ያደገ ሰው መገለጫ
ጠንካራ ምግብ ይመገባል
ሕፃናት ወተት ሲመገቡ ትንሽ ያደጉ ደግሞ ሥጋ ይበላሉ ። የጠነከሩ ደግሞ አጥንት ይግጣሉ ። ምንም ጠቃሚ ቢሆን ለሕፃናት አጥንትና ሥጋ ገዳይ ይሆናል ። ለመካከለኞቹ ደግሞ ወተትና ሥጋ በአንድነት ይሰጣል ። ያደጉት ግን አጥንት ይግጣሉ ። ላደገ ሰው ወተት ተጨማሪ እንጂ ዋና ምግብ መሆን አይችልም ። ሥጋ ይበላል ፣ አጥንት ይቆረጥማል ። እውቀትና መንፈሳዊነት የጅማሬ ፣ የመካከለኛነትና የፍጹምነት ደረጃ አላቸው ። የጅማሬ እውቀቶች ግላዊ እድገትን ብቻ ታሳቢ ያደረጉ ናቸው ። ጀማሪ አዋቂ እንዲያስተምር ፣ ወጣኒ ክርስቲያንም የካደውን ሰው እንዲያሳምን አይመከርም ። ወተት የሚጠጣው ሕፃን ወላጆቼ ምን በሉ ? አይልም ። ለወንድሜ ላስተርፍለት የሚል አሳብም የለውም ። ለራሱ ረሀብ ብቻ ያለቅሳል ። ፍላጎቱንም የሚገልጥበት ብቸኛ ቋንቋው ልቅሶ ነው ። ጀማሪ አዋቂና መንፈሳዊም ስለ ራሱ እድገት ብቻ ይታሰብለታል እንጂ ለምን ለሌላው አልተረፍክም አይባልም ። በሃይማኖት ያልጠነከረ ሰው ሌሎችን እንዲያሳምን አይመከርም ። ቢጠይቁት መልስ ፣ ቢቃወሙት ጽናት ፣ እሺ ቢሉት ምግብ የለውም ። አዲስ ክርስቲያን አደራ አይሰጠውም ፣ ሥልጣንም ሊቆየው ይገባል ። ልጅነቱን ማጣጣም ፣ ስላመነው ነገር በቂ እውቀት መያዝ ያስፈልገዋል ። ሁልጊዜ ግን የሚታሰብለት አይደለም ። በማደግ እዩኝ ተመልከቱኝ ባይነቱን ይሽራል ።
በትንሽ ነገር መደሰት በትንሽ ነገር ማዘን የመንፈሳዊ ልጅነት መገለጫ ነው ። ሁሉንም በልክ ማድረግ ያዋቂ ሰው መልክ ነው ። ሁሉም ኃላፊ መሆኑን ማወቁ የአንድ ሙሉ ሰው ማሳያ ነው ። እኔ የሚል አዋቂ አይደለም ፣ እኛ የሚል የሌሎችን ፍላጎት የሚያዳምጥ እርሱ በርግጥ አድጓል ። እኔነት ስቃይ አለው ፣ ከበቂ በላይ መብላት ጉዳት እንዳለው ሁሉ ፣ ምግብም እንደ መድኃኒት መመጠን ያስፈልገዋል ። ለራስ ብቻ ማሰብ ኃይልን ማባከን ነው ። እርካታን የሚያሳጣ ነው ። ግለኞችና ዘረኞች በሕይወታቸው በስቃይ ውስጥ የሚያልፉ ናቸው ። መሥራት አይወዱም ፣ ሌላው ሲሠራ ግን ይቀናሉ ። የሚቀኑት በሥራው ሳይሆን በፍሬው ነው ። ሳይደክሙ ሁሉ እንዲሆንላቸው የሚመኙ ፣ የሌላውን ቀምተው መክበር የሚሹ ናቸው ። መብሰል ለሌሎች መኖር ነው ። የሌላው ህልውና የእኔም ህልውና ነው ብሎ ማሰብ ትልቅ ዕድገት ነው ። ከተማው ያለ ሰው ፣ ልቅሶው ያለ አላቃሽ ፣ ሰርጉ ያለ ወገን ከባድ ነው ። የሙሉ ከተማ ባለቤት ብንሆን ያለ ሰው ከተማው የእኛ ቢሆን በቁማችን ሲኦል እንደ ገባን ይሰማናል ። ከሰው ጋር ሲያለቅሱት ኀዘንም ይወጣል ። ደስታው ያለ አጋር ደስታ አይሆንም ። የምንረዳቸው ምስኪኖች ብቻ ሳይሆኑ የምንወዳጃቸው እኩዮችም ያስፈልጉናል ።
መካከለኛ እውቀት እንደ ድልድይ መሸጋገሪያ መሆን ነው ። ስለ ተሰማራንበት ነገር ፣ ይበልጥ ስለምናምነው ነገር በቂ እውቀት ያስፈልገናል ። አየሩን ሁሉ የሞላው ድምፅ የመካከለኞቹ ነው ። እውቀታቸው ካለ ማወቅ ከፍ ያለ ከማወቅ ያነሰ ፣ አንድን ነገር በቅጡ አድምተው መገንዘብ ያልቻሉ ሰዎች ሁሉንም መቆጣጠር እንደሚችሉ ያስባሉ ። ቅድስና ቢያጡ በነውር መታወቅ ይሻሉ ። ሮጠው መቅደም ቢያቅታቸው ጠልፈው መጣልን ግብ ያደርጋሉ ። መካከለኛ እውቀት ተናጋሪ ያደርጋል ፣ የበላዮቹን ግን ማክበር አይችልም ።
