የትምህርቱ ርዕስ | ዕድገት -11

ያደገ ሰው መገለጫ

ሁሉን የማወቅ ጉጉት የለውም

ያላደገ ልጅ ሁሉን የማወቅ ጥማት አለው ። በዓይኑ ያየውን በእግሩ ተራምዶ ወይም በጉልበቱ ድሆ በመሄድ በእጁ ይዳስሰዋል ፣ በአፍንጫው ያሸተዋል ፣ በጆሮው ያዳምጠዋል ፣ በመጨረሻ በምላሱ ይቀምሰዋል ። በስሜት ሕዋሳቱ ሁሉ ካላረጋገጠ በቀር ዕረፍት አያገኝም ። ገና ይህችን ዓለም መተዋወቅ የጀመረ በመሆኑ ሁሉን የማወቅ ጥማት አለው ። ያደገ ሰው ግን ሁሉን የማወቅ ጥማት ውስጥ አይገባም ። እነ እገሌ እንዴት ነው የሚኖሩት ? የገቢ ምንጫቸው ምንድነው ? ከየት አምጥተው ነው መኪናና ቤት የገዙት እያለ ራሱን አያጣብብም ። የሰውን ንብረት ማንሣት ፣ ሰው ያስቀመጠውን ነገር መፈተሽ ፣ የሰው ስልክ መበርበር ፣ የሰው ቦርሳ ማየት አናሳነት ነው ። ሕይወት የግልና የጋራ ኑሮ ድምር እንደሆነች ያገደ ሰው ያውቃል ። ሁሉም ሰው የራሱ ምሥጢር እንዳለው ይረዳል ። የማረከው ነገር ካለ እንኳ ባለቤቱን ያስፈቅዳል ። ምንድነው ብሎ ሊጠይቅ ይችላል ። ሰዎች ግላዊ ስለሆነ ሕይወታቸው ፈቅደው ካልተናገሩ ሲጠየቁ አይወዱም ። ከልባቸው ሲያምኑብን ግን ራሳቸው ይነግሩናል ። ጭነት ለማሸከም የሰውዬውን ጉልበት እንደምናየው ሁሉ ምሥጢር ለመንገርም የውስጥ ጉልበት ይታያል ። ለምሥጢር የማይበቃ ፣ ቢነግሩት የሚያወራ ወይም ቢነግሩት እንቅልፍ የሚያጣ አለ ።

ስለ ሰው ከመጠን በላይ መረጃ ያላቸው ሰዎች ቆይቶ የአእምሮ ታማሚ ይሆናሉ ። እግዚአብሔር ያላሸከመውን ሸከም የሚሸከም ሰው ተንገዳግዶ መውደቁ አይቀርም ። ሥልጣኔ ለአገራችን በጣም እየተመኘነው ያለ ነገር ነው ። ቢያንስ ከመቶ ዓመት በላይ ይህን ሥልጣኔ እየፈለግነው ነው ። ሥልጣኔ ማለት በሰው ኑሮ አለመግባት ነው ። ሥልጣኔን እየፈለግን በሰው ኑሮ መግባትና የሰውን ሕይወት ለአደባባይ ግብአት ማድረግ እንፈልጋለን ። ይህ የሚቃረን ነገር ነው ። ስለ ማንም ሰው ግላዊ ሕይወት አይመለከተንም ። በአገራችን የግልና የጋራ ኑሮ ድንበር አልተበጀለትም ። የእኛንም እርዳታ ካልፈለገ ልምራህ ማለት አይቻለንም ። ሰዎች በጣም ልናውቃቸው ስንንሰፈሰፍ በጣም ዝግ እያደረጉብን ይመጣሉ ። የዚያን ሰው ምሥጢር ማወቅ የፈለግሁት ለመርዳት አስቤ ነው ? ወይስ የወሬ ጥማት ይዞኝ ነው ? ብሎ ራስን መጠየቅ ይገባል ። እንኳን ሰው ቤት ለመዋልና ለማደር ይቅርና የራሳችንን የሕይወት ጥያቄ በቅጡ መመለስ ከቻልን ጎበዞች ነን ። የተሰጠን ዕድሜ የእግዚአብሔርን ሥራ የምንሠራበት መክሊት ነው ።

