የትምህርቱ ርዕስ | ዕድገት -13

ያደገ ሰው መገለጫ

ለአገሩ ዘብ ይቆማል

ከግለሰብ ክብር የአገር ክብር ይበልጣል ። ያ ማለት የአገር ክብር የሚጀምረው አንድ ግለሰብን ከማክበር ነው ። አንድ ግለሰብ ግን አገሬ ከምትሞት እኔ ልሙት ብሎ ራሱን ሊሰጥ ይገባዋል ። ትልቅ ተብለው የሚታፈሩ አገሮች ለአንድ ዜጋቸው የሚከፍሉት ዋጋ ከፍ ያለ ነው ። አንድን በጠላት መንደር የወደቀ ወታደር ለማንሣት የሚከፍሉት ዋጋ ፣ አንድ ዜጋቸው ሲታሰር ሁሉንም አቅም ተጠቅመው ወደ አገሩ ሲመልሱት ትልቅነታቸው ጎልቶ ይታያል ። ጣልያን ወደ አገር ገብቶ የፈጀውን ያህልና የፈጸመውን ዘግናኝ የግድያ ዓይነት እርስ በርሳችን አድርገነዋል ። አንድን ግለሰብ እንዲጠብቅ አደራ የተሰጠው ዘብ መልሶ ያንን ግለሰብ በአደባባይ ሲገርፍ ፣ ያለ ፍርድ እርምጃ ሲወስድ የታየ ነው ። ይልቁንም በአገራችን ከምንከበረው በሰው አገር ላይ የምንከበረው እየበለጠ ይመስላል ። ሰውን ለማክበር ሰውነቱን ማየት ብቻ በቂ ነው ። የተከበረ ሕዝብ ያከብራል ። የአንድ ግለሰብ ነጻነትና ክብር ሲመለስ ያን ጊዜ አገራችን ከፍ ትላለች ። እኛ የናቅነውን አካላችንን ማንም ሊያከብርልን አይችልም ። በንጉሡ ዘመን በኢትዮጵያ ፓስፖርት ብቻ ያለ ቪዛ አውሮፓ አገራት ይገባ ነበር ፣ አንድ የኢትዮጵያ ብር ለንደን ላይ ባለ ባንክ በእኩያ ይዘረዘር ነበር ። በፈረንጅ አገር ጥገኝነት የጠየቀ ኢትዮጵያዊ በቍጥር ሁለት ነበር ። አንደኛውም ከንጉሡ የተጣሉ አምባሳደር ናቸው ። ከ12 ዓመታት በላይ ለዘለቀው የተማሪ እንቅስቃሴ ከውኃ መርጨት በላይ ርምጃ አልተወሰደበትም ። የውጭ ትምህርት ዕድል አግኝተው የሄዱ ተማሪዎች አገራቸው ለመመለስ ይናፍቁ ነበር ፣ አንዳንዶችም ናፍቀው ትምህርታቸውን ጥለው ይመጡ ነበር ። ያ ሁሉ ክብር የት ሄደ (

አገር ማለት ግለሰብ ፣ ቤተሰብ ፣ የሃይማኖት ተቋማት ናቸው ። እነዚህ ሁሉ ክብር ፣ ክብር ካልሸተቱ አገራችን ልትከበር አትችልም ። አንዲት አገር የምታድገው በአዋቂዎቿ ነው ፣ ክብሯ የሚቀጥለውም በአማካሪዎችዋ ነው ። እኛ ግን አዋቂውን ጠልተን ፣ መካሪውን በጠላት ሰፈር ፈርጀን ዕራቁታችንን በዓለም አደባባይ ፊት ቆመናል ። የራሳችንን ሰው አዋርደን የሌላውን ስንቀበል ዓለም ይስቅብናል ። እንግዳ ተቀባይ ነን እያልን የገዛ መልካችን የሆነውን ወገን ስናሳድድ ሁሉም ይሸሸናል ። ሰዎች የሚያከብሩን ራሳችንን ባከበርነው መጠን ነው ። ጣሊያን ወደ ኢትዮጵያ ለሁለተኛ ጊዜ ሲገባ የተማሩትን ፈጀ ፣ ለባንዳዎች ደመወዝ ቆረጠ ። የ1953 ዓ.ም. መፈንቅለ መንግሥት ጣሊያንን ያባረሩ ፣ ነጻነትን ያስከበሩ ታላላቅ ሰዎችን የፈጀ ነው ። የ1966 ዓ.ም. አብዮት አገሪቱ የነበሩአትን ምሁራን ፣ አስተዳዳሪዎችና የጦር ጀግኖች ፣ እንዲሁም እውቅ ዲፕሎማቶች ፣ የአፍሪካ ሕብረት መሥራቾችን የፈጀ ነው ። ቀኝ እጃችን ግራ እጃችንን የመቍረጥ ያህል የተሠራ ትልቅ ስህተት ነው ። የቀለም አብዮት አስነሥተን ቀይና ነጭ ሽብር እያልን የፈጀነውም ያው የተማረውን ወገን ነው ። የደርግ መንግሥት እንደ ወደቀ አሁንም ሊቃውንቱ እንዲባረሩ ፣ የዳኝነት ሥርዓቱ እንዲታወክ ተደረገ ። በየሥርዓቱ አገሪቱ ብዙ ዋጋ የከፈለችባቸው አዋቂዎች ያልቃሉ ፣ ይሰደዳሉ ። አሁንም ድረስ አዋቂዎች ስፍራ አላገኙም ። ዋዘኞች የሚከበሩትን ያህል ሊቃውንትን የሚያውቅም ፣ የሚያከብርም ትውልድ እየጠፋ ነው ።

