መግቢያ » ልዩ ልዩ ሁለት » ዝምተኛነት

የትምህርቱ ርዕስ | ዝምተኛነት

ዝምተኛነት ተፈጥሮ ሊሆን አይችልም። ጨለማ የተፈጠረ ሳይሆን የብርሃን አለመኖር ነው ይባላል። መብራት ማብሪያና ማጥፊያ አለው። ውኃም መክፈቻና መዝጊያ አለው። ሰው የመናገሪያና የዝምታ ጊዜ አለው፡፡ ዝም ብሎ መቅረት ዱዳነት ፣ ሲናገሩ መኖር ለፋፍነት ነው። ዝም ፣ ድርግም ማለት ዱዳነት ፣ ሁልጊዜ ተናጋሪ መሆን እብደት ነው። ሙቅና ቀዝቃዛ ውኃ ተመጣጥኖ ሲወርድ ምቾት ይሰጣል። ዝምታና ንግግርም መመጣጠን አለባቸው። የምናመጣጥነውም ለራሳችንና ለሰዎች ጤንነት በማሰብ ነው።

የተመጠነ የሚባለው ከበርበሬውም ሳያቃጥል፣ ከሽሮውም አልጫ ሳይሆን ነው:: ሁልጊዜ መናገርም ያቃጥላል፣ አንደበት እሳት ነው፣ የፈተና መግቢያም ነው። ሰው ለፈተና የሚዳረገው በመናገርም ነው። በዚህ በኩል ጎበዝ ነኝ ሲል፣ ሲፈርድ፣ ራሱን ከመጠን በላይ ሲገልጥ ለፈተና ሊዳረግ ይችላል። ሁልጊዜ ዝም ማለትም ተገቢ አይደለም። ግዑዝ የትራፊክ ምልክት እንኳ ይናገራል። ሐውልትም ዘመንና ታሪክን ያወሳል። ሰው ከእነዚህ አንሶ ዝም ቢል ይወቀሳል። ዋናው የምንናገርበትና ዝም የምንልበት ሁኔታ በዓላማ ሊሆን ይገባዋል።

ዝም የሚሉ ሰዎች ሲበዛ ሰዎችን ያስጨንቃሉ፣ እንደ  ድብቅ ይታያሉ። ንግግር ገና በጠዋቱ የጀመርነው በልምምድ ነው:: ዝምታ በልምምድ የተገኘውን ቋንቋ ማጥፋት ነው። ዝም የሚሉ ሰዎች ከምናውቃቸው የተለየ ጠባይ አላቸው። ጥያቄ መፍጠርና ጥያቄ መሆን ደስ ይላቸዋል። በዝምታቸው ሰዎች ሲተራመሱ ማየት በጣም ይወዳሉ። ዝምታ በቀልም ሊሆን ይችላል። ደስታቸውን መግለጥ ስለማይፈልጉ ስሜታቸውን ሰው እንዳያውቅባቸው ይፈልጋሉ። አጠገባቸው ያሉትን ተናጋሪ ሰዎች በዝምታ መቅጣት ይፈልጋሉ። ተናጋሪ  ራሱ ነዶ እስኪጠፋ ድረስ ያዩታል። ውስጣቸው ጠንካራ ሲሆን ሁሉም ነገር ከልክ አያልፍም የሚል አሰተሳሰብ አላቸው።

ዝም የሚሉ ሰዎች ከሌሎች በተሻለ ስለ ዓለም ግንዛቤ አላቸው። ማወቃቸውን ግን ሰዎች እንዲያውቁባቸው አይፈልጉም። ከራሳቸው ጋር በጣም ልዩ ፍቅር አላቸው። ወደ ውስጣቸው በጣም ስለሚያወሩ ከሰዎች ጋር ማውራትን አይፈልጉም። ራሳቸውን አውርተው አይጠግቡትም። አጠገባቸው ስላሉት ሰዎች ቸልተኝነት ሊሰማቸው ይችላል። በጣም የሚወዱት ነገር ጫጫታ ነው። ብዙ ዝምተኞች ኳስ ፣ ዘፈን፣ መዝሙር፣ በዓላት፣ ሰርግ ፣  ድምፁ ከፍ ያለ ነገር ይወዳሉ። ቀኑን በሙሉ የሚለፈልፉ የሬዲዮ አፍቃሪዎች ናቸው። መናገርን ባይፈልጉም የሚዝናኑት ግን ጩኸት በመስማት ነው።

ዝምተኞች ራሳቸውን ገለል ማድረግ ሲወዱ ሁልጊዜ መፈለግ እንዳለባቸው ያስባሉ። በውስጣቸው የማይገለጽ ደስታ ሲኖራቸው ያንን ለሌሎች ማጋራት አይችሉም። ሥራ መሥራት ያስደስታቸዋል :: ሥራቸውን ግን መግለጽ ስለማይችሉ አይታወቅላቸውም። ወንዶች ከሆኑ ብዙ ሴቶችን የማስከተል አቅም አላቸው። ዝምተኛ ሴቶችም በዙሪያቸው ለፍላፊ ወንዶች አሉ። ዝም የሚለው ግን ዝም ያለ አይደለም። ተናጋሪዎችን ቀጥሯል፣ አሊያም በጽሑፍ ተደብቆ ይናገራል። ሥዕል ይሥላል::

የዝምታው ምንጭ ለመናገር የሚያበረታታ ቤተሰብ አለማግኘት ሊሆን ይችላል። በቂ እውቀት አለማዳበር ዝም ያሰኛል። ፍርሃትም የዝምታ ምንጭ ነው። ዝምታን እንደ ቅድስናና ጨዋነት ማሰብም ዝም ያሰኛል። በመከራና በአደጋ መደንገጥ ወደ ዝምታ ዓለም ይወስዳል። ብናገር ሰው ላስቀይም እችላለሁ በማለት ዝም ሊባል ይችላል። ከመጠን በላይ ሰዎችን ማክበርና መፍራትም ዝምታን ይወልዳል።

ዝም የሚሉ ሰዎች ብዙ ዕድሎች ያመልጧቸዋል። ክብርን ያገኙ ቢመስላቸውም በተቃራኒው ግን ምንም እንደማያውቁና ስሜት አልባ እንደሆኑ ይገመታሉ። ተገቢ ንግግር አለማድረጋቸው ከቅን ፍርድ እንዲርቁ ያደርጋቸዋል። የአንደበትን አገልግሎት አልተረዱምና ሌሎችን መስበክ ያቅታቸዋል። ችግርን መናገር እንደ ሽንፈት ስለሚቆጥሩት በቀላሉ ጉዳይ ትልቅ ዋጋ ይከፍላሉ። ራሴ እወጣዋለሁ የሚል ኩራት ቢኖራቸውም መረዳዳት ግን አስፈላጊ መሆኑን ይረሳሉ።

ለመናገር ጊዜውን፣ ቦታውን ፣ ሁኔታውን መርምሩ ! እንዲሁም ለዝምታ ጊዜውን፣ ቦታውንና ሁኔታውን ተመልከቱ !

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

መስከረም 9 ቀን 2018 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