የተጠራነው ለማደግ ነው ። ከጀማሪነት ወደ ሙሉነት እናድጋለን ። በዕድሜ ፣ በእውቀት ፣ በቁመት ፣ በመወደድ ማደግ ያስፈልገናል ። ለዕድገታችን ጊዜ ፣ ቦታ ፣ ሁኔታ ፣ ምግብ ፣ ሰዎች አስፈላጊ ናቸው ። መንፈስ ቅዱስ የማይደክመው መምህር ፣ የማይታዘብ አሰልጣኝ ነውና ክርስቶስን ወደ መምሰል ዕድገት ያመጣናል ። ሰዎች በገንዘብ ፣ በሥልጣን ፣ በዝና ፣ በደጋፊዎች ብዛት እያደጉ ይመጣሉ ። እውነተኛው ዕድገት ግን አካላዊ ፣ ሥነ ልቡናዊ ፣ ፍቅራዊና መንፈሳዊ ነው ። የተሟላ ዕድገት በሩቅም በቅርብም ቢያዩት ያው ነው ። ያልተሟላ ዕድገት ውስጡ ለቄስ ፣ ቢከፍቱት ተልባ ፣ ምነው በሩቁ በቀረብኝ የሚያሰኝ ነው ። በቂ የአካል ብቃት ያለው ካላነበበ የሚያስበው በጡንቻው ነው ። ንግግሩም ልልና ዕድሜውን የማይመጥን ይሆናል ። አዋቂውም አካላዊ ጥንካሬ ከሌለው አለሁ የሚለው ከአንገት በላይ ብቻ ነው ። የተሟላ ዕድገት አስፈላጊ ነው ። የእግዚአብሔርም ዕቅድ ነው ።
ዕድገት ወደ ታች ዝቅ ወደ ላይ ብቅ የሚል ነው ። ወደ ታች ዝቅ የሚለው ሥር ለመስደድ ነው ። ሥር ያልሰደደ ዛፍ ነፋስ ቢመጣም ባይመጣም ቶሎ ይወድቃል ። ሥር መስደድ በተባራሪ እውቀት ሳይሆን ሥነ ሥርዓት ባለው መንገድ ከመምህር እግር ሥር ቁጭ ብሎ በመማር የሚገኝ ነው ። ሥር መስደድ ማዕበሉንም ነፋሱንም አሳልፎ ለመቀጠል ይረዳል ። ወደ ላይ ብቅ ማለት መሥረጽ ፣ ቡቃያ ማውጣት አስፈላጊ ነው ። መጀመሪያ ሥር ለመስደድ ፣ ራስን ለማጠንከር መሰወር ቀጥሎ ለሌሎች ተስፋ ፣ ልምላሜ ፣ ፍሬ ፣ መብል ፣ በረከት ለመሆን መገለጥ ይገባል ። ዕድገት በመሰወርና በመገለጥ የሚታይ ነው ። የመሰወርን ወራት ማክበር ቦታ ለመያዝ ፣ ዘላቂ ምግብን ለማግኘት ፣ ተግዳሮቶችን ለመቋቋም አስፈላጊ ነው ።
የሚታዩ ነገሮች ሁሉ የማይታይ ነገር አላቸው ። የሚታየው ዛፍ የማይታይ ሥር አለው ። የሚታየው ሕንፃ የማይታይ መሠረት አለው ። የሚታየው መንግሥት የማይታዩ አማካሪዎች አሉት ። የሚታየው ጥበቃ የማይታዩ የደኅንነት ሠራተኞች አሉት ። የሚታየው ግብዣ የማይታዩ ወጥ ቤቶች አሉት ። የሚታየው ድል የማይታዩ የጸሎት ደጀኖች አሉት ። በአደባባይ ውጤታማ ለመሆን በድብቅ መጸለይ ፣ በር ዘግቶ ማንበብ ፣ አዋቂዎችን ማማከር ወሳኝ ነው ። አሊያ ለጥቂት ጊዜ መንጎማለል ይቻላል ፣ ቀጥሎ ግን ዘላለማዊ ውዳቂ መሆን ይመጣል ።
ዝቅ ካላሉ ከፍ ማለት አይቻልም ። የዛፉ ሥር ፣ የሕንፃው መሠረት ጭቃ ለጭቃ መሄድ ይፈልጋል ። መልክ አጥቶ ሥሩ ለዛፉ ፣ መሠረቱ ለሕንፃው ውበት ይሰጠዋል ። ዝቅ ማለት ወይም ትሑት መሆን ወሳኝ ነው ። ለመፋቀር መደማመጥ ፣ ለመግዛት መደማመጥ ያስፈልጋል ። መደማጥ ያለው በትሕትና ውስጥ ነው ። እግዚአብሔር በሁሉም ሰው ውስጥ ውድ ነገር አስቀምጧል የሚለው ክቡር አስተሳሰብ እንድንደማመጥ ያደርገናል ። የሰለጠነው ወታደር በገሀድ መታየት አለበት ፣ በስውር የተዘጋጀው ያ ጸሎተኛ ፣ ያ ደቀ መዝሙር አሁን ደግሞ በአገልግሎት መታየት ያስፈልገዋል ። የሚገለጥ የተሰወረ ነው ። የሚናፍቁትም የተሰወረውን ነው ። ስጦታው ተሸፍኖ ሲመጣ ያጓጓል ። የመሰወር ወራትን ያላወቀ የመገለጥ ዘመኑ ቀና አይሆንለትም ። በመሰወር ዘመን የሚገለጡ ፣ በመገለጥ ዘመን ደግሞ የሚሰወሩ አያሌ ናቸው ። ዕድገት መሰወርና መገለጥ ነው ። ምልምሉ ወጣት ተሰውሮ ሲመጣ ስልጡን ወታደር ሁኖ ይመለሳል ፤ ዲያቆኑ ተሰውሮ ሲመጣ መንኵሶ ፣ አበ ብዙኃን ሁኖ ይመጣል ። በስውር ተዘጋጅተዋልና ሁሉም ያከብራቸዋል ። መቼም ሰፈሩ ላይ ወታደርም መነኵሴም የሚሆን የለም ። ራቅ ብሎ ፣ ተሰውሮ ፣ ተዘጋጅቶ ፣ ተለማምዶ ይመጣል ። ዓለም እነዚህን አለማክበር አይሆንላትም ። ማደግ ትፈልጋላችሁ ? ስኬታማ ስለሆናችሁ አድጋችኋል ማለት ነው ?
ይቀጥላል
መጋቢት 26 ቀን 2018 ዓ.ም.