የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የሁልጊዜው ጎበዝ

“ውኆቻቸው ጮኹ ተናወጡም፥ ተራሮችም ከኃይሉ የተነሣ ተናወጡ።” (መዝ. 45 ፡ 3 ።)

ተራሮች ወደ ባሕር ልብ ሲወሰዱ ከሚከሰቱ ነገሮች አንዱ የውኆች ጩኸትና መናወጥ ነው ። እንደ ተራራ የገዘፈ ቁመናና ስም ፣ ዝናና ከበሬታ ያላቸው ሰዎች ድንገት ሲወድቁ ዓለም በወሬ ይናወጣል ፣ በሰበር ዜና ይወጠራል ። የማይጠፉ የሚመስሉ ሲጠፉ ፣ ዘላለም ኗሪ ነን ያሉ ሲታጠፉ ብዙ ጩኸት ይሰማል ። ግንዱን የተደገፉ ግንዱ ሲወድቅ አብረው ይወድቃሉ ። በገናና ሰዎች ስምና ዝና የሚኖሩም የታመኑባቸው ቀን ሲከዳቸው ፣ እነርሱም በጨለማ ይዋጣሉ ። የበሉትን የሚያስተፋ ፍርሃት ይከባቸዋል ። በምን ቀን በእገሌ ፎከርኩ ? እስኪሉ ድረስ ጸጸት ያሰቃያቸዋል ። የቀን ጌቶችን መታመን መጨረሻው ሐፍረት ነው ። በእግዚአብሔር የሚታመኑ እርሱ ይሰጠኛል ብለው ይሰጣሉ ፣ በሰው የሚታመኑ ግን የሌላውን ይቀማሉ ። በእግዚአብሔር የሚታመኑ ዝቅ ይላሉ ፣ በሰው የሚታመኑ ግን አምባውን ካልሞላን ይላሉ ። በእግዚአብሔር የሚታመኑ የነገውን ያስባሉ ፣ ከነገም አልፈው ስለ ዘላለም ያሰላስላሉ ፤ በሰው የሚታመኑ ግን የአሁን ብቻ ሰው ሆነው ይኖራሉ ። በእግዚአብሔር የሚታመኑ ነገ የማይደገም ንግግር አይናገሩም ፣ በሰው የሚታመኑ ግን ለአንደበታቸው ልጓም የለውም ። አዎ የታመኑባቸው ተራሮች ሲሰወሩ ብዙዎች በልባቸውም በአፋቸውም ይጮኻሉ ። መደበቂያም እስኪያጡ ይናወጣሉ ። የሰደቡአቸው ሰዎች ፣ የገፉአቸው ድሆች ፊት ለፊታቸው ድቅን ይሉባቸዋል ። “የጊዜ እንጂ የሰው ጀግና የለውም” እንዲሉ ደፋሩ ፈሪ የሚሆንበት ጊዜ ይመጣል ።

ውኆቻቸው ይጮኻሉ ። ተራሮች ወደ ባሕር ልብ ሲገቡ ፣ ኃያላን ሲወድቁ በእጃቸው የበሉ ይጮኻሉ ። እነዚህ መንገድ የሚሸኙ እንጂ አብረው መከራ የሚቀበሉ አይደሉም ። የበላ ሆድ መከረኛ ነውና ትንሽ ቡፍ ፣ ቡፍ ይላሉ ። እነዚህ ሰዎች ተራሮቻቸው በጸኑ ዘመን እነርሱ እንጀራ ስለጠገቡ የሌላውን ረሀብ ሐሰት ነው ይሉ ነበር ። የእንግሊዝ ንግሥት ልጅ ፣ “ሰው ተራበ” ቢሏት “አይስክሬም አይበሉም ወይ?” አለች ይባላል ። ሰው በአእምሮው ማሰብ ትቶ በጎሣ ፣ በገንዘብ ካሰበ ከአራዊት እየከፋ ይመጣል ። ሰው ስለ ራሱ ድሎት መናገር ይችላል ፣ እገሌ አልራበውም ማለት ግን ተገቢ አይደለም ። ተራሮች ሲነዋወጡ የነገዱ ፣ ያናገዱ ይጮኻሉ ። የማይናወጠውን ዙፋን ፣ መንበረ ሥላሴን የተጠጉ ግን እንደ ከበሩ ይኖራሉ ። ሟች ሰው በሟች ላይ ተስፋ ማድረጉ ይገርማል ። ሕያው እግዚአብሔርን ትቶ “ሞተ” በሚል በሁለት ፊደል በሚዘጋ ሰው መታመን ሞኝነት ነው ። ዘመናችን የቲፎዞ ዘመን ነው ። ፀሐፊም ፣ ደራሲም ፣ ሰባኪም ፣ ዘማሪም በእምነት ሳይሆን በሚጨፍሩ ሰዎች ተደግፈው ቆመዋል ። በሚላሉ የሰው እጆች ላይ ፣ በሚዝሉ የሥጋ ለባሽ ክንድ ላይ የተሳፈራችሁ አሁኑኑ ካልወረዳችሁ ፣ ለራሳችሁም ለሚወዱአችሁም ማፈሪያ ትሆናላችሁ ። እግዚአብሔር ብዙ ነገሮችን በትዕግሥት ያልፋል ፣ ከንቱ ትምክሕትን ግን ፈጥኖ ያዋርዳል ።

