የትምህርቱ ርዕስ | ዕድገት -9

ያደገ ሰው መገለጫ

ስሜቱን ይገዛል

ጀግንነት ሰዎች ወደው ፈቅደው ራሳቸውን የሚሰጡበት እንጂ በግዳጅ የሚገኝ አይደለም ። ይህችን አጭር ዘመንና ጎዶሎ ዓለም በጀግንነት አጣፍጠዋት የሚያልፉ ዕድለኞች አሉ ። ጀግና ለራሱ ክብርና ጥቅም ሳይሆን ለወገኑ ክብርና ጥቅም የሚቆም ነው ። ጀግና ሕይወቱን ለዓላማው ለመሠዋት የማይሰስት በሙላትና በጉድለት ውስጥ ለወገኑ የሚገኝ ነው ። ጀግና ከተጎዳ ጋር የሚቆም ፣ ለምስኪኖች የሚሞትላቸው ፣ ዛሬ ተሰብሮ ነገ ላይ ሲታወስ የሚኖር ነው ። ጀግና የዛሬው ሆዱ ሳይሆን የነገው የአገር ክብር የሚታየው ነው ። የሚያደርገውን የሚያደርገው እከበር ብሎ ሳይሆን ነፍሱን ለማሳረፍ ብሎ ነው ። ጀግንነት በአንድ አቅጣጫ ብቻ የሚገኝ ሳይሆን በተሰየሙበት ተግባር ለወገን ብርሃን መሆን ፣ ቀልጦ እንደ ሻማ ማብራት ነው ። የመሥዋዕትነት ኑሮ አካልን ቢያጎሳቁልም ነፍስን ግን ያረካል ። ለእውነት መቆም ከሁሉ በላይ ደስ ይላል ። ጀግና ዘሎ ሰው ተጋፊ ፣ የሰው አገር ደፋሪ አይደለም ። ጀግና ራሱን ሲያከብር የሌላውንም ክብር የሚጠብቅ ነው ። ቤተ ክርስቲያን የሃይማኖት አርበኞችዋን ታከብራለች ፣ ታስባለች ። የጀግኖች ታሪክ በተነገረ ጊዜ ሁሉ ለአገር የተከፈለውን ዋጋ ትውልድ ተረድቶ ለነጻነቱ እንደሚነሣ ሁሉ የሰማዕታትና የመምህራን ታሪክ በተነሣ ጊዜ ሁሉ የአሁን ዘመን ምእመናንና አገልጋዮች ልባቸው ለሰማዕትነት ይነሣሣል ። ጀግኖች ብዙ ጠባይ ቢኖራቸውም አንደኛው ጠባያቸው ስሜታቸውን መግዛት ነው ።

በታላላቅ ፈተናዎችና የውጊያ ውሎዎች ስማቸውን ያስጠሩ በሰላማዊው ዘመንም ክብራቸውን ጠብቀው መኖር ይገባቸዋል ። በመጠጥ ፣ በአጉል ነገር እስረኛ ከሆኑ ፣ አዩኝ ገላመጡኝ እያሉ ዘራፍ ካሉ ጀግንነታቸው ይረክሳል ። ጀግንነት ጥበቃ ይፈልጋል ። የጀግንነት የክብር መጠበቂያው ስሜትን መግዛት ነው ። ያን ጊዜ በወጣትነት አርበኛ የነበረው ጀግና በሽምግልናው መካሪ ፣ አገርን በጸሎት ጠባቂ ይሆናል ። ስሜትን መግዛት ዕድገት ነው ። መኖር በራሱ ጦር ሜዳ ውስጥ ማለፍ ነው ። ሕይወት ብርቱ ጦርነት ናት እንደ ተባለ በሕይወት ውጊያ ውስጥ ብዙ ጀግኖች ይወጣሉ ። ትዕግሥትን ገንዘብ በማድረግ ፣ ደርሶ ሌላውን አጥቂ ባለመሆን ፣ ለተማረከ በመራራት ፣ በልኩ በመጣላት በሕይወት ውስጥ አርበኞች ይወጣሉ ። ሕይወት ጦር ሜዳ ናት ። ጦር ሜዳ መዋጊያው ነው ። መሸሽ የማይችሉበት የከበባ ዘመን አለ ። ያንን ቆራጥ ሁኖ ማሳለፍ ይገባል ። የእኔን ሕመም ማን ሊታመምልኝ ፣ የእኔን ሞት ማን ይሞትልኛል ? ብሎ በቆራጥነት መጋፈጥ አስፈላጊ ነው ። የትዳር አጋር ወኅኒ ቢገባ ፣ ልጅ የአልጋ ቍራኛ ቢሆን ዕዳው የእኔ ነው ፣ ፍቅሬ የሚገለጥበት ዘመን መጣ ብሎ ጸንቶ መዋጋት ፣ አሸንፎ መውጣት አስፈላጊ ነው ።

