የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ዓለም ሁለት ነው

“ስለዚህ ምድር ብትነዋወጥ፥ ተራሮችም ወደ ባሕር ልብ ቢወሰዱ አንፈራም።” (መዝ. 45፡2 ።)

የምድር መነዋወጥ ምንድነው ? ብለን ከጠየቅን የተማመንባቸው ሰዎች ደጋግመው መክዳታቸው ነው ። ዓለም የሁለት ሰዎች ታሪክ ነው ። የአዳምና የሔዋን ፣ የአቤልና የቃየን ፣ የእስማኤልና የይስሐቅ ፣ የያዕቆብና የዔሣው ፣ የሙሴና የአሮን ታሪክ ነው ። በአጭር ቋንቋ የታማኞችና የከዳተኞች ታሪክ ነው ። በየትኛውም ዘመን ደጋጎች ነበሩ ፣ ስማቸው መቃብራቸውን ጥሶ ሲወጣ አይተናል ። በየትኛውም ዘመን ከዳተኞች ነበሩ ፣ በሥጋ ጨርሰው በነፍስ ሲወቀሱ ሰምተናል ። እውነትን ያፈነ መቃብር እስካሁን ድረስ የለም ። አንዳንዱ በልደቱ ፣ ሌላው በሞቱ ያብባል ። ከመጀመሪያው የመጨረሻው ይሻላል ። ትላንት የተወገዙ ዛሬ አማኝ ተብለው ሲወደሱ እንሰማለን ። ትላንት የተጠሉ ዛሬ ላይ ሲወደዱ እናስተውላለን ። ትላንት ባለ ዝና የነበሩ በተሰረቀ ተግባር ደምቀው እንደ ኖሩ ቀን ያወጣዋል ። የተሰጣቸውም ሽልማት ይነጠቃል ። አዎ ዓለም የሁለት ሰዎች ታሪክ ነው ። ከዳተኞች ለእኛ እንጂ ለታሪክ እንግዳ አይደሉም ። ክዳት የተጀመረው በእግዚአብሔር ላይ ነው ። ሰይጣን በዓለመ መላእክት ፣ አዳም በገነት እግዚአብሔርን ከዱ ። የመጀመሪው ተከጂ እግዚአብሔር ነው ። ከእግዚአብሔር በላይም በመከዳት ስሜት ለሚሰቃዩ መልስ የሚሆን ማንም የለም ።

ምድርን እናምናታለን ። ስረግጣት ቀጥሎ ብትገመስስ የሚል ስጋት የለንም ። ምድርን ባናምናት ኖሮ የተሠሩ ሕንፃዎች ሁሉ ባልተሠሩ ነበር ። ያመንናት ምድር ብትነዋወጥ ፣ አንድ ጊዜ አይደለም ብዙ ጊዜ ብትንቀጠቀጥ ምድርም ያለችው በእግዚአብሔር እጅ ነውና ልንሰጋ አይገባንም ። የተሸከመችን ምድር ሳትሆን ምድርን የተሸከመው እግዚአብሔር ነው ። ዓለምን በመሐል እጁ ይዞ የሚያስተዳድር ፣ እንዳይረሳን በእጁ ላይ የቀረጸን እግዚአብሔር በየዕለቱ ቡሩክ ነው ። ከምድር መነዋወጥ በላይ የሚያስደነግጥ ነገር የለም ። የሚያስፈሩ ነገሮች ሁሉ የማያስፈሩን እግዚአብሔርን ስንፈራ ብቻ ነው ። ፍርሃት በፍርሃት ይነቀሳል ። ከንቱ ፍርሃት በእግዚአብሔር ፍርሃት ድል ይነሣል ። የተማመንባቸው እነማን ይሆኑ ?

