መግቢያ » መጽሐፍ ቅዱስ » ብሉይ ኪዳን » መዝሙረ ዳዊት » ዐርፍ ዘንድ ተወኝ (19)

የትምህርቱ ርዕስ | ዐርፍ ዘንድ ተወኝ (19)

“አቤቱ ፥ ጸሎቴን ስማ ፥ ጩኸቴንም አድምጥ ፥ ልቅሶዬንም ቸል አትበለኝ እኔ በምድር ላይ መጻተኛ ነኝና ፥ እንደ አባቶችም እንግዳ ነኝና ።” (መዝ. 38 ፡ 12 ።)

እግዚአብሔር ልመናን የሚሰማ አምላክ ነው ። በሰው እጅ የተያዙ ሰዎችን እናውቃለን ። እየተማጸኑአቸው ይገድሏቸዋል ። ሰው ልመናን አያከብርም ። በተለመነ ቍጥር እየደነደነ ይመጣል ። ራሱን ትልቅ ፣ ያንን ሰው መላ የለሽ ያደርገዋል ። ልመናን ለመቀበል ውስጣዊ ጆሮ መከፈት ፣ ድንጋዩ ልብ መፈርከስ አለበት ። እየለመኑን ጥለን የሄድናቸው ብዙ ወገኖች አሉ ። ይቅርታችንን እየተማጸኑ ከሕሊና እስር ሳይፈቱ ያለፉ ብዙ ሰዎች አሉ ። ልመናን መስማት እግዚአብሔር እኔንም ሰምቶኛል ብሎ መመስከር ነው ። ባለውለታችን የሆነውን እግዚአብሔር የት አግኝተን እንጋብዘዋለን ? የት አግኝተን ፍቅራችንን እንገልጥለታለን ? እርሱ የመከረኛ ልጆቹን ስቃይ ዛሬም ተሸክሟል ። ከረሀብተኞች ጋር ረሀብተኛ ፣ ከስደተኞች ጋር ስደተኛ ነው ። በድሆች ላይ በተዘጉ በሮችና ድንበሮች ያዝናል ። ዛሬም መስቀሉን እንደ ስምዖን ቀሬና ተቀብለን ትንሽ ልናሳርፈው እንችላለን ። የወደቁ ሕፃናትን በመሰብሰብ ፣ የተረሱ አረጋውያንን በማስታወስ ቍስሉን ማጠብ ይቻላል ። ክርስቶስ ዛሬም በምድር አለ ። በቅምጥሎች ቤት ሳይሆን በምስኪኖች ጉረኖ ወድቋል ። ዓለም በየትኛውም አቅርቦትዋ ልትሰጠን የማትችለውን ደስታ ከአንድ ጎስቋላ ጋር በማሳለፍ ማግኘት ይቻላል ። ደስታ ሩቅ አይደለም ። ደስታ ውሳኔ ነው ።

እግዚአብሔር ጩኸትን የሚሰማ አምላክ ነው። የጩኸት ድምፆች ሲሰሙ አንዳንዶች ይደርሳሉ ። የሚደርሱት ወገኖች የመጀመሪያዎቹ ወሬ ሊያዩ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ በእጃቸው ያለውን መፍትሔ ለመስጠት ነው ። የጩኸት ድምፅ ሲሰሙ የሚፈሩና የሚሸሹ አሉ ። ስገላግል ብጎዳስ  ብለው ደግሞም ምስክር ተብዬ በየፍርድ ሸንጎው እንገላታለሁ በማለት ሽሽት የሚመርጡ አያሌ ናቸው ። የጩኸት ድምፅ የሚያራራ ነው ። እገሌ ይስማኝ ተብሎ የሚመረጥ ሳይሆን ሰው የሆነ ይርዳኝ የሚል የመሸነፍ ድምፅ ነው ። ጸሎት ቍርጥ ልመና ላይ ደረሰ የሚባለው ጩኸት ሲሆን ነው ። ከዚህ በላይ የመሸከም አቅም የለኝም የሚለው አማኝ ጩኸት ያሰማል ። ሰዓቱን የሚያውቅ እግዚአብሔር ይደርሳል ።

