የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ዓለምና ሥጋ

 አባ ኢሳይያስ እንዲህ አለ፡- የእግዚአብሔር ጠላት ያደርጉሃልና በዚህ ዓለም ላይ ያለን ነገር ሁሉ የሥጋን ረፍት ጥላ ። ላት ያለው ሰው ከጠላቱ ጋር እንደሚዋጋ እኛም ልክ እንደዚሁ ሥጋ ረፍት እንዳያገኝ ልንቃወመው ይገባል ።” (አባ ኢሳይያስ ፣ የምነና ንግግሮች ፣ 26)
“ግመል ተራራ አጠገብ እስክትደርስ ትልቅ ነኝ ብላ ታስባለች” ይባላል ተራራው ግን ትንሽ መሆኗን ያሳውቃታል ተራራው በመናገሩ ሳይሆን በዝምታው ትልቅ መሆኑን ይናገራል ግመልም በዝምታ ተምራ ትንሽ መሆኗን ትገነዘባለች በቅድስና የበረቱ አባቶች ጋ እስክንደርስ ቅዱሳንን የሆንን ይመስለናል ብዙ ቸርነት የሚያደርጉ ሰዎችን እስክናይ ድሆችን የረዳን መስሎ ይሰማናል ከሁሉ በላይ ወደ እግዚአብሔር ስንቀርብ ራሳችን ያንስብናል ይህ ማነስ ግን የሚያሰቃየው የበታችነት ስሜት ሳይሆን ደስታ የሚሰጠው ፣ ራስን በትክክል የሚያሳውቀው ትሕትና ነው የእግዚአብሔር ወዳጅ መሆን ማለት ወደ እግዚአብሔር መቅረብ ነው የመንግሥተ ሰማያትን ደስታ ስናስብ በትንንሽ መልካም ሥራዎች አንረካም ነበር የገሀነመ እሳት ቅጣትን ብናስተውል በኃጢአት አንጫወትም ነበር ብቻ ከእግዚአብሔር መራቅ ማለት የእግዚአብሔር ጠላት መሆን ማለት ነው ጠላት የሆኑ ሰዎች አጠገባችን መድረስ አይፈልጉም ፤ ክፋታቸው ግን እንዲደርሰን ይፈልጋሉ ከተራራው ሩቅ ያለ ረጅም የሆነ ይመስለዋል ከእግዚአብሔር የራቀም ትዕቢተኛ ይሆናል
በዓለም ላይ ብዙ ነገሮች ተንሰራፍተዋል አለማመን ወይም ሃይማኖት የለሽት የምሁርነትና የዘመናዊነት መገለጫ ሆኗል በእግዚአብሔር የሚያምኑ ሰዎች ዕለት ዕለት እየተገፉ ነው ትሑታን ምስኪኖች ፣ አፍቃሪዎችም ስስ ልብ ያላቸው ተደርገው ተስለዋል በእግዚአብሔር ውስጥ የተሸሸገና በሃይማኖቱ ቀናዒ የሆነ ሰው አእምሮ በሽተኛ አሊያም የአካባቢውን ደስታ እንደሚያደፈርስ ይቆጠራል
ዓለሙ እውነትን በዲፕሎማሲ ተክቷል ባትወደውም እወድሃለሁ በል እያለ ያማክራል ይህ በእግዚአብሔር ቤት ሳይቀር የሚጠላሉ ሰዎች “በክርስቶስ ፍቅር እወድሃለሁ” ይባባላሉ ፍቅር በጥርስ ተተክቷል ነጭ ጥርስ እየበዛ ነጭ ልብ ግን እያነሰ ነው ሰው ከልቡ ጋር የተጣላበት እንደዚህ ያለ ዘመን የለም በጨለመ ልብ ፈገግ የሚሉ ሰዎች በዝተዋል እውነትነት የሌለው ፈገግታ ኃይል የለውም ሰጪውን ሲያደክም ፣ ተቀባዩን አይፈውስም እማሆይ ትሬሣ፡- “እርስ በርሳችን ስንገናኝ በፈገግታ እንገናኝ ፤ ፈገግታ የፍቅር መጀመሪያ ነውና” ያሉትን እዚህ ማስታወስ ይገባናል ቸርነት