የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ዘላቂ ክብር

 የቴባኑ አባ ዮሴፍ በጌታ ፊት ሦስት ነገሮች የከበሩ ናቸው አለ፡- አንድ ሰው ፈተናና መም ሲመጣበት በስታ ሲቀበል ሁለተኛው አንድ ሰው ሥራውን በጌታ ፊት አንዳችም ሰዋዊ መልክ ሳይኖረው ንጹ አድርጎ ሲያቀርብ ሦስተኛው ደግሞ አንድ ሰው ለመንፈሳዊ አባቱ ታዛዥ ሆኖ ሲኖርና የራሱን ፍላጎት ሲተው ነው ።
ወዳጆቻችንን ደስ የምናሰኘው የምንፈልገውን ብቻ በማድረግ ሳይሆን ፍላጎታችንን አሸንፈን ፍላጎታቸውን ስናደርግላቸው ነው ደስታ ዘላቂነት ያለው ወዳጅነት ጽድቅ የሰፈነበት ሲሆን ብቻ ነው እውነትን ታሳቢ ያደረጉ ፍላጎቶች ለእግዚአብሔር ክብር ይውላሉ እግዚአብሔርንም ወዳጅ ስናደርግ የምንወደውን ሁሉ ለእርሱ በመተዉ ነው አብርሃም የእግዚአብሔር ወዳጅ የተባለው ለሚወደው እግዚአብሔር የሚወደውን ልጁን ለመሥዋዕትነት ስላቀረበ ነው እግዚአብሔርም፡- “የምትወደውን አንድ ልጅህን ይስሐቅን ይዘህ ወደ ሞሪያም ምድር ሂድ እኔም በምነግርህ በአንድ ተራራ ላይ በዚያ መሥዋዕት አድርገህ ሠዋው አለ ።” ዘፍ. 22፡2 አብርሃም የተጓዘበት መንገድና የፈጀበት ቀናት ለማመንታትና አሳብ ለመለወጥ በቂ ነበሩ እግዚአብሔርን ግን የወደደው ከምክንያት በላይ ነው በዚህም የእግዚአብሔር ወዳጅ ተባለ የእግዚአብሔር ጥያቄ የምትወደውን ልጅህን እንጂ የምትጠላውን ጠላትህን ሠዋ የሚል አልነበረም የሚጠሉትን መሠዋት ሰውነት ነው ፤ የሚወዱትን መሠዋት ወይም ለእግዚአብሔር መተዉ ግን መንፈሳዊነት ነው
እግዚአብሔር የምንወደውን ነገር በመተዉ ለእርሱ ያለንን ፍቅር እንድንገልጽለት ይፈልጋል እግዚአብሔርን የምንወደው ከጠላቶቻችን ጋር አወዳድረን ሳይሆን ከምንወዳቸው ይልቅ ውድ አድርገነው ሊሆን ይገባል አብርሃም የሚወደውን ልጁን በመተዉ የእግዚአብሔር ወዳጅ እንደ ተባለ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም ከሚወዳቸው ይልቅ ጌታን በመውደዱ ታላቁን የእረኝነት አደራ ተቀበለ “ምሳ ከበሉ በኋላም ኢየሱስ ስምዖን ጴጥሮስን፡- የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ ፥ ከእነዚህ ይልቅ ትወደኛለህን ? አለው ።” ዮሐ. 21፡15 ልብ በሉ የምትወዳቸውን ያህል አላለውም ሰው ዕቃም ይወዳል ጌታችን ልዩ ፍቅር ፈለገ ስለዚህ፡- “ከእነዚህ ይልቅ ትወደኛለህን ?” አለው ፈቃዳቸውን ለክርስቶስ ፈቃድ የተዉ የከበሩ ይሆናሉ
