የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የሐዋርያው ጳውሎስ መልእክት ወደ ሮሜ ሰዎች ትርጓሜ (ክፍል 2)

                       የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ ረቡዕ የካቲት 6/2005 ዓ.ም.
የመልእክቱ ዓላማ
ባለፈው መልእክታችን የፀሐፊውንና የተደራስያኑን ማንነት፣ የመልእክቱን መቼት ወይም የትና መቼ? እንደ ተጻፈ አጥንተናል፡፡ በክፍል ሁለት ጥናታችን ደግሞ የመልእክቱን ዓላማና ልዩ ባሕርያት እንዲሁም የመልእክቱን አከፋፈል እናጠናለን፡፡
        እግዚአብሔር ቃል ወፍ ዘራሽ ወይም የፈላስፎች ስሜት አሊያም የሥነ ጽሑፍ ውጤት አይደለም፡፡ የእግዚአብሔር ቃል የእግዚአብሔር እስትንፋስ፣ የአፉ ቊራጭ የልቡ መስተዋት ነው፡፡ እያንዳንዱ ክፍል ብቻ ሳይሆን እያንዳንዱ ነቁጥ የራሱ የሆነ ሰማያዊ ድምፅ አለው፡፡ ታዲያ የሮሜ መልእክት ዓላማ ምንድነው? ሐዋርያው ጳውሎስ ይህንን መልእክት ለመጻፍ ያነሣሣው፡-
1-     እነዚህ ምእመናን የታወቀ አገልጋይ ወይም ከሐዋርያት አንዱ እንዳገለገላቸው ምንም ማስረጃ የለም፡፡ ነገር ግን የታወቀ መልእክት ባለቤት ሊያደርጋቸው ጽፏል፡፡ የሮሜ መልእክት በዘመናት ሁሉ ድንቅ መልእክት፣ የመንፈሳዊ አብዮትም መነሻ ነው፡፡ ለክፍሉ አመልካች ቃል ተብሎ በብዙ አዋቂዎች የተሰየመው “በወንጌል አላፍርም” የሚለው መሪ ቃል ነው /ሮሜ 1÷16/፡፡ ጳውሎስ የሮሜን ሰዎች እያየ የጻፈው መልእክት ቢሆንም መንፈስ ቅዱስ ግን እኛን እያየ ያጻፈው መልእክት ነው፡፡
2-    ሕይወታቸው ተናጋሪ ስለ ነበር ሐዋርያው ደስታውን ለመግለጥ መልእክቱን ጽፏል /ሮሜ 1÷8/፡፡ ዓለም ሁሉ ቃላቸውን ቢቃወምም ኑሮአቸውን ግን መቃወም አይችልም፡፡ ዓለምን ዝም የምናሰኘው በኑሮ ምስክርነት ነው፡፡  
3-   ሐዋርያው የዚያን ጊዜ የምድር ጥግ የነበረችውን ስፔንን የመጎብኘትና ወንጌልን የማድረስ ዕቅድ ነበረው፡፡ በዚያው የሮሜን ቤተ ክርስቲያን ስለሚጎበኝ መልእክቱን እንደ አምባሳደር አድርጎ ልኮታል /ሮሜ 15÷28/፡፡ ሐዋርያው እስከ ዓለም ዳርቻ ያቅዳል፡፡ እኛ ግን ስለ አጥቢያው ምእመን እንኳ ግድ የለንም፡፡ ወንጌላችን እስከ ቤተሰባችን እንኳ አልደረሰም፡፡ ሐዋርያው እንዳሰበው የወንጌል መልእክተኛ ሆኖ ወደ ሮም አልገባም፡፡ ነገር ግን እስረኛ ሆኖ ገባ /የሐዋ. 28÷16/፡፡ በ67 ዓ.ም. በሮም ከተማ በሰይፍ ሰማዕትነትን ተቀበለ፡፡ እንዳሰብነው አይሆንም፡፡ እግዚአብሔር ያሰበው ብቻ ይሆናል፡፡ ለሙሽርነት ያሰብነው ቀን የሰማዕትነት ቀን ቢሆንም እግዚአብሔር ከፈቀደው እጅግ መልካም ነው!
