የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ዘወረደ

እንኳን ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ታላቅ ጾም አደረሳችሁ !

“በውድ ልጁም እንዲያው የሰጠን የጸጋው ክብር ይመሰገን ዘንድ ይህን አደረገ ።” ኤፌ. 1 ፡ 6 ።

እግዚአብሔር አብ ሰው ሁን ፣ ሙትላቸው ብሎ ወደዚህ ዓለም የላከው አንድ ልጁን ነው ። አንድ ልጁን ለድግስ እንኳ የሚልክ ወላጅ በሌለበት ዓለም አንድ ልጁን ሞትን ቅመስ ብሎ ላከው ። አንድ ልጁን ለበደለ ባሪያ የሚሰጥ ጌታም ከእግዚአብሔር አብ በቀር ማንም የለም ። ፈቃዳቸው ግን አንድ ነውና አብ ቢልክ ወልድም ፈቅዶ ነው ። በፈቃድ አንድ እንደሆኑ በሥልጣንም አንድ ናቸው ። እግዚአብሔር ይህን ዓለም በመፍጠር ከገለጠው ፍቅር ይህን ዓለም ለማዳን የገለጠው ፍቅር ይበልጣል ። ሰውን ለመፍጠር ወደ መሬት ዝቅ ያለው ፣ ሰውን ለማዳን በበረት ተወለደ ። ሰውን ለመፍጠር እጆቹ በጭቃ የተለወሱ ሰውን ለማዳን በችንካር እጆቹ በደም ራሱ ። ሰውን ለማዳን ሰማያዊው ምድራዊ ሆነ ። እርሱ ምድራዊ ካልሆነ እኛ ሰማያዊ መሆን አንችልምና ። ምድር እንኳ የማትገባን ሁና የስቃያችን ስፍራ እንድትሆን ተፈርዶ ሳለ ሰማይን የምንወርስ ሆንን ። እኛ ከበደልነው መድኃኔ ዓለም የካሰው በለጠ ። ባለ ዙፋኑ ባለ በረት ሆነ ። እኛም ያለንን በረት ሰጠነው ፤ እርሱም በየማኑ መቀመጥን ለቤተ ክርስቲያን ሰጠ ።

ሁሉ ግዛቱ ሳለ ተሰደደ ተባለ ። መግደል እየቻለ ሞተ ። ወዳልተለያት ዓለም መጣ ተብሎ ተነገረለት ። ከዚህ በፊት ያልነበረውን ወልደ እጓለእመሕያው መባልን ገንዘብ አደረገ ። ከዚህ በፊት አባቱን በሁሉ ታዝዞ ሳለ ሙት ለሚለው ትእዛዝ ግን ለመጀመሪያም ለመጨረሻም ጊዜ አንዴ ታዘዘ ። በሚገድል አምላክ የሚኮራው የሰው ልጅ አምላኬ ሞተልኝ ብሎ ይመካ ዘንድ ትሕትናን አገነነ ። አምላክነቱ ሳይለወጥ ሰው ሆነ ። ሰውነታችን ሳይለወጥ አማልክት ዘበጸጋ ተባልን ። ያለ ልክ ዝቅ ስላለ ያለ ልክ ከፍ ከፍ አለን ። ደጋኑ ወደ ኋላ በተሳበ ቍጥር ቀስቱ ርቆ ይሄዳል ፤ እርሱ ዝቅ ባለ መጠንም የሰው ክብር ከፍ ብሏል ። ከመሬት በታች የተፈረደበት የአዳም ሥጋ ከመናብርትና ከሥልጣናት በላይ በዙፋን ተቀመጠ ። የመንግሥተ ሰማያት ጌታ ዘመዳችን ሁኗልና መንግሥተ ሰማያት የማያሰጋን ሆነ ።