የቴባኑ አባ ዮሴፍ በጌታ ፊት ሦስት ነገሮች የከበሩ ናቸው አለና የመጀመሪያው፡- “አንድ ሰው ፈተናና መም ሲመጣበት በስታ ሲቀበል ነው” አለ ሕመም ለደረሰብን ነገር የምንሰጠው ስሜታዊ ምላሽ ነው ሕመም ለአካላዊና ለሥነ ልቡናዊ ጉዳቶች የሚጠቀስ ነው ሕመም የሚወልደው ፈተና አለ ዓለምና ሰይጣን የተለያዩ ሕመሞችን በማምጣት ይፈትኑናል “እግዚአብሔር ይወደኛል ትላለህ ፣ የምታልፍበት ግን የተወደደ ልጅ የሚልፍበት አይደለም ፤ እግዚአብሔርስ ልጄ ካለህ ልጁን እያሰቃየ የሚደሰት አባት አለ ወይ ?” የሚል ፈተና ይመጣል ፈተና የተማርነውን የምንዳስስበት የተግባር መለኪያ ነው አንድ በቅርብ ዘመናት የነበሩ ኦርቶዶክሳዊ አባት በሃምሳ ዓመታቸው በካንሰር በሽታ ተያዙ እርሳቸውም፡- “እስከ ዛሬ ያስተማርሁትን የምኖርበት ዘመን መጣ” በማለት ተናግረዋል
ፈተና መበጠር ነው ሰፌድ ላይ እንዳለ ስንዴ መንጠርጠርና መበጠር ነው የተመሳሰለውና የተደባለቀው ነገር ሁሉ እንዲጠራ ፈተና ያስፈልጋል ያወቅን የመሰለንና ያወቅነው እንዲታወቅ ፈተና አስፈላጊ ነው ፈተና ትርጉሙ መመዘኛ ማለት ነው ምን ያህል እንደ ተማርንና እንዳወቅን የምንመዝንበት ነው “እግዚአብሔር ይህ ፈተና እንዲመጣ የፈቀደው ክርስትናን በርግጠኝነት እንዳውቀውና እንድመሰክረው ነው” በማለት መደሰት ያስፈልጋል ሕይወት ሌሊትና ቀን በመሆኗ ቀኑን ብቻ በማየት ስለ ሕይወት ሙሉ እውቀት አይኖረንም ፈተና ሙሉ ሰው ፣ ሕመምም አዛኝ ሰብእናን ያስገኝልናል ሕመም ትልቁ የወታደር ማሰልጠኛ ነው ልካችንን የምናውቅበት የትሕትና ኮሌጅ ሕመም ነው በፈተናና በሕመም ጻድቁ አብርሃምና ጻድቁ ኢዮብ እንደ ከበሩ አትርሱ
በእግዚአብሔር ዘንድ የከበረው ሁለተኛው ነገር፡- “አንድ ሰው ሥራውን በጌታ ፊት አንዳችም ሰዋዊ መልክ ሳይኖረው ንጹአድርጎ ሲያቀርብ” ነው በእግዚአብሔር ስም እያገለገልን የሰዎችን የስሜት ጣቢያ ሳይሆን የእርሱን ደስታ ማሰብ ይገባል የእርሱ ደስታ የእውነተኛ ሰዎች ደስታ ነው ሰዋዊ መልክ ያለው አገልግሎት ሽንገላና ራስን ማታለል ያለበት አገልግሎት ነው ሰዋዊ መልክ ያለው አገልግሎት ውስጣዊ ማንነት ተራቁቶ ውጫዊ ክብረትን ብቻ ማሰብ ነው ሰዋዊ መልክ በጌታ ፍቅር እወድሃለሁ እያሉ ለወንድም መቃብር መቆፈር ነው ሰዋዊ መልክ በአፍ እየቆረሱ በእጅ መስጠት አለመቻል ነው ሰዋዊ መልክ መስጠት እየቻሉ ለድሀው ሰው ጌታ ሆይ ስጠው ማለት ነው ሰዋዊው መልክ በፊት ለፊት እየሸነገሉ ፣ በጀርባ ማማት ነው ሰዋዊ መልክ አድካሚው የተውኔት ኑሮ ፣ የጭንብል ዓለም ነው