ሁሉም ቦታ አለሁ ማለት ተገቢ አይደለም ። እኛ ምሉዕ በኩለሄ የሆንን ሳይሆን ውስንነት ያለብን ፍጡራን ነን ። በሁሉ ቦታ ካልተገኘሁ ማለት ያስንቃል ። መስቀሉንም መሣሪያውንም ፣ ስብከቱንም ፖለቲካውንም የእኔ ብቻ ነው ማለት ሚና የለሽ ሰው ያሰኛል ። አምባገነን የሆኑ መንግሥታት ስለ ዜጋቸው ሁሉን የማወቅ ፍላጎት አላቸው ። ግላዊ መብትንም በመጋፋት ስልኮችን በመጥለፍ ፣ በመከታተል ፣ እርስ በርስ በማናቆር ስልት ይራመዳሉ ። ይህ ረጅም ዕድሜ የሚሰጥ መንገድ አይደለም ። የበታችነት ስሜት ያለባቸው የትዳር ጓዶች በጣም መከታተል ያበዛሉ ። በዚህ መንገድ ትዳራቸውን የሚመሩ ሰዎች የሚጓዙት ለጥቂት ጊዜ ብቻ ነው ። ረጅም ጉዞ ቢጓዙ እንኳ ኑሮአቸው ሲኦልን የሚያስንቅ ይሆናል ። የሰው ልጅ በጣም አጭር ፣ ታይቶ ጠፊ የሆነችውን ይህችን ዕድሜ እንዴት ውብ እንደሚያደርጋት ብቻ ማሰብ አለበት ። እንኳን ጠርቶ ለሚያመጣው መከራ አይደለም ፣ ለታዘዘው መከራም የሚሆን ጉልበት ካገኘ ዕድለኛ ነው ። ከማንም ሰው ጋር ስንኖር ገብስ ገብሱን እንጂ ጠለቅ ያለ የማወቅ ፍላጎት ሊኖረን አይገባም ። ምክንያቱም ባለቤቱ የተሸከመውን ነገር ያለ ጊዜው ሰርስረን ስናውቅ በዚያ ፈተና ልንጠመድ እንችላለን ። ለማማከር ቢሆን የምክር መንፈስ ያግዘናል ፣ የወሬ ጥማት ግን ፈተና ይዞ ይመጣል።

ይህ ዘመን ብዙ ምርጫዎች ያሉበት ዘመን ነውና መርጠን ማየትና መስማት ካልቻልን ዕድሜአችን በዋዛ ፈዛዛ ነገር ሊያልቅ ይችላል ። ዋዛ ፈዛዛ ማለት ራሱ ዋዛ ነገር ፈዛዛ ያደርጋል ማለት ነው ። ስልካችን ላይ ረጅም ሰዓት ስናጠፋ እየፈዘዝን እንመጣለን ፣ እንቅልፋችንም ችግር ይገጥመዋል ። የምንሰማውና የምናየው ነገር ሕይወታችንን ፣ ሙያችንን ፣ ከሁሉ በላይ ሃይማኖታችንን የሚያዳብር መሆን አለበት ። ብዙ ሙያ ያላቸው ሰዎች ውጤታማ አይደሉም ፣ አንዱን ሙያ አድምተው የያዙ ግን ጠንክረው ይሠራሉ ፣ ተፈላጊም ይሆናሉ ። ሁሉን ማወቅ ለፍላፊ ያደርጋል ። በቅንጥብጣቢ እውቀት መታለልን ያመጣል ። ሊቃውንትን እንዳንሰማ እንቅፋት ይሆናል ። ብዙ ቋንቋ ማወቅ መልካም ነው ፣ ብዙ ቋንቋ የሚያውቁ ግን ባካና ናቸው ። ሁሉ ቦታ መኖር የሚችሉ ስለሚመስላቸው የረጋ ስፍራ የላቸውም ። ምናልባት ለስለላ ሥራ ይፈለጉ ይሆናል ። ይህ ደግሞ ሕይወትን ውስብስብ ያደርጋል ።

ሰዎች በነጻነት ከእኛ ጋር እንዲኖሩ ጥያቄ ማብዛት የለብንም ። እንዴት ? ለምን ? እያልን ሰውን ማስጨነቅ ተገቢ አይደለም ። የማወቅ ጥማት የሚባለው እውቀት ነክ የሆነ ነገር ነው ። ከወሬ የማያልፍን ነገር አጥብቆ መጠየቅ አስፈላጊ አይደለም ። “አጥብቆ ጠያቂ እናቱን ሞት ይረዳል” እንዲሉ ጥያቄ ማብዛት የሚያሳዝን ነገር ይዞ መግባት ፣ ሳይዘጋጁ መርዶ መስማትን ያመጣል ። ሕይወትን ቀለል ማድረግ ፣ ባልንጀርነትን መከርከም ፣ የነገሮችን በጎ ገጽታቸውን ብቻ ማሰብ ፣ ሰዎችን ይቅር ማለት ፣ ዓለም እንዲህ ነው ብሎ መደነቅን መቀነስ ደስተኛ ያደርጋል ። በዚህ ዓለም ላይ ስንኖር በሁለት ዓይናችን ዓይተን ከሰው ጋር መኖር በጣም ከባድ ነው ፣ አንዱ ሲያይ አንዱ መጨፈን አለበት ። በሁለት ጆሮ ሰምቶም ከሰው ጋር መኖር አይቻልም ፣ ባንዱ ሰምቶ በሁለተኛው ማፍሰስ ግድ ይላል ። ያደገ ሰው ያወቅሁትን ምን አደግሁት ? ለሰማሁት ነገር ምን መፍትሔ አበጀሁ? ይላል እንጂ ሁሉን የማወቅ ጥማት የለውም ። እንደ ሰላይም የሰውን ኑሮ መከታተል ተገቢ አይደለም ፣ ክብረ ነክ ነው ። የራስን እየደበቁ የሰውን ለማወቅ መጨነቅም ከንቱ ልፋት ፣ ራስን ማሰቃየት ነው ። ብቻ ያደገ ሰው ሁሉን የማወቅ ጥማት የለውም ።

ይቀጥላል

ሚያዝያ 14 ቀን 2018 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