የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ ዓርብ መጋቢት 6/2005 ዓ.ም.
“በእርሱም ስለ ስሙ በአሕዛብ ሁሉ መካከል ከእምነት የሚነሣ መታዘዝ እንዲገኝ ጸጋንና ሐዋርያነትን ተቀበልን፤ በእነርሱም መካከል የኢየሱስ ክርስቶስ ልትሆኑ የተጠራችሁ እናንተ ደግሞ ናችሁ” (ሮሜ. 1÷5-6)፡፡
ሐዋርያው ባለፉት ቊጥሮች ስለ ራሱና ስለሚያገለግለው ወንጌል ተናግሯል፡፡ ጳውሎስ ከተከበረበት ምኲራብ፣ ከሚወደው መምህሩ ከገማልያል፣ ስመ – ጥር ከሆነበት ከፈሪሳዊነት ወንጌልን ብሎ ተለየ፡፡ ወንጌል መለየትን ያስከትላል፡፡ የመለየትን ዋጋ ለመክፈል ከፈራን የሰማነውን ወንጌል አላመነውም ማለት ነው፡፡ ሰውዬው ወንዙ እየወሰደው አንድ ግንድ አንቆ፡– “ጌታ ሆይ አድነኝ” በማለት መጮህ ጀመረ፡፡ ጌታም፡– “እንደማድንህ የምታመን ከሆነ የያዘከውን ግንድ ልቀቅ” አለው፡፡ ሰውዬውም፡– “አንተንም አልክድም፣ ግንዱንም አለቅም” አለው ይባላል፡፡ እኛም ጌታን አልክድም፣ ግንዱንም አለቅም፣ ዓለሙንም አለቅም፣ ውሸቱንም አለቅም የምንል እንመስላለን፡፡ በጌታ መስቀል ቀኝና ግራ የተሰቀሉት ሁለት ወንበዴዎች ዘመናቸውን በሙሉ አንድ ሆነው የኖሩ፣ በእንግደል የተስማሙ ነበሩ፡፡ መስቀል ላይ ግን በክርስቶስ ተለያዩ፡፡ በመግደል የተስማሙ በሚያድነው ክርስቶስ ተለያዩ፡፡ ወንገል ይለያል፡፡ ሴት ልጅ ራሷን ለወደደችው ባሏ በቃል ኪዳን ስትለይ እያለቀሰች አባት እናቷን ትለያለች፡፡ ዘላቂው ቤቷ ባሏ ነው፡፡ እኛም ሙሽሮች ነንና መለየት ግድ ይለናል፡፡ ታዲያ ወላጆቻችንና ወዳጆቻችን በአፍ ክደን በልብ እንድናምን ይነግሩናል፡፡ ጴጥሮስም በአፍ ክዶ በልቡ አምኖ ነበር፡፡ ነገር ግን ንስሐ የሚያሻው ከሃዲ ሆነ፡፡
የምንማረው በአስተሳሰብም፣ በአኗኗርም ለመለየት ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ሰዎች ተለውጣችኋል ሲሉን እንደነግጣለን፡፡ በእርግጥ ተለውጠናል፡፡ ጴጥሮስ በሁለንተናው ከገዳዮች ጋር ቢመሳሰልም አነጋገሩ ግን ክርስቶስን ይመስል ነበር፡፡ የክርስቶስ አሻራ ክደንም ጨርሶ አይለቅም፡፡ አዎ ለዚህ ጌታ ጳውሎስ ተለየ፡፡
ሐዋርያው በቁ. 4 ላይ ስለ ወንጌል ይናገራል፡፡ በወንጌል ማመን ግድ ነው፡፡ የአገሩን ሕገ መንግሥት ያልተቀበለ የአገሩ ዜጋ ለመሆን ቢጠይቅ ጥያቄው ተቀባይነት አያገኝም፡፡ ወንጌልም የእግዚአብሔር ሕገ መንግሥት ናት፡፡ የሰማይ ዜጋ ለመሆን ወንጌልን መቀበል ግድ ይላል፡፡ ሰዎች በሀልወተ እግዚአብሔር ሊያምኑ ይችላሉ፣ በእግዚአብሔር መኖር ማመን ብቻውን ግን ወደ መንግሥቱ አያስገባም፡፡ በወንጌል ማመን ግድ ይላል፡፡ እግዚአብሔር ፍጹም አምላክ ብቻ ሳይሆን ፍጹም አዳኝም ነው፡፡