አንዳንድ ሰው በወላጆቹ በጣም ይታመናል ። እነርሱ የሞቱ ቀን ፣ የቀን ጨለማ ይውጠዋል ። ልጆችን ዘላለም እንደምንኖር አድርገን ማቅበጥ በቁም መግደል ነው ። ደግሞም በእኛ በተሰባሪዎቹ ላይ ሳይሆን በእግዚአብሔር ላይ እንዲደገፉ ማድረግ ብልህነት ነው ። “እኔ ሳለሁ” ሳይሆን “እግዚአብሔር ሳለ ምንም አትሆኑም” ብለን ማሳደግ ፣ የእምነትን ከለላ ማለማመድ በእውነት አስተዋይነት ነው ። በእርግጥም ስናየው የሚሞቱ አባትና እናትን የሰጠው የማይሞተው አባትና እናት እግዚአብሔር ነው ። አንዳንድ ሰው በልጆቹ ይታመናል ። አንድ የወለደ ሰው ሲያዩ፡- “አንድማ ምን ይሆናል ?” ብለው ያሳቅቃሉ ። እግዚአብሔር አሥራ ሁለቱንም መውሰድ እንደሚችል ይረሳሉ ። ልጆቼ ባይኖሩ አልኖርም የሚሉ አሉ ። ነገር ግን አሥራ ሁለት ልጅ የቀበሩ እናት አውቃለሁ ፣ አሁንም በሕይወት አሉ ። የልጅን ሞት መሞት ቢቻል ኖሮ ብዙ እናቶች በሞቱ ነበር ። ሁሉም የሚሞተው የራሱን ነው ። ጠላቴ ሞተ ብለን የማንደሰተው የእኛን ሞት ስላልሞተልን ነው ። ዓይን ዓይኑን ያየነው አይበረክትም ። ከቀን በኋላ በመጣ ልጅ ከቀን በፊት የሚያውቀንን እግዚአብሔር መለወጥ ትልቅ ክህደት ነው ። ልጆች ራሳቸውን ከቻሉም ትልቅ ነገር ነው ። ከዚያ አልፈው ለእኛ መታመኛ ሊሆኑ አይችሉም ። ልጆችን ኖረን ካኖርናቸው የረሱን ቀን አንጎዳም ፣ ሞተን ካኖርናቸው ግን ሜዳ ላይ እንወድቃለን ።

አንዳንድ ሰው የፍቅር ጓደኛው ላይ በጣም ይተማመናል ። ጓደኝነት የጋራ ፍቅር ነው ። በአንድ ሰው ብቻ ፍቅር ሊቀጥል አይችልም ። የማይጠልቅ የፍቅር ፀሐይ እግዚአብሔር ብቻ ነው ። ሰዎች ጥለውን ሲሄዱ እነርሱ የሄዱት ከክዳት ጋር ወይም ከሰይጣን ጋር ነው ። እኛ የቀረነው ከእግዚአብሔር ጋር ነው ። ደግሞም የሚሄዱት ወንጀለኛ ስለሆንን ሳይሆን የገዛ ጥፋታቸው ከእኛ ጋር አላኖር ብሏቸው ሊሆን ይችላል ። በጊዜ ከሄዱ ዕድሜአችንን ስላተረፉልን ማመስገን ይገባናል ። መዋደድ እንዳለ መጣላትም ይኖራልና መደንገጥ አይገባንም ። ከሚወደው ጋር የኖረ ጥቂት ነው። ፍቅር ለዘወትር አይወድቅም ተብሏል ። ይህንን ቃል የሚሽሩት ግን ቀዳሚዎቹ ክርስቲያን ተብለው የተጠሩት ወይም የተጠራነው መሆናችን ያሳዝናል ። የትዳር ጓደኛም ቆሞ በክዳት ፣ ሞቶ በጥሪ ሊለየን ይችላል ። የሚሆነው ሁሉ ሲሆን የነበረ ነው ። እኛ የምንጀምረው አዲስ መከራ ፣ የምናሟሸው አዲስ ሸክላ የለምና መደነቅ አይገባንም ። “ዘላለም” የሚባል ልጅ ሞተና ሲያለቅሱለት “ስም ብቻ ፣ ስም ብቻ” እያሉ አርግደውለታል ። አንዳንድ ነገሮች ስም ብቻ በሚሆኑበት ዓለም ላይ መታመናችንን በእግዚአብሔር ብቻ ማድረግ ይገባናል ። አንዲት እናት ሲመርቁ ሰማኋቸው፡- “ልጆቼ የማይከዳው እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይሁን !”

ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ታኅሣሥ 12 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