ዓለም የጥበቃ ስፍራ ናት። ጥበቃም ለአንድ ቀን ቆሞ አያውቅም። ይመጣል የሚሉትን ነገር ግለሰቦች፣ መንግሥታት ይጠብቃሉ። ጥበቃ ባይኖርም ሕይወት ብዙ ጣዕም አይኖራትም ነበር ። 5500 ዘመን የሰው ልጆች ቡሩኩን መሢሕ ሲጠብቁ ነበር ። እርሱ ቀጥሮ አይቀርምና የማርያምን ሥጋ ለብሶ ተገለጠ። የመጀመሪያ ምጽአቱን አጠናቅቆ ሲሄድ በዚያው ሰዓት እመጣለሁ ጠብቁ ብሎ አሁንም ለጥበቃ አስገዛን (የሐዋ. 1:11)። ላለፉት ሁለት ሺህ ዓመታት ቤተ ክርስቲያን ሙሽራዋን የምትጠብቅ ሙሽራይት ናት። ጥበቃ አያልቅም። በጥበቃና በፍጻሜው መካከል ብዙ ዓይነት ነገሮች ይከሰታሉ። ብዙ ጨለማ ፣ ብዙ ኀዘን፣ ብዙ ሰቆቃ ይኖራል። መጠበቅ ዋጋ ያስከፍላል።
የዛሬ ሕፃናት ዘመናዊ ነገር ላይ ተጠምደው እናታቸው ስትሄድም ስትመጣም ትዝ አይላቸውም። “አንተ ሰላም አትለኝም ወይ?” ተብለው በግድ ተስበው ይስማሉ፣ እርሱም ከልባቸው አይደለም። የሚጠብቁት ነገር ስለ ሌለ መደነቅና መደሰት አልቻሉም። ልባቸው ሙቀት የለውም። እኛ ባደግንበት ዘመን ገበያ የሄደች እናታችንን በር ላይ ቆመን እንጠብቅ ነበር። መጠበቃችንን የሚያረሳሳብን ምንም ነገር የለም። ልባችን ይፈራል፣ የምንለያይ እየመሰለው ትንሹ ጭንቅላታችን ይወጠራል። እንባ እንባ ይለናል። በመንገድ የሚያልፉት “ምን ሆነህ ነው የምታለቅሰው?” ይሉናል። መልሳችንን ሰምተው “አይዞህ ትመጣለች” ብለው ያጽናኑናል። ማልቀሳችንን አይስቁበትም። ተገቢ እንደሆነ ያ ትውልድ ያምን ነበር። አዎ ያደግነው በመጠበቅ ነው ።
ንጉሡ እንዲወርዱ ብዙ ተደከመ። ንጉሡ ወረዱ ያስብነው መና ግን አልወረደም። ንጉሡ ያንን ሁሉ ተቃዋሚ ውኃ እንዳይረጭበት ይከለክሉ ነበር። ተዉ የማይል ገዳይ መጣ። አህያ ተማላ ጅብ አወረደች እንዲሉ ። ጠብቀን ነበረ ፣ ግን አላገኘንም። “ደርግ ይውረድ እንጂ ሰይጣን በዙፋን ተቀምጦ ይግዛን” ተብሎ ነበር። የሚለዋወጡ ሰዎች እንጂ የሚለወጥ ነገር ታጣ። የጠበቅነው አልሆነም። መጠበቅ የሰው ታሪክ ነው ።
የሌለ ነገር መጠበቅ ግን ከባድ ነው። ድመት ስታልፍ ሌባ መጣ ብለው ሲጠብቁ የሚያድሩ ብዙ ናቸው። ትጋት አለ፣ የማይጠቅም ትጋት ነው። የሌለ ነገር መጠበቅ እንቅልፍ ይነሣል፤ ፍርሃት ይነዛል። ውጤቱም አስደሳች አይደለም። ለፍቻለሁ አይቆጨኝም አያስብልም። እንደውም ራስን መታዘብ ያመጣል። አንዳንድ በሮች ተዘግተው ሰው አለ እያልን እንጠብቃለን። ድምፃችንን ቀንሰን እናወራለን። በጥንቃቄ እንራመዳለን። ቀኑ ሲጋመስ በሩን ስንከፍት ባዶ ቤት ነው። አገር አቀፍ ስብሰባዎች፣ አጠቃላይ የሃይማኖት ጉባዔዎች በማስታወቂያ መጣሁ ተቀበሉኝ በሚለው ድምፀት ያውኩናል። ሲያልቅ ምንም የለም። ዝናብ የሌላቸው ደመናዎች ናቸው። አዎ የሰው ስብስብ ዝናብ የሌለው ደመና ነው።
የምንወዳቸው የማይወዱን፣ የምናከብራቸው ለእኛ ግድ የሌላቸው ሊኖሩ ይችላሉ:: በአንድ ሰው ፍቅር ወዳጅነት የሚቀጥል እየመሰለን ብዙ እንደክማለን ፣ የሌለ ነገር መጠበቅ ጉም መዝገን ነው። ጥፋቱ የሰዎቹ አይደለም፣ የሌለ ነገር የጠበቅን የእኛው ነው:: በዚህ ዓለም ላይ ትልቅ መክሊታችን ጊዜ ነው:: የሌለ ነገር መጠበቅ ጊዜ ይበላል። ልሂድ ባዩን መሸኘት፣ ጊዜ ገዳዩን ማሰናበት በሁለት ወገን የተሳለ ጽድቅ ነው ።
የሌለ ነገር መጠበቅ ሁልጊዜ እያፈርን እንድንኖር ያደርጋል። ከሁሉ በላይ ጊዜአችንን ያባክናል። በመጨረሻ የሐፍረት ካባ ያለብሰናል። እግዚአብሔርን መጠበቅ ግን ዋጋ አለው። እንደ አሳቡና እንደ ፈቃዱ ከሆነም ነገርን ሁሉ ለበጎ ይለውጠዋል። የመጣውን ትተን ያልመጣ መጠበቅ የሕይወት መተላለፍ ያመጣል።
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ጥቅምት 20 ቀን 2017 ዓ.ም