በቃላት ተተክቷል ለድሆች ምርጥ ቃላት ምርጥ ምግብ አይሆኑም ረሀብ ከንግግር ተግባርን ይፈልጋል ታማኝነት በመተጣጠፍ ተተክቷል የተሻለ ገቢ እንጂ የተሻለ ፍቅር የዘመኑን መስፈርት አያሟላም ሰዎችን በስፍራቸው ማግኘት እየቸገረ አብዛኛው ሰው ከቦታው እየተነሣ ነው ብዙ ባዶ ወንበሮች የሚታዩን ፣ መፍትሔ ፍለጋ ሄደን ፍርድ አጥተን የምንመለሰው ታማኝነት ስለ ጠፋ ነው ታማኞች ደረቆች ፣ ተጣጣፊዎች ዘመን የገባቸው ተደርገው መታሰባቸው ያሳዝናል ታማኝነት እየወረደ ሲመጣ ሰው ለራሱም መታመን ያቅተዋል ያለኝ ይበቃኛል በመስገብገብ ተተክቷል ሁሉን ለእኔ እንጂ ለወንድሜ የሚል የለም ማኅተማ ጋንዲ፡- “ለሰው ልጅ የሚበቃ ሀብት በምድር ላይ አለ ፣ ለሰው ልጆች መስገብገብ የሚበቃ ሀብት ግን የለም” ብለዋል
ትሕትና በራስ በመተማመን ተተክቷል ትሕትና በእግዚአብሔር ተማምኖ መቆም ነው በራስ መተማመን አምላክ የለሽ ያደረጋቸው ሰዎች አሉ ፣ የእግዚአብሔርን ትእዛዛት እንደ ክልከላና መብት ተጋፊነት የሚቆጥሩ ብዙ ናቸው መሰበክ የለብንም ፣ ስብከት በሰው ላይ ጫና ማሳደርና እኔ ልምረጥልህ ማለት ነውና በሕግ መከልከል አለበት የሚሉ እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል ጸሎትም በእምቅ ኃይል ተተክቷል ዘመናዊው ዓለም በውስጥህ ያለውን እምቅ ኃይል ተጠቀም እንጂ በጸሎት ወደ እግዚአብሔር መቅረብ አስፈላጊህ አይደለም ይላል ይህ እምቅ ኃይል ግን የሰውን ልጅ ራሱን እንዳይገዛ ፣ ተስፋ እንዲቆርጥ አደረገው እንጂ የብርታትን ስሜት አልሰጠውም ኅብረት በግለኝነት ተተክቷል ሁሉም ነገር ግላዊ እየሆነ ከመጣ ሰንብቷል የግል ቤት ፣ የግል ኢሜል ፣ የግል ስልክ ፣ የግል ሐኪም ፣ የግል ሥራ ፣ የግል አማካሪ ፣ የግል ሰባኪ የሚሉ ድምፆች እየበዙ ነው ሕግም ላለመነካካት እንጂ ለመረዳዳት አልጠቀመንም በእኛ አገር ደግሞ ላለመነካካት ሕግ ፣ ለመረዳዳት ሰብአዊነት እያጣን ይመስላል
ዓለሙ ማለት ፈጽሞ የማይክድ ፈጽሞ የማያምን ነው ዓለሙ መንፈሳዊውን ነገር በሥጋዊ ፣ የእግዚአብሔርን በሰው ሠራሽ ነገር ተክቶ የሚጽናና ነው ከዚህ ዓለም መራቅ ያስፈልጋል ከመልክአ ምድሩ ሳይሆን ከአስተሳሰቡ መለየት ግድ ይለናል ከዓለም መውጣት አንችልም ፣ ዓለምን ግን ከልባችን ማስወጣት እንችላለን ጌታችን በሐሙስ ማታ ጸሎቱ ከክፉ እንድትጠብቃቸው እንጂ ከዓለም እንድታወጣቸው አልለምንምአለ ዮሐ. 17፡15 የዓለም ወዳጅ መሆን የእግዚአብሔር ጠላት ያደርጋል