የሮሜ መልእክት ልዩ ባሕርያት
   የሮሜ መልእክት ወጥ ከሆኑት የሐዋርያው ሁለት መልእክታት አንደኛው ነው፡፡ ሁለተኛው ወጥ መልእክት ስለ ክርስቶስ ታላቅነት የሚናገረው የዕብራውያን መልእክት ነው፡፡ የሮሜ መልእክት ደግሞ ስለ ጽድቅ ጠቅላላ አሳብ የያዘ ወጥ መልእክት ነው፡፡ የሮሜ መልእክት ልዩ ባሕርያት አሉት፡-

1.     ሁለቱን ሕዝቦች ማለት አይሁድና አሕዛብን አድራሻ ያደረገ መልእክት ነው፡፡ ለምሳሌ፡- የዕብራውያን መልእክት አይሁድን አድራሻ ያደረገ መልእክት ሲሆን የገላትያ መልእክት ደግሞ አሕዛብን አድራሻ ያደረገ ነው፡፡ የሮሜ መልእክት ልዩነታቸውን በክርስቶስ ላስወገዱ፣ ክርስቶስ የአንድነት ምክንያት ሆኖላቸው ተባብረው ለሚያመልኩ ምእመናን የተጻፈ ነው፡፡
2.    መልእክቱ ወጥ መልእክት ነው፡፡ እንዲህ ያለ ወጥ መልእክትን የምናገኘው ከላይ እንደጠቀስነው በዕብራውያን መልእክት ውስጥ ነው፡፡ የዕብራውያን መልእክት ከክርስቶስ ለሚሸሹ ምእመናን ማስጠንቀቂያ ሆኖ የተጻፈ ሲሆን የሮሜ መልእክት ግን ወደ ክርስቶስ ለሸሹ ምእመናን የተላከ የጽናት መልእክት ነው፡፡ ጽናት የሚኖረው ላመኑበት ነገር በቂ ዕውቀት ሲኖር ብቻ ነውና ሐዋርያው የጽድቅን መነሻ እስከ ግቡ አስፍሮላቸዋል፡፡
3.    ለአድናቆት የተጻፈ መልእክት ነው፡፡ ከመልእክታቱ እረኞችን ለመምራት የተጻፉ አሉ፡፡ እረኛውም እረኛ ያስፈልገዋልና፡፡ ለምሳሌ 1ኛና 2ኛ ጢሞቴዎስ እንዲሁም የቲቶ መልእክታት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ለተግሣጽም የተጻፉ አሉ፤ ለምሳሌ፡- 1ኛ ቆሮንቶስ፣ የገላትያና የዕብራውያን መልእክታት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ የሮሜ መልእክት ግን በዝና ደስ ላሰኙት፣ ላመኑበት ነገር ለኖሩት ምእመናን የተጻፈ ነው፡፡ ያስደሰቱን ወገኖች እንዳስደሰቱን እንዲቀሩ ልንጸልይላቸውና በዕውቀት ልንገነባቸው ይገባናል፡፡ ይህ ሐዋርያዊ ጥበብ ነው፡፡
የሮሜ መልእክት በእነዚህ ሦስት ነጥቦች የተለየ ባሕርይ አለው፡፡ ቀጥሎ የምናየው የመልእክቱን አከፋፈል ነው፡፡ መልእክቱን በንባብ አንድ ጊዜ ብትዘልቁት እጅግ መልካም ነው፡፡ አንድን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ነጥሎ ማጥናት የተሻለና ሥነ ሥርዓት ያለው አጠናን ነው፡፡ ለክፍሉ ርዕስ ቢሰጠው መልካም ነው፡፡ የሮሜ መልእክት ርዕስ ይሰጠው ከተባለ “የጽድቅ መልእክት” ወይም “ጦማረ ጽድቅ” መባል ይችላል፡፡
የሮሜ መልእክት ዋና ዋና አከፋፈል
የሮሜ መልእክት 16 ምዕራፎች ያሉት ሲሆን በሦስት በሦስት ምዕራፎች ይከፋፈላል፡፡
ከምዕ. 1 እስከ 3 ÷20 ስለ ሰው ኃጢአተኝነት
ከምዕ. 3÷ 21 እስከ 5 ስለ እግዚአብሔር ጽድቅ
ከምዕ. 6 እስከ 8 ስለ ቅድስና
ከምዕ. 9 እስከ 11 ስለ እስራኤል ውድቀትና ትንሣኤ
ከምዕ. 12 እስከ 14 ስለ ክርስቲያናዊ አኗኗር
ምዕ. 15-14-33 የመልእክቱ ማጠቃለያና ሐዋርያዊ ዕቅድ
ምዕ. 16 ሰላምታና መሰናበቻ
ዝርዝር አከፋፈል
ምዕ. 1 እስከ 3 ÷19
ስለ ሰው ኃጢአተኝነት
ምዕ. 1 ስለ አሕዛብ ዓመፃ
ምዕ.2 ስለ አይሁድ ውድቀት
ምዕ. 3 ስለ መላው የሰው ልጅ ኃጢአት
ምዕ. 3÷21-5
ስለ እግዚአብሰሔር ጽድቅ
ምዕ. 3÷ 21-31 የጽድቁ መሠረት
ምዕ. 4 የጽድቁ መገኛ
ምዕ. 5 የጽድቁ ብልጫ
ምዕ. 6-8
ስለ ቅድስና
ምዕ. 6 የቅድስና ምሥጢር
ምዕ. 7 ከኃጢአት ኃይል መዳን
ምዕ. 8 ቀዳሹ መንፈስ ቅዱስ
ምዕ. 9-11
ስለ እስራኤል
ምዕ. 9 የእስራኤል ምርጫ
ምዕ. 10 የእስራኤል መጣል