ጠንካራ ምግብ መመገብ የማደግ ምልክት ነው ። ጠንካራ ምግብ የምንለው ፍልስፍና ፣ የኖሩ ነገሮችን መንቀፍ አይደለም ። ከብዙኃኑ ለየት ለማለት የሚደረግ ሙከራም አይደለም ። ጠንካራ ምግብ የሚለውን በዚህ ዘመን የምንረዳው ጥርጥርን እንደ ሃይማኖት ቃል መቀበል ነው ። ጠንካራ ምግብ ነገረ እግዚአብሔርን በጥልቀት መረዳት ፣ ቅዱሳት ምሥጢራትን በእምነት መካፈል ፣ በአምልኮተ እግዚአብሔር ዕለት ዕለት ማደግ ፣ መንፈሳዊውን ዓለም መመርመር መቻል ፣ የነፍስን ድምፅ የመላእክትን ዜማ መስማት መቻል ፣ በማየት ብቻ አለመወሰን ፣ ለበላይ አለቆች በደስታ መገዛት ነው ።
ነገረ እግዚአብሔር የማይሰለች ምሥጢር ነው ። የተነበበን መጽሐፍ ደግሞ ማንበብ የሚፈልግ ጥቂት ነው ። መጽሐፍ ቅዱስን ግን ከ200 ጊዜ በላይ የዘለቁ መነኮሳትን አውቃለሁ ። የእግዚአብሔር ነገር ማለዳ አዲስ ነው ። ዜና በትኩሱ ፣ ወይን በመክረሙ ተፈላጊ ነው ። ዜና ሥላሴ የሆነው ግን በየዕለቱ ጣዕም አለው ። ዘመን የማያልፍበት ርእስ ነው ። የሥላሴን አንድነትና ሦስትነት ፣ አስማተ መለኮትን ፣ ግብረ መለኮትን ፣ ኩነታትን ፣ የወልድን ሰው መሆን ፣ የቤዛነት ሥራውን በጥልቀት ማወቅ ፣ እስከ ተፈቀደልን ድረስ መመርመር ተገቢ ነው ። በቤተ ክርስቲያን ሕፃናት ማን ፈጠረህ? ሥላሴ ከሚለው ትምህርት ይሳተፋሉ ፣ ትልልቅ አዋቂዎችም የሥላሴን ምሥጢር ያጠናሉ ። እግዚአብሔር ሰማይና ምድርን የፈጠረ እንደሆነ ሁሉ ከሰማይና ምድር የሚሰፋ ምሥጢርም አለው ። ቅዱሳት ምሥጢራት የምንማራቸውና የምናምናቸው ብቻ ሳይሆኑ የምንሳተፋቸው ጸጋና በረከት ናቸው ። በመንፈሳዊ ሕይወት ለማደግ ፣ የቤተ ክርስቲያንን አንድነት ለማጽናት ፣ የሥጋና የነፍስ ጤንነትን ለመጠበቅ ምሥጢራት አስፈላጊና ግድ ናቸው ። ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት የዕለት ተግባራቸው ምሥጢራትን ለምእመናን ማቅረብ ነው ። የመማር ግቡም ምሥጢራት ናቸው።
ጸሎት ሁልጊዜ የተመጠነ ሳይሆን የሚያድግ ነው ። መዘመርም ደስታን የሚሰጥ ነው ። በየጊዜው በየሰዓቱ ፣ ያለማቋረጥ እግዚአብሔርን ማምለክ የተፈጠርንበት ዓላማ ፣ ሰማይ ስንደርስ ለዘላለም የምንከውነው ነው ። አምልኮታችን ማደግ አለበት ። መንፈሳዊው ዓለም ምንድነው ? ብለን መጠየቅ የማደግ መገለጫ ነው ። መንፈሳዊውን ዓለም ማወቅ የቻለ ሰው ስለ ምድር ማወቅ አይቸገርም ። ምን እየመጣ እንደሆነ ያውቃል ። የሰዎችን ስሜት ያነባል ። ለማያስተውሉም እያየ ይነግራቸዋል ። መንፈሳዊ ሰው የዜና መስኮትን ሳይሆን የትንቢት መስኮትን ማየት ይችላል ። ዛሬን ሳይሆን ነገን ለማየት ብቃት አለው ። ወደ ጥልቅ የነፍስ ስርገት ውስጥ መግባት ይችላል ። ነፍሱ የምትፈልገውን ማወቅና መስጠት ይፈልጋል ። የመላእክትን ዜማ መስማት ፣ አብዝቶ መዘመር ፣ ወደ ጣዕመ ነፍስ መድረስ ይችላል ። ጠንካራውን ምግብ የበሉ አባቶች ተአምራትን በስመ እግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ ያደርጋሉ ፣ በሰው ልብ ያለውን ይገነዘባሉ ። በሩቅ አገር የሚመከረውን ይሰማሉ ፣ ዓይን ከሚያየው ርቀው ማየት ይችላሉ ። ይህ ለጥቂት ሰዎች የተሰጠ ሳይሆን መንፈሳዊ ጥልቀት ሲኖር የሚመጣ ነው ።
ይቀጥላል
ሚያዝያ 27 ቀን 2018 ዓ.ም.