የሥጋ ዕረፍት የጠላት መግቢያ በር ነው ሔዋን ብቻዋን ደግሞም ሥራ ፈትታ ሳለ ሰይጣን ፈተናት ሥራ ስንፈታ ለሰይጣን ፈተና እንመቻቻለን ሰንበት የምንለውም የሥጋ ዕረፍት የነፍስ ግን የሩጫ ዕለት ነው ሥራ ፈትነት በምንም መንገድ አይበረታታም በቀን ውስጥ ሮጠን ሮጠን እንቆማለን ፣ ደክመን ደክመን እንቀመጣለን ፣ ውለን እንተኛለን በየዕለቱ የሥጋ ዕረፍት አለን ስንቀመጥ ፣ ስንቆምና ስንተኛ የደከመው ሥጋችን እንደገና ይታደሳል ሥጋ በማያቋርጥ መታደስ ይኖራል ማረፍና ሥራ መፍታት ሰፊ ልዩነት አላቸው ሥራ ስንፈታ እንኳን በሰው እጅ ያለውን በእግዚአብሔር ሥልጣን ያለውን ነገር መፈለግ እንጀምራለን ሥራ ስንፈታ ያለንን ትተን የሌለንን እንከጅላለን ሥራ ስንፈታ የተከለከሉ ነገሮችን መፈለግ ውስጥ እንገባለን ሥራ ስንፈታ አጉል ባልንጀሮችን ፊልምና አሳች መጻሕፍትን እንወዳጃለን ሥራ ስንፈታ ከትዝታችን ጋር መጨዋወት እንጀምራለን ሥራ ስንፈታ ሁሉም ነገር አሰልቺና አድካሚ ይሆንብናል ሥራ ስንፈታ ከሰዎች ጋር ግጭት ውስጥ እንገባለን ሥራ ስንፈታ በሰው ነገር ውስጥ ገብተን ማዘዝ እንጀምራለን ሥራ ስንፈታ ሐሜትን እናሰራጫለን ሥራ ስንፈታ እንከን እየፈለግን መሳደብ እንከጅላለን ሥራ ስንፈታ አእምሮአችንን በነገር እንሞላለን ሥራ ስንፈታ የካብነውን እንንዳለን ሥራ ስንፈታ በሱስ እንያዛለን ሥራ ስንፈታ ዘዋሪና ወሬ አመላላሽ እንሆናለን ሥራ ስንፈታ ብስጩና ተጨናቂ እንሆናለን ጫማችንን በመጥረግም ፣ ቤታችንን በማጽዳትም ቢሆን ሥጋችንን መወጠር አለብን ሥጋ አርነት ካገኘ አይቻልም ለዚህ ነው ሐዋርያው፡- ነገር ግን ለሌሎች ከሰበክሁ በኋላ ራሴ የተጣልሁ እንዳልሆን ሥጋዬን እየጎሰምሁ አስገዛዋለሁ ያለው 1ቆሮ. 9፡27
ሥጋችን ዕረፍት እንዳያገኝ ከምንጥርበት መንገዶች አንዱ በቂ እንቅልፍ ማግኘት ነው እንቅልፍ እንቢ ሲለን የምናስባቸውን አሳቦች አስታውሱ እንቅልፍ ትልቅ ጸጋና ከአሳብ መገላገያ መሆኑን መረዳት እንችላለን በቂ እንቅልፍ ፣ በጊዜ ተኝቶ በጊዜ መንቃት አንዱ ባሕላችን ሊሆን ይገባዋል ይልቁንም ጨለማና ብርሃን ሲታገሉ እኛ ሜዳ እንዳንሆን ማልደን መንቃት ቀኑን በብርታት ለመዋል በጣም ይረዳናል የጸሎት ዲሲፕሊን ያስፈልገናል በሰዓት የተወሰነና የተለካ የጸሎት መርሐ ግብር ያሻናል ጸሎት ዲስፕሊን ከሌለው አይዘልቅም አንዳንድ ሰው በጠዋትና በማታ የጸሎት ሰዓት አለው ሌሎችም በቀን ሰባት ጊዜ ያህል በእግዚአብሔር ፊት ይቆማሉ ሥጋችንን ከከንቱ ዕረፍት የምንታደገው በመጸለይ ነው የማያነብ ሰው አእምሮውን ለማይረቡ ጥያቄዎች አሳልፎ የሚሰጥ ነው አሳብ እንደ ቀበዝባዛ በግ ቶሎ ይጠፋል መላሹ ግን ንባብ ነው የቀኑ ክፋት ካነበብን ንባቡ ላይ ሲያርፍ ካላነበብን እኛ ላይ ያርፋል