ሐዋርያው በሀልወተ እግዚአብሔር ብቻ ሳይሆን በሞተውና በተነሣው ጌታ ማመን እንደሚገባ ተናገረ፡፡ መታዘዝ ብቻውን ዋጋ እንደሌለው በእግዚአብሔር ፊት የተወደደው መታዘዝ በእምነት የሆነ መታዘዝ መሆኑን ይገልጻል፡፡ እንደውም ያለ እምነት የሚደረግ ነገር ሁሉ ኃጢአት ነው /ሮሜ. 14÷23፤ ዕብ. 11÷6፤ ሮሜ. 1÷17/፡፡ “በእርሱም ስለ ስሙ በአሕዛብ ሁሉ መካከል ከእምነት የሚነሣ መታዘዝ እንዲገኝ …” ይላል (ቁ.5)፡፡ መታዘዝ ብቻውን በቂ አይደለም፣ መነሻው እምነት መሆን አለበት፡፡ እግዚአብሔርን የማያምኑ ግን በሰብአዊ ርኅራኄና ጨዋነት የተሞሉ ሰዎች አሉ፡፡ በሚሊየን ለድሃ የሚመጸውቱ አያሌ ናቸው፡፡ ነገር ግን እምነት የላቸው፡፡ የሂንዱ፣ የቡዲዝም ሃይማኖት ተከታዮች የረቀቁ ነገሮችን ሳይቀር ለመታዘዝ ይተጋሉ፡፡ በመንገድ ላይ ያለችን አንዲትን ትል ረግጠው እንዳይገድሉ ባዶ እግራቸውን ይሄዳሉ፡፡ ሰይጣንም ለስሙ ይታዘዛል፡፡ ይፈራል፣ ይንቀጠቀጣል፡፡ ስሜታዊ እምነትም አለው (ያዕ. 2÷19)፡፡ እግዚአብሔር የሚፈልገው ግን ከእምነት የሚነሣ መታዘዝን ነው፡፡ እግዚአብሔር የድርጊቱን ያህል ድርጊቱ የተፈጸመበትን ልብ ያያል፡፡
“ … ጸጋንና ሐዋርያነትን ተቀበልን” (ቁ.5) ይላል፡፡ ጸጋንና ሐዋርያነትን የተቀበለው በአሕዛብ ሁሉ ከእምነት የሚነሣ መታዘዝ እንዲሆን ነው፡፡ ዛሬ ጸጋና ሐዋርያነት ሁለቱ ነገሮች አብረው መገኘት አልቻሉም፡፡ ጸጋው ያላቸው ኃላፊነቱን አልያዙም፡፡ ሐዋርያ ነን የሚሉት ጸጋ የላቸውም፡፡ ወደ ሹመት ሊያደርሰን የሚገባው ጸጋው መሆን ነበረበት፡፡ ያ ስላልሆነ ሹማምንት ሞልተዋል ባለ ጸጎች (ጸጋ ያላቸው) ግን አይደሉም፡፡ የቤተ ክርስቲያን መስፈርቷ ጸጋና መንፈሳዊነት ሳይሆን እንግሊዝኛ እየሆነ መምጣቱ ልብ ያለውን ያሳዝናል፡፡ ቤተ ክርስቲያን በሙያ እንጂ በጸጋ ማመን ካቃታት አደጋ ውስጥ ናት ማለት ነው፡፡ መንፈሳዊ ሹመትን ጵጵስናን ሳይቀር እንደ ሲሞን መሠርይ በገንዘብ ለመግዛት የሚፈልጉ ፈልተዋል /የሐዋ. 8÷14-24/፡፡ በርግጥ አንዳንዴ ሹመት ከሰው ቢገኝም እንኳ ጸጋ ግን ከእግዚአብሔር ነው፡፡ አዎ ቤተ ክርስቲያን ወደ ጸጋ አስተዳደር መግባት ያስፈልጋታል፡፡
“በእነርሱም መካከል የኢየሱስ ክርስቶስ ልትሆኑ የተጠራችሁ እናንተ ደግሞ ናችሁ” (ቊ.6)፡፡ ከአእላፋት መካከል መመረጣቸውን እየተነገራቸው ነው፡፡ እኛ ራሳችንን ብናጭ ጌታ ግን ካልተቀበለን ዋጋ የለውም፡፡ ከእኛ እሺታ በላይ እርሱ እኛን መምረጡ ዋጋው ከፍ ያለ ነው፡፡ ወደዚህ ዓለም ስንመጣ በመቶ ሚሊየን ከሚቆጠር የወንድ ዘር አንደኛ ወጥተን እንደሆነ ሁሉ ወደ ክርስቶስ ስንመጣም ከብዙዎች መካከል ነው፡፡ በማኅፀን የፈጣሪነቱን ሥራ እንዳየን፣ በጥሪው ደግሞ የአዳኝነቱን ምሥጢር ዓይተናል፡፡ የተጠራነው የክርስቶስ እንድንሆን ነው፡፡ አንድ አጭር ምሳሌ ብንጠቅስ በገበያ ሥፍራ ያለ ዕቃ የራሱ ነው፡፡ አምሮና ተውቦ ተቀምጧል፡፡ ጥቅም አይሰጥም፡፡ ገዢው ሲመጣ ግን ለተሠራበት አገልግሎት ይውላል፡፡ ሻጩ ምነው ከእጄ በወጣልኝ ይላል፣ ገዢው ግን ከእጄ ባልወጣብኝ እያለ ዘብ አቁም ይጠብቀዋል፡፡ ክርስቶስ በደሙ እስኪገዛን ያማርን ግን የማንጠቅም ደግሞም በነጋዴዋ ዓለም ሥር ነበርን፡፡ ክርስቶስ በደሙ ከገዛን በኋላ ግን የምንጠቅም ብቻ ሳይሆን ዋስትና ያለን ሆነናል፡፡ መላእክቱም ይጠብቁናል፡፡ የእግዚአብሔር ንብረት ነንና፡፡ “ኃጢአተኛ ነን” ትሉኝ ይሆናል፡፡ አዎ የተበላሹ ዕቃዎችም ይጠበቃሉ፡፡ በተበላሸው ዕቃ ላይም የሚወስነው ባለቤቱ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ለራሳችን አይደለንም፣ ለገዛን ጌታ እንኖራለን፡፡ የገዛን ባለው ገንዘብ ሳይሆን ራሱን አስይዞ ነው፡፡ ታዲያ ራሱን ለሰጠን ከዚያ ያነሰውን መስጠት ነውር ነው፡፡ ፍቅር የሚቀበለው ራሱን ነው፡፡
“በእግዚአብሔር ለተወደዳችሁና ቅዱሳን ልትሆኑ ለተጠራችሁ በሮሜ ላላችሁት ሁሉ ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን” (ቁ.7)፡፡
“በእግዚአብሔር የተወደዳችሁ” የሚለው ቃል ልዩ ነው፡፡ ሕይወት ያገኘነው እኛ እግዚአብሔርን በወደድንበት ፍቅር ሳይሆን እግዚአብሔር እኛን በወደደበት ፍቅር ነው፡፡ ወዶ የሚያድን እርሱ ብቻ ነው፡፡ ሊተርክ የሚገባውም የሚያድን ፍቅር ያለው ክርስቶስ ብቻ ነው፡፡ ፍቅር በመስቀል ላይ ተገልጦ የልብ–ወለድ ፍቅር ማሰስ የሚገርም ነው፡፡ የሰው ልጅ ጉዞ ከአካል ወደ ጥላ መሆኑ ያሳዝናል፡፡ የተጨበጠውን ፍቅር ትቶ ያልተጨበጠውን መከጀል አሳዛኝ ነው፡፡ አዎ የፍቅር ጀማሪው እርሱ ነው፡፡ እኛ ምእመናንን ሰላምታ ስንሰጥ፡– “እግዚአብሔርን የምትወዱ” እንላለን፡፡ ጳውሎስ ግን ወዳጅ እግዚአብሔር መሆኑን ይናገራል፡፡ “በእግዚአብሔር ለተወደዳችሁ”
ጳውሎስ ከሰላምታው በፊት ሌላ አንገብጋቢ ነገር ይናገራል፡፡ “ቅዱሳን ልትሆኑ ለተጠራችሁ” ይላል (ቁ.7)፡፡ የጥሪው ግብ መቀደስ ነው፡፡ የማይረሳ ነገር በመሆኑ ከሰላምታ በፊት ያነሣዋል፡፡ ከሰላምታ በፊት የምንናገረው ነገር እጅግ ብርቱ ነገር ነው፡፡ የተጠራነው ለመዘመር ለማስቀደስ ብቻ ሳይሆን ለመቀደስም ነው፡፡ ተቀድሶ ማስቀደስም ክብሩ ትልቅ ነው፡፡
“ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን” (ቁ.7)፡፡
እግዚአብሔር አብን አባት አለው፡፡ ክርስቶስ ኢየሱስን ጌታ አለው፡፡ አባት የወለደ፣ የቤቱ መሪ ነው፡፡ ጌታ ደግሞ የአገር መሪ ነው፡፡ አባት ያለው ልጅ፣ ንጉሥ ያለው ሕዝብ ዋስትና ይሰማዋል፡፡ እግዚአብሔር ከቤት እስከ አገር ዋስትናችን ነው፡፡ ታዲያ አባት እንዳለው ልጅ ሙቀት ይሰማናል? ወይስ እንደ ሙት ልጅ ሆድ ይበሰናል? ንጉሥ እንዳለው ሕዝብስ በመተማመን የምንመላለስ፣ ደግሞ ሥርዓት ያለን ነን?
“ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን” (ቁ.)፡፡ ጸጋ ይቀድማል ሰላም ይከተላል፡፡ ጸጋ መዳናችን ነው፡፡ ጸጋ በሌለበት ሰላም ሊኖር አይችልም፡፡ መዳን ባልቀደመበት ሕይወትም ሰላም የለም፡፡ ቃሉን ስንሰማ ጊዜያዊ ዕረፍት ቢሰማንም የሰላም መሠረቱ ግን ድኅነተ ነፍስ ነው፡፡ ይህንንም መልእክት ለምትከታተሉ በሐዋርያው ቡራኬ እንመርቃችኋለን፡– “ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን”
ይቀጥላል