እግዚአብሔር ይህን ዓለም ለማዳን ውድ ልጁን ሰጠ ። አብ ፈቀደ ስንል ወልድም ፈቀደ ማለታችን ነው ። ወልድ አዳነ ስንልም አብም አዳነ እያልን ነው ። በማዳን አንድ ናቸውና ። አዳምን የፈጠሩ እጆች አዳምን ለማዳን ተቸነከሩ ። ፍጠረኝ ሳይለው ፈጥሮታልና አድነኝ ሳይለው ሊያድነው ሞተ ። ፍቅር ማሳሰቢያ ሳያሻው የሚያስብ ፣ ያለ ጠያቂም መልስ የሚሰጥ ነው ። ሰው ግን እንደ ቀላል እንዳይቆጥረው 5500 ዘመን የዝግጅት ጊዜ ሰጠ ። የጸሎታችን መልስ የሚዘገየው ደጅ የጠናንበትን ነገር ቶሎ እንደማንተወው ስለሚያውቅ ነው ።

ሰው ለማዳን የምንወደውን መስጠት ግድ ይላል ። እግዚአብሔር ይህን ዓለም ለማዳን የሚወደውን አንድ ልጁን ሰጠ ። የምንጥለውን መስጠትማ መገላገል ነው ። ለሚገላግሉንም ዋጋ እንከፍላለን ። የምንወደውን መስጠት ግን ዋጋ መክፈል ነው ። የምንወደውን ካልሰጠን የምንወደውንም እንዲያው በነጻ ካልሰጠን ሌሎችን መታደግ አንችልም ። እግዚአብሔር ግን የሰጠው አንድ ልጁን ነው ። አንድ ልጁን ያለ እናት የወለደ እግዚአብሔር አብ አዳምን አባትም እናትም ሁኖ የጸጋ ልጅነት ሰጠው ። እግዚአብሔር አብ የሚወደውን ልጁን እንደ ሰጠን ተናግሯል ። በዮርዳኖስ የሰማነው ድምፅ ይህ ነው ። በአብና በወልድ መካከል ያለው ፍቅር ሊተረጎም አይችልም ። ወላጆች ከልጃቸው ጋር ያላቸው ፍቅር ይቀጥላል ፣ ልደቱ ግን በተከፍሎ ነው ። ልጁ ያለ ወላጆቹ የሚቀርበት ነገር አለ እንጂ አይሞትም ። አብ ወልድን የወለደው ግን ያለ ተከፍሎ ነው ። ያለ ልጁ የኖረበትና የሚኖርበት ዘመን የለም ። ለዘላለም ከአባቱ ያልተለየ ልጅ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው ።

ልጅ መባልም የአካልና የክብር ስም የሆነው ለወልድ ነው ። የአብና የወልድ የፍቅር ግንኙነት እኛ የእግዚአብሔር ልጆች ከሆንበት ጸጋ ጋር ምንም ግንኙነት የለውም ። ያገሬ ሞኝ “ኢየሱስም ልጅ ነው ፣ እኔም ልጅ ነኝ” ይላል ። እርሱ ራሱ ለይቶ፡- “ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ” አለ ። ዮሐ. 20፡17። ደባልቆ ወደ አባታችን አላለም ። የእርሱ ልጅነት የባሕርይ የእኛ የጸጋ ነውና ። እግዚአብሔር አብም ምንም እንኳ ዮሐንስ መጥምቅ ልጁ ቢሆንም ከክርስቶስ ጋር ደባልቆ የምወዳችሁ ልጆቼ አላለም ። የምወደው ልጄ አለ እንጂ ። በመልክ የሚመስለው ፣ በባሕርይ የሚተካከለው ልጁ አንድ ነው ። የፀሐይ ብርሃን ከፀሐይ ሳይለይ ወደ ዓለም ይመጣል ፣ ክርስቶስም ከአብ ሳይለይ ወደ ዓለም መጥቷል ። ምስጋናና ክብር ይድረሰው ። ዘወረደ ብለን በዐቢይ ጾም የመጀመሪያ እሑድ የምንዘምረው ምሥጢረ ሥጋዌን ነው ።

የኤፌሶን መልእክት ትርጓሜ /12

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
የካቲት 20 ቀን 2014 ዓ.ም.

እባካችሁ ለሌሎች አካፍሉት

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