በሰው አገር ላይ የወፍ ጎጆ ላለመንካት ጥንቃቄ ይደረጋል ፣ አንድ የጫካ አውሬ በመኪና ተገጭቶ እንዳይሞት ሁሉም ቆሞ ያሳልፈዋል ። ከሰው ክብር አልፈን እንስሳትን ማክበር ፣ ደኖችን መንከባከብ የፈጠረውን አምላክ ማምለክና ማስደሰት ነው ። አገር እንድትከበር እያንዳንዱ ግለሰብ ነጻነቱና ክብሩ ሊጠበቅለት ይገባል ። አገር ማለት ሰው ነው ። መሬቱ ያለ ሰው አንዳች ጥቅም የለውም ። ሰው ከሌለ የለማው ከተማ የአውሬ መፈንጫ ይሆናል ። አገር ዕድገትዋ ትልቅ እንዲሆን ምሁራንዋን ማክበር አለባት ። ለሰው አገር አዋቂ እየከፈልን የራሳችንን አዋቂ ስደተኛ ካደረግን ትልቅ ሞኝነት ነው ።

ላለፉት ሃምሳ ዓመታት በባዕድ አገር ቤተ መንግሥት ፊት ለፊት ሰላማዊ ሰልፎች በኢትዮጵያውያን ይደረጋሉ ። እነርሱ እንዳሳመሙን ረስተን አድኑን እንላለን ። በዚህ ምክንያት የአገራችንን ውስጥ ልብስ ለዓለም እንገልጣለን ። ችግራችንን ራሳችን ካልፈታነው የዜና ርእስ እንኳ የመሆን ዕድልን አናገኝም ። ሞቱ ብሎ እንኳ ለመዘገብ ዓለም ይንቀናል ። አገራችንን እንደ አንድ ጎጆ ቆጥረን እርስ በርስ ለመመካከር መወሰን ያሻናል ። የሁላችን አገር እንጂ የእገሌ አገር የለችንም ። ሁሉም ሰው በአገሩ እንደሚመለከተው ሊያስብ ይገባዋል ። ሰለጠኑ የሚባሉት ቆሻሻ መንገድ ሲያገኙ ባይጥሉትም ያነሡታል ። ምክንያቱም ውብ አገር እንድትኖራቸው ይፈልጋሉ ። እኛ ግን ውበትን ፈልገን ፣ ማጽዳትን ጠልተን የምንኖር ነን ። እስካሁን ድረስ ኢትዮጵያዊ በአገሩ ፣ በሚስቱና በሃይማኖቱ ተደራድሮ አያውቅም ። ግን ረሀብ ትልቅ ወራሪ ነውና ይህንን ጠላት በሥራ ማባረር አለብን ። ራሱን ያልቻለ ከልመና ያልወጣ ሕዝብ በፉከራ ብቻ ክብር አያገኝም ! የድርሻንን በመወጣት የጎደለውን መጠየቅ ይገባናል ። ራሳችንን የሚያሳዩንን እንኳን ልንገፋቸው ልንከፍላቸው ይገባል ። የአገር መስተዋት የሆኑ አዋቂዎች አይገኙም ። ሐኪም ቤት የምንሄደው በሽታችንን ለማወቅና መፍትሔ ለማግኘት ነው ። ችግራችንን የሚነግሩንን ማክበር ይገባናል ። ሁሉንም ለማወቅ አንችልምና መካሪ አታሳጣን ብለን መጸለይ አለብን ።

አብዝተን የምንመለከተውና የምናራግበው ነገር በመላው ዓለም ይታያል ። ነውራችንን ባራገብን ቍጥር ዓለም ሰምቶ ይጸየፈናል ። “እናንተ ኢትዮጵያውያን ምን ሆናችኋል ? ሃይማኖት ነበራችሁ እኮ” እያሉ ብዙ የውጭ ሰዎች ይጠይቃሉ ። አንድ ኢትዮጵያዊ ታማኝነትን ሲያጎድል መላው ኢትዮጵያዊ መጥፎ ስም ያገኛል ። አገሬን ለማስከበርም ጨዋ መሆን ይገባኛል ማለትን መልመድ አለብን ። አሊያ በአንድ እኔ ስህተት የ130 ሚሊየን ወገኔ ክብርና ተቀባይነት ይወድቃል ብለን መስጋት አለብን ። ሁሉም ነገር ይነካ ፣ አገራችንን ግን ማስነካት አይገባንም ። የምንፈልገውን ነጻነት አጠገባችን ካለው ሰው እንጀምር ፣ ነጻነትን እየፈለግን የሌላው ነጻነት ላይ ከቆምን ምኞት ብቻ ሆነን እንቀራለን ። የሌላውን አስተሳሰብና ሃይማኖት ማክበር አለብን ። ሰው ሁሉ እንደ እኔ ይሁን ከሚል አዙሪት መውጣት ያስፈልገናል ። ሁሉንም ግፍ ሞክረነዋል አሁን የቀረን ደግነት ነውና እንጀምረው ።

ያደገ ሰው ለአገሩ ዘብ ይቆማል ፣ የአገሩን ምሥጢር አሳልፎ አይሰጥም !

ይቀጥላል

ሚያዝያ 21 ቀን 2018 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