“ወንድ ልጅ ካለቀሰ እግዚአብሔር ይለመናል” ይባላል ። ፍጹም ካልተሸነፈ በቀር ወንድ ልጅ ሊያለቅስ አይችልም ተብሎ ይታሰባል ። በርግጥ የሚያለቅስ ወንድ ሁሉ እውነተኛ ነው ማለት አይደለም ። የአባይ(ሲነበብ ላላ ይደረግ) እንባ ባቄላ ፣ ባቄላ ያህላል ይባላል ። አባይ ማለት የሚያብል ውሸታም ማለት ነው ። ምስክሩ ፣ ጠበቃው እንባ ስለሆነች ያለቅሳል ማለት ነው ። እንባ ግን ልዩ ቋንቋ ነው ። የእንባን ቋንቋ አፍ ያልፈታ ልጅ ፣ አንደበቱ የማይናገር ዲዳ የሚጠቀሙት ነው ። እንባ ዓለም አቀፍ ቋንቋ ነው ። ከቋንቋ በላይ የሆነ ጉዳይ ሲገጥም እንባ ይወርዳል ። እንባ የታላቅ ደስታ ፣ የታላቅ ኀዘን መግለጫ ነው ። ንጉሥ ዳዊት ያለቅስ ነበር ። በቤተ መንግሥትም ልቅሶ ነበረ ። በትልልቅ ቤት ውስጥ ያለውን ልቅሶ እግዚአብሔር ብቻ ያውቀዋል ። ኑሮ ከፍ ባለ ቍጥር ጥያቄውም ከፍ እያለ ይመጣል ። ንጉሥ ዳዊት ያለቅስ የነበረው ወደ እግዚአብሔር ነው ። ወደ ሰው ቢያለቅስም ማንም አያምነውም ነበር ። ለፍጥረቱ እኩል ዓይን ያለው እግዚአብሔር ግን ያዝንለታል ። አንድ ሚሊየን የቸገረውን ሀብታምና አንድ ብር የቸገረውን ድሀ በፍቅር የሚሰማ እግዚአብሔር ብቻ ነው ።

ንጉሥ ዳዊት ሺህ ዓመት ንገሥ እየተባለ በየቀኑ ሲወደስ የሚኖር ቢሆንም እርሱ ግን በዚህ ምድር እንግዳ እንደሆነ ይሰማው ነበር ። ሺህ ዓመት ይንገሡ ሲባሉ ሺህ ዓመት የሚነግሡ የመሰላቸው ብዙዎች ናቸው ። ንጉሥ ዳዊት ግን መጻተኛ መሆኑን አውቆታል ። አንዱ ከደሳሳ ጎጆ ፣ ሌላው ከቤተ መንግሥት ሬሳው ይወጣል ። የልቅሶ ብዛት ፣ የሥነ ሥርዓት ጋጋታ የመለሰው ሟች የለም ። ሁሉም በድንጋይ ይዘጋል ። ኃያልነት ያበቃል ። ከእግዚአብሔር የተወዳጀ ነፍሱን ያተርፋል ። እንግድነት ምንድነው ? ብለን መጠየቅ አለብን ። እንግዳ ለሚያየው ለሚሰማው አዲስ ነው ። በእንግድነት ዓለምም ያልጠበቅነውን ነገር እናያለን እንሰማለን ። እንግዳ ቤቱ ሌላ ስፍራ ነው ። ሰውም መኖሪያው ሰማይ ፣ መቆያው ምድር ነው ። እንግዳ ፊት ፊት እያየ የሚኖር ነው ። ሰውም በምድር ላይ ሰውን ፈርቶ የሚኖር ነው ። እንግዳ ቢሰነብት እንጂ መሄዱ አይቀርም ። ሰውም ምንም ዘጠና ፣ መቶ ዓመት ሞላው ቢባል መሞቱ አይቀርም ። ሰው እንደ ነዋሪና እንደ እንግዳ ሲኖር ጠባዩ ይለያያል ። እንደ እንግዳ የሚኖር ቅዱስ ፍርሃት ይገዛዋል ። እንደ ልቡ መራመድ ፣ እንደ ልቡ መናገርን ይፈራል ። አባቶች ሁሉ እንግዳ ነበሩ ። ልጁን እየተካ የሄደ እንጂ የቀረ ማንም የለም ። እግዚአብሔር ከፈቀደላቸው ጥቂት ሰዎች በቀር ብዙዎች በራሳቸው የዘር ሐረግ እንኳ ስማቸው ተረስቷል ። የዓለም ታሪክ የሚባለው የጥቂት ሰዎች ታሪክ ነው ። እነዚያ ባለ ሕንፃዎች ዛሬ የሉም ። እነዚያ ድምፃውያን ዛሬ አያዜሙም ። እነዚያ ፈላጭ ቆራጮች ስማቸው እንጂ ግርማቸው የለም ። አዎ እንደ አባቶቻችን እንግዶች ነን ። ጥቂት በክርስቶስ እናርፍ ዘንድ እምነትን እንለምናለን ።

አሜን!

ይቀጥላል

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ኅዳር 17 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ

አዳዲስ መጻሕፍት

ትርጉሙ:- ቀይ ዕንቈ

ለምድራችንና ለአገልግሎታችን በረከት የሆነ መጽሐፍ
የመጀመሪያ እትም ጥቅምት 2016 ዓ.ም

1ኛ ጢሞቴዎስ ትርጓሜ – ክፍል አንድ

የመጀመሪያ እትም ሐምሌ 2013 ዓ.ም

ምክር አዘል መጽሐፍ

የመጀመሪያ እትም