ምዕ. 11 የእስራኤል መዳን
ምዕ. 12-14
ስለ ክርስቲያናዊ አኗኗር
ምዕ. 12 ክርስቲያን በግል ሕይወቱ
ምዕ. 13 ክርስቲያን በዜግነቱ
ምዕ. 14 ክርስቲያን በቤተ ክርስቲያን
ምዕ 15-16
ምዕ. 15 ምክርና የሐዋርያው ዕቅድ
ምዕ. 16 የስንብት ሰላምታ
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም መምጣት ያስፈለገው ሰው ሁሉ በኃጢአት ሞት ስለተፈረደበት ነው፡፡ እርሱ መጥቶ ዕዳችንን ከፈለ፣ በሚመጣውም ብቃታችን ራሱ ሆነ፡፡ የማዳኑ ሥራም በቅድስና አኗኗር በሕይወታችን ይገለጣል፡፡ ከክርስቲያን የሚጠበቅ ነገር አለ፡፡ ከፖለቲከኛ የሚጠበቅ ነገር እንዳለ ሁሉ ከክርስቲያንም የሚጠበቅ ነገር አለ፡፡ ክርስቲያን በራሱ ፊት፣ በመንግሥት ፊት፣ በምእመናን አንድነት ፊት በእውነተኛ ታማኝነት መመላለስ አለበት፡፡ የሮሜ መልእክት ይህንን አሳብ ጠቅልሎ የያዘ ነው፡፡
የሮሜ መልእክት አስተዋጽኦች፡-
1.     ጽድቅ ያስፈለገበት ምክንያት ሰው ሁሉ ኃጠአተኛ በመሆኑ ነው ይላል፡፡
2.    የጽድቁ መገኛም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ እርሱም የእግዚአብሔር ጽድቅ ተብሏል፡፡
3.    ጽድቁን የምንቀበልበት እጅ እምነት ነው፡፡
4.    ጽድቅ ዓላማ አለው፡፡ የጽድቁ ዓላማ የእኛ መቀደስ ነው፡፡
5.    ቅድስና እንደ ጽድቅ ቅጽበታዊ ሳይሆን ዕለት ዕለት የሚያድግ ሀብት ነው፡፡ ለመጽድቅ ክርስቶስ እንዳስፈለገን ለመቀደስ መንፈስ ቅዱስ ያስፈልገናል፡፡ የሁሉም ነገር ክብሩ እምነት ነው፡፡ በእምነትም ጽድቅን እንደምንቀበል በእምነትም እንኖራለን፡፡
6.    እስራኤል የቤተ ክርስቲያን ባለ ውለታ ናት፡፡ የብሉይ ኪዳንና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት ፀሐፊዎች እስራኤላውያን ናቸው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ እመቤታችን ድንግል ማርያም፣ 12ቱ ሐዋርያት የተገኙት ከእስራኤል ነው፡፡ እስራኤል በጉን አርደው የጠገበው ዓለም ነው፡፡ በወንጌል በኩል ራሳቸውን በደሉ እንጂ እኛን አልጐዱንም፡፡ የቃል ኪዳን ሕዝቦች ናቸውና አይወድቁም፡፡ እነርሱ ለእኛ ሰብከው አሁን ግን ወድቀዋል፡፡ ስለዚህ መላው የዓለም ክርስቲያን ለእስራኤል መጸለይና መመስከር፣ በሚቃጣባቸውም አደጋ ከጐናቸው መቆም ይገባዋል፡፡
7.    ክርስቲያን ከቤቱ እስከ አደባባይ ከግሉ እስከ ኅብረት ቅዱስ ሊሆን ይገባዋል፡፡ ልባዊ ሰው፣ መንግሥትን የማያታልል፣ በደከሙት የማይፈርድ ሊሆን ያስፈልገዋል፡፡
8.    ቃሉን ዕለት ዕለት ማንበብና ቃሉ በሚሰጠን ተስፋ መደሰት የክርስትናው ኃይል ነው፡፡
9.    ጳውሎስ ለመጨረሻ የሚሰናበታቸው የስም ዝርዝሮችን በምዕ. 16 ላይ እናገኛለን፡፡ በዚህ የስም ዝርዝር ውስጥ ልዑላንና ልዕልቶች ብቻ ሳይሆን ባሮችም በአንድነት ተጠቅሰዋል፡፡ በሰማይ የምንታወቀው በምድር በታወቅንበት ሳይሆን በክርስቶስ ብቻ ነው፡፡ በክርስቶስ ሁሉም አንድ አካል ነው፡፡ የኑሮ ደረጃ በቤ/ክ ዋጋ የለውም፡፡ ማንም በሚሊየነርነቱ ወይም በሻለቃነቱ ወደ መንግሥተ ሰማያት አይገባም፡፡ ሰማይ በእምነት የምትወረስ ናት፡፡ የሮሜ መልእክት እነዚህን አስተዋጽኦዎች የያዘ ድንቅ መልእክት ነው፡፡ ምሥጢርን የሚገልጥ አምላክ በሰማይ አለ፡፡ ይኸው እንክፈተው፡-
ምዕራፍ አንድ
                                                                       ይቀጥላል
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