በዓለም ላይ ክብር ከሸሸ በኋላ እንደ ገና የመመለሱ ነገር ከባድ ነው ። “ቆብ የሚቀደደው አንድ ጊዜ ነው” ይላሉ ። እግዚአብሔር የሰጠንን ዕድል በአግባቡ ካልተጠቀምን እንደገና ላይኖረው ይችላል ። ተራሮች ወደ ባሕር ልብ ሲወሰዱ አብረው የተሻረኩ ባለጠጎችና ኃያላን ሊጮኹ ይችላሉ ። እግዚአብሔር ሲጥል የሚያነሣ የለምና ጩኸታቸው ከንቱ ሆኖ ይቀራል ። የጠለቀችን ፀሐይ ማንም ብርቱ ሊያወጣት አይችልም ፣ የጠለቀ ዕድልም በማንም ብርታት አይመለስም ። ዕድል ከሄደ አይመለስም ። መልካም ሰውም ከሄደ አይመለስም ። እግዚአብሔር ዕድልና መልካም ሰው ሲሰጠን ፈጣንና ብልህ መሆን አለብን ።

ነቢዩ ዳዊት በሌላ ስፍራ፡- “አንተን ተስፋ የሚያደርጉ አያፍሩም በከንቱ የሚገበዙ ያፍራሉ” ብሏል። (መዝ. 24 ፡ 3 ።) በነቢዩ ኢሳይያስ እንዲህ ብሏል፡- “እኔንም በመተማመን የሚጠባበቁ አያፍሩም።” (ኢሳ. 49 ፡ 23 ።) ዳዊት ሳኦልን ተመክተው የነበሩ ሲወድቁ ፣ የንጉሥ ልጅ ቁራሽ ሲያርበት ፣ አገር የመራው ንጉሥ ቀባሪ ሲያጣ ፣ ልዑላን በዱር ሲቀሩ ፣ ልዕልቶች የአሽከር መጫወቻ ሲሆኑ አይቷል ። እርሱም በዘመኑ ሁሉ በሌላ በመመካት እግዚአብሔርን ላለማሳዘን ጥሯል ።

በመቀጠልም፡- “ተራሮችም ከኃይሉ የተነሣ ተናወጡ ።” አለ ። የአዋቂዎች እውቀት አለማወቅ ሆነ ፣ የባጠጎች ወርቅ ወደ ዝገት ተለወጠ ፣ ዝነኞች መኖሪያቸው ዋሻ ሆነ ፣ ይሰጡ የነበሩ የልመና ዕድልም ተነፈጉ ፣ ሰው ሁሉ ይሸታቸው የነበሩ ልብሳቸው በላያቸው ላይ አለቀ ። ሰውን ከአንበሳ ጋር እያታገሉ ይዝናኑ የነበሩ ፣ በዕብደት ተቀጡ ። በእግዚአብሔር ኃይል ፊት የቆመ አንድም ብርቱ የለም ። እግዚአብሔር ሲነሣ በፊቱ የሚቆም ጀግና የለም ። የሁልጊዜውን ጎበዝ እግዚአብሔርን ተተገኑ ።

ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ታኅሣሥ 18 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