬ አለቀብኝ ማለት እንኳ ያሳቅቃል ። ራሴ አልቆብኛል ማለት ከባድ ነው ። የምናምነው ጌታ ግን ሞትን ልደት ፣ መቃብርን ሰርግ ማድረግ የሚችል ነው ። እንኳን በሰዎች ላይ በራሳችን ላይ የሚከናወነውንም ምክንያቱን ማወቅ አንችልም ። እግዚአብሔር አምላክ ነውና ለእኛ ዝርዝር ምክንያት ማቅረብ አይጠበቅበትም ። አንዱ በችግር ሌላው በምቾት በሚሰቃይበት ዓለም ላይ ነን ። እኛ አርባ ኪሎ ሜትር ለመጓዝ ገንዘብ የለንም ። ከምድር ዳር እስከ ምድር ዳርቻ በጭንቀት የሚጓዙ ፣ ምድር የጠበባቸው ሀብታሞች አሉ ። የእነርሱን ስቃይ ማግኘት አይፈውሰውም ። በዚህ ዓለም ላይ የሌለውና ኖሮት እንደሌለው የሚሰማው ሁለት ዓይነት ረሀብተኞች አሉ ። ብቻ የድሀ ደስታው ቅርብ ነው ። ባለጠጎች ሳቅን ይገዛሉ ፣ ድሆች በዕለት ሲሳይ ይደሰታሉ ። መኖር ፈልገው የሞቱ አሉ ፣ ሞትን እየለመንን መኖራችን ሊደንቀን ይገባል ። በዚህ ሁሉ ውስጥ ታዲያ እንደ ዳዊት “መቅሠፍትህን ከእኔ አርቅ ፥ ከእጅህ ብርታት የተነሣ አልቄአለሁና” እንላለን ። (መዝ. 38 ፡ 10 ።) እያጉረመረምንም ከእግዚአብሔር ቤት አለመለየት መልካም ነው ። ወላጆቹን ስለ ዱላቸው ሲወቅስ የነበረ ወጣት ሲወልድ ዱላቸው ፍቅር መሆኑ ይገባዋል ። ወላጆች ለጥፋታችን አይተዉንም ። የእግዚአብሔር ዱላ ፍቅር መሆኑ የሚገባን ቆይቶ ፣ በእምነት ስንጎለምስ ነው ።

ደግሞም ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በልደት ተፈጥሮ ፣ በሰማዕትነት ጽዋ መግባት ግድ ነው ። ሰማዕትነቱ ይለያይ እንጂ ሁላችንም በበሽታ አሊያም በፈተና እያለፍን ለሽልማት እንበቃለን ። አማኑኤል ሆይ የሚሆንብኝ አልገባኝም በእውቀትህ አድነኝ !

ይቀጥላል

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ኅዳር 12 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