በእግዚአብሔር ፊት የከበረው ሦስተኛው ነገር ደግሞ፡- “አንድ ሰው ለመንፈሳዊ አባቱ ታዛዥ ሆኖ ሲኖርና የራሱን ፍላጎት ሲተው ነው ።” ልብ አድርጉ ልጅ የሆነ ሁሉ አባት አለው የተወለደ ሁሉ አባት አለው በግ የሆነ ሁሉ እረኛ አለው መንፈሳዊ ሕንፃ የሆነ ሁሉ አናጢ አለው እነዚህን የምናገኘው በቤተ ክርስቲያን በኩል ነው ቅዱስ ሲፕሪያን፡- “ከቤተ ክርስቲያን ውጭ ድኅነት የለም” ያለው ለዚህ ነው
ዲቃላም አባት አለው አባቱን አለማወቁ አንድ ችግር ሊሆን ይችላል በቤተ ክርስቲያን ትምህርት “አባት የሌለው አባት እግዚአብሔር አብ ብቻ ነው ” ደግሞም ተኩላ እረኛ የለውም በግ ግን እረኛ አለው በግ የሆነ ሁሉ እረኛና አባት አለው መንፈሳውያን አባቶቻችን በቃሉ የወለዱን በቃሉ ያሳደጉን ሲሆኑ መንፈሳዊ ጉዞአችን ቀላል እንዲሆን የሚረዱን ናቸው ትልቅ የሥነ ልቡና ሐኪሞቻችን ፣ በጸሎት የሚረዱንና ወደ ፈውስ እንድንጠጋ የሚያግዙን ናቸው እነዚህን በቃሉ ያገለገሉንን አባቶች መታዘዝ ያስፈልጋል በቤት ውስጥ ጉርምስና ሊኖር ይችላል በመንፈሳዊ ዓለም ግን ጉልምስና እንጂ ጉርምስና የለም በመታዘዝ ውስጥ የራሳችንን ፍላጎት በግድ እንጥላለን መታዘዝ ለብዙ ሰው መራራ የሚሆነው ይህን ሐቅ ባለመረዳቱ ነው ፍላጎታችንን ካልጣልን አልታዘዝንም ማለት ነው
መታዘዝ ብዙ አደጋ የሚመስሉ ነገሮች አሉት አብርሃም ሲታዝዝ ከፊቱ ያለው ልጁን መሠዋት ነው ሙሴ ሲታዘዝ ከፊቱ ያለው ለሞት ወደሚፈልገው ፈርዖን መሄድ ነው እስራኤል ሲታዘዙ ወደ ቀይ ባሕር መጥለቅ አለባቸው መታዘዝ መራራ እውነትን መጋፈጥ ይጠይቃል ውጤቱ ግን በእግዚአብሔር ፊት መክበር ነው እነዚህን ሁሉ ባለ ማድረግ በሰው ዘንድ መክበር ይቻላል ፤ የሰው ክብር ግን የሞትን ማኅተም አይሰብርም የእግዚአብሔር ክብር ግን ለዘላለም ይኖራል
ጸሎት
እታዘዝ ዘንድ በለበስከው ሥጋ ለናዝሬት ነዋሪዎች ሁሉ እየታዘዝህ አርአያ የሆንኸኝ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ፣ የጠፋውን ዓለም በመታዘዝ መማርክን አድለኝ የሚያስጨንቀኝ በሰው ዘንድ ያለው ክብር እንጂ ያንተ ክብር አይደለም የሚጠፋውን ከማይጠፋው የምለይበት ጸጋ አድለኝ ያመንሁትን እንድኖረው መጨከንን ስጠኝ ከምወዳቸው ይልቅ አንተን በመውደድ ወዳጅ እንድባል አግዘኝ ፍጻሜ ባለው ዓላማህ ለዘላለሙ አሜን
የበረሃ ጥላ 4
መስከረም 4 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲአመ
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