ሥጋን ዕረፍት የለሽ የምናደርገው ሥራችንን በመሥራት ነው የሥራን በረከትነት የምናውቀው ሥራ የፈታን ቀን ነው ሰው በምንም መንገድ መወጠር አለበት የሥራ ጥቅሙ ደመወዙ ሳይሆን ሥራ አለኝ ብሎ ከቤት መውጣቱ ነው የሚበዛውን ንጹሕ ሰዓት የምናሳልፈው በሥራ ቦታችን ነው ቤታችን በድካም የምንገባበት ነው ስለዚህ የሥራ ቦታችንን ንጹሕ ማድረግ ደግሞም አብረውን ከሚሠሩት ጋር በተቻለ መጠን ሰላም መሆን ይገባናል ሥራችንን በአግባቡ ስንሠራ የአእምሮ እርካታ እናገኛለን እግዚአብሔር ሰነፍ ልጆች የሉትም
ሥጋችንን ከከንቱ ዕረፍት የምናወጣው ለቤተሰባችን ጊዜ በመስጠት ነው ይበልጥ ልጆች ከእኛ ጋር የሚኖሩት ለተወሰነ ጊዜ ነውና እነዚህን እንግዶች ባሉበት ዘመን ጊዜ መስጠት ተገቢ ነው ከቤት ባይወጡ እንኳ የልጅነት ጣዕማቸውን ሊያጡ ይችላሉና በሕፃንነታቸው ጊዜ መስጠት መልካም ነው ልጆች ሲወጥሩን ብንጠላውም ከሰጠናቸው የሰጡን እንደሚበልጥ ማሰብ ይገባናል የታመሙትን ፣ የታሰሩት መጠየቅ ጊዜን ክቡር ያደርጋል ስፖርት መሥራት ፣ ተፈጥሮን እየተዘዋወሩ ማድነቅ ሥጋን ከከንቱነት ይታደገዋል ብዙ ሰው ካለበት ከተማ ወጥቶ መዝናናት እንደማይችል እያሰበ ይበሳጫል ፀሐይ ስትወጣና ስትገባ ያለውን ውበት ለመመልከት የትም መሄድ አያስፈልግም ስንቶቻችሁ ናችሁ ጀምበር ስትወጣና ስትገባ ለማድነቅ ጊዜ ያላችሁ ከንቱ ጊዜዎችን መዋጋት ፣ ሁሉንም ነገር በተለካ የጊዜ ሰሌዳ ማከናወን አስፈላጊያችን ነው
ጸሎት
በልደት ወደዚህ ዓለም ያመጣኸኝ ፣ በዳግም ልደትም የመንግሥትህ ባለሟል ያደረግከኝ ሠሪው እግዚአብሔር ሆይ አመሰግንሃለሁ በጨካኞች እየቀናሁ ርኅራኄን እየነቀፍሁ ፤ በንፉጎች እየተሳብሁ በድሆች ሬሳ ላይ እየኖርሁ ነውና እባክህ ይቅር በለኝ ዓለም የራስዋ ልታደርገኝ ትታገለኛለች እንደ መንፈሳዊ ለመኖር ተጠርቼ እንደ ሰው እየተገለጥሁ ነውና እባክህ አስበኝ የዓለም ዝናም ውርደትም ሁሉም እንዳይገርመኝ የምትመጣዋን መንግሥትህን አሳስበኝ እኔ ላንተ ብሆን ከመባከን እድናለሁ ፣ ካንተ ይልቅ እኔ እጠቀማለሁ እባክህን የራስህ አድርገኝ ለጮኸ ውሻ ሁሉ ድንጋይ አይነሣም የፎከረ ሁሉም አይገድልም ፣ የጠበቁትም በዓለም ላይ አይሆንም ያንተን ፣ ያንተን ብቻ ማሰብና ማረፍ ይሁንልኝ እኔ ስፈርድ አንተ ዝም ትላለህና የቅን ፍርድህ ተጠባባቂ አድርገኝ እንደገና ሠርተህ ለክብርህ አቁመኝ ዓለምንና ሥጋን ባንተ ኃይል እክዳለሁ በተሰቀልከው መድኅን አምናለሁ ለዘላለሙ አሜን
የበረሃ ጥላ 25
ጥቅምት 5 ቀን 2012 ዓ.ም.
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