ስልት የሚነደፍበት የጦር ሰፈር አለ ። የጦር ሊቃውንት መሬት ላይ ወረቀት ዘርግተው ፣ አሸዋ ላይ አስምረው የጦርነቱን ካርታ ፣ ምክረ አሳብ ይሰጣሉ ። እነዚህ በብዙ ውጊያ የዋሉ ፣ የጦር ትምህርት የቀሰሙ ፣ በዕድሜ የገፉ ናቸው ። በሕይወት ጦርነት በእውቀትም በዕድሜም ከበሰሉት ምክር መቀበል ይገባል ። ስልቱ የሚገኘው ከበሰሉት ነው ። ድል መጋፈጥ ብቻ ሳይሆን ስልትም ይፈልጋል ። ከጦር ሜዳው ኋላ የሚገኘው ሌላው ደጀኑ ነው ። ደጀኑ ሕዝብ ነው ። ትጥቅና ስንቅ አቅራቢው ነው ። ልቡን አንጠልጥሎ ድልን የሚጠብቀው ነው ። ድል ጠባቂ ከሌለው ከንቱ ሞት ነው ። ድሉ ሲበሰር ሆ የሚለው ያ ደጀን ነው ። በሕይወት ውስጥም ደጀኑ በጸሎት የሚረዱን ወላጆች ፣ ልጆቻችንን በሥነ ምግባር የሚያንጹ ካህናት ፣ አደራ የምንላቸው ጎረቤቶች ፣ ደግሞም የምንኖርላቸው ወገኖች ናቸው ። የሚኖሩለት ነገር ከሌለ መኖር ብቁ አይደለም ። ጀግና ለራሱ አይሞትም ፣ ወገኑ ላይ መሣሪያ አይደግንም ። ለወገኑ ግን ራሱን በደስታ ይሰጣል ። በሕይወት ውስጥ ለራስ ከመኖር ለሌሎች መኖር ፣ ጥቅምን ሳይሆን አገርን ማስቀደም ትልቅ አርበኝነት ነው ። ድሆችን ፣ ምስኪኖችን ማሰብ ፣ ለድምፅ አልባዎች ድምፅ መሆን ፣ ፍትሕን መፈለግ የአንድ ልከኛ ነዋሪ መገለጫ ነው ። የጀግና መውጫው አስቸጋሪ ቀን ነው ፣ የሕይወት ፈተናም ለድል አክሊል የሚያበቃ ነው ።

ስሜትን መግዛት ትልቅ የጀግንነት መገለጫ ነው ። ሰዎች ስሜታችንን አነሣሥተው በምንሰጠው ምላሽ ያለንበትን አድራሻ ያውቃሉ ። ስንቆጣ ኃይላችንና ብልሃታችን ስለሚከዳን ግብታዊ ሊያደርጉን ይፈልጋሉ ። ስሜታችንን ስንቆጣጠር ምን እያሰብን እንደሆነ ስለማይረዱ የሚጠሉን ይሰጋሉ ። ዝምታ በጊዜው አስፈላጊና የድል መንገድ ነው ። የሰው ልጅ አንደበቱንና ፍትወተ ሥጋውን ከተቆጣጠረ ሌላው ፈተና ቀላል ነው ። በስሜት ተነሣሥተን የምንናገረው ሌሎችን የሚጎዳ ፣ እኛን የሚያጸጽት ይሆናል ። ነገሮችን በስሜት ማድረግ ጥሩ ነው ፣ ስሜታዊ መሆን ግን ተገቢ አይደለም ። ቶሎ መልስ መስጠት ፣ ላስብበት ሳይሉ ቶሎ ቃል መግባት ራስን በራስ ማሰር ነው ። ስሜታችንን ለመግዛት ቀን መውሰድ ተገቢ ነው ። ይደር ማለት ትልቅ ብልሃት ነው ። ይልቁንም ከፍ ባለ ቦታ ስንቀመጥ ፈጣን ምላሽን መጠንቀቅ አለብን ። ሁሉን ባናስደስትም ሁሉን ግን ማስከፋት አይገባንም ። ስሜት የአሁን ዘመድ ፣ በቀለኛ የሚያደርግ ሙቀት ፣ መተው ስንችል ገንዘብ ወዳጅ የሚያደርገን ስግብግብነት ነው ፤ ይህ እንዳይደገም ትምህርት መውሰድ ይገባናል ። ስንጣላ በልኩ ፣ መልስ ስንሰጥ በተጠየቅነው መጠን ፣ ስንሰደብ ንቆ በማለፍ ማደጋችንን ማረጋገጥ አለብን ።

ያደገ ሰው መገለጫ ስሜቱን መግዛት ነው ።

ይቀጥላል

ሚያዝያ 9 ቀን 2018 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