…ሁሉንም ቤት አንኳኩተን ብንጠይቅ አሳቡ በሙሉ የደረሰለት የለም ። በራሱ ከተደሰተ በራሱ ያዘነ ይበዛል ። ራሱን ለቆ መሄድ ስለማይችል ግን አብሮ ይኖራል ። በትዳሩ ፣ በወለዳቸው ፣ በሄደበት አገር ፣ በጀመረው ሥራ የልቡ የደረሰ ጥቂት ነው ። የነገሠውም የጰጰሰውም አሳቡ አልደረሰለትም ። እፎይ የሚያሰኝ ነገር የለም ። ለዚህ ነው የሰው ልጅ እንደ ረሀቡ ዘመን ጥጋቡ ዕረፍት ነሥቶት የሚታየው ። ፍላጎት አያልቅም ፣ ገደብ ካልሰጡት ግን ይዞ ይሄዳል ። “አሁን የልቤ ደረሰ” ብለው የሚዘምሩትን ስናይ ወደ እግዚአብሔር ቤት የመጡ ምእመናን ብቻ ናቸው ። የልብ አድርስ ፣ አንጀት አርስ ቃሉ ብቻ ነው ። የልብ ሰው ፣ የልብ አውቃ አንዱ ብቻ ነው ። ራሳችንን ገና ሳንረዳው ሰዎች አልተረዱኝም ብለን እናዝናለን ። የልባችን ያልደረሰው ክፉና ሰነፍ ስለሆንን ሳይሆን አቅማችን የተወሰነ ፍጡር ስለሆንን ነው ። አዎ የልብ ሳይደርስ ዕድሜ ይደርስ ነው ። አሳብ ጥቁር ደንጊያ ታላቅ ተራራ ነው ፣ አፈር ሥጋህ ሊሸከመው አይችልምና አውርደው ። የረሱህን በማስታወስ ፣ ስላንተ ግድ የሌላቸውን በማሰስ አትድከም ። ይሉኛልን ፈርተህ አትረበሽ ። ለመሞት እየኖርህ ለመኖር አትጨነቅ ! ያልከው አይሆንም ፣ ያለው አይቀርም ! የምትፈልገው ቢዘገይም የሚያስፈልግህ መጥቷል ! መሞትህን ረስተህ ውርስ አትመኝ ! አንድ ቀን ትሄዳለህና ክፉ ስም ጥለህ አትሂድ ! ከሁሉ በላይ ክፉ አስተሳሰብህን ተዋጋ !
እግዚአብሔር ያበርታን !
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ግንቦት 11 ቀን 2017 ዓ.ም.