ሕይወት በሥነ ሥርዓት የምትገለጥ ፣ የምታበራ የመለኮት እቅድ ናት ። ተፈጥሮ በስምምነት የሚኖረው ሥነ ሥርዓት ስላለ ነው ። የተፈጥሮን ውበት ያየነውም በሥነ ሥርዓቱ እርጋታ ነው ። ሥነ ሥርዓት ሌላውን ሳያውኩ የራስን ሥራ መሥራት ነው ። ሥነ ሥርዓት ሳይጨነቁ ተግባርን መወጣት ነው ። ሥነ ሥርዓት ከሌሎች ጋር ያለንን ግጭት የሚቀንስ ፣ በቦታችን እንድንገለጥ የሚያበረታታ ፣ ያለ ቦታችን ደግሞ ለባለ ቦታዎች ስፍራ እንድንለቅ የሚመክረን ትልቅ መምህር ነው ። ሥነ ሥርዓት ካለ የዕዝ ሰንሰለት ይኖራል ። ብዙ ራስ ያለው አካል ተግባሩን መፈጸም እንደማይችል ፣ ሥነ ሥርዓትም አንድ አዛዥና ትእዛዝ ሰሚ የአካል ክፍሎችን የሚያደላድል ነው ። ብዙ ራስ ያለው አካል ብዙ ትእዛዝ ይቀበላል ። አንድ የአካል ክፍል ብቻ ያለውም ትእዛዙ አይሰምርም ። በአንድ ሰው ላይ ንጉሥ የሚሆን የለምና ። ሥነ ሥርዓት ዘመናዊው ዓለም የሚመራበት ትልቁ ተዳሳሽና ረቂቅ ጎዳና ሆኗል ። ሥነ ሥርዓት ልክ እንደ ጨው የማይገባበት ነገርና ቦታ የለም ። በሁሉ ቦታ ሥነ ሥርዓት ያስፈልጋል ። ሥነ ሥርዓት ከሌለ ስብሰባ ተጀምሮ አይፈጸምም ። ሰውም በጤና ዕድሜውን አይፈጽምም ። የቤተ ክርስቲያን አምልኮም ትልቅ አደጋ ውስጥ ይገባል ።
ሥነ ሥርዓት ለዛሬው ትውልዳችን በእጅጉ ያስፈልገዋል ። አንዳንድ ታናናሽ ትውልዶቻችን ከዕድሜ ማነስና ከአስተማሪ እጦት ስድ ተለቀው ይታያሉ ። ይህ መንገድ ብዙ ያሳጣቸው/ያከሰራቸው መሆኑን እንኳ መገንዘብ አይችሉም ። በዚህ ምክንያት ትልልቅ ሰዎችና ትልልቅ በረከቶች ሲሸሹአቸው ግራ ይጋባሉ ። ሥነ ሥርዓት ያለው ሰው በመብራት የሚፈለግበት ዘመን ነው ። በዕለታዊ ኑሮአችን ሥነ ሥርዓት ራስን ለመቆጣጠር ፣ የሌሎችንም ቀልብ ለመግዛት ያስፈልገናል ። ሥነ ሥርዓት አንዲት ቤተ ክርስቲያን ለመቀጠልም ለመፍረስም ምክንያትዋ ሊሆን ይችላል ። አንዲት አገርም ሥነ ሥርዓት ከሌለ በወታደር ብዛት ህልውናዋን ማስቀጠል ፣ በዘፈንና በቀረርቶም ነገ ላይ ማድረስ አትችልም ። ለዚህች ዓለም ቀጣይነት ሥነ ሥርዓት እስትንፋስ ነው ። ፊት ለፊታችሁ ምራቅ የሚተፋ ሰው ያበሳጫችኋል ። በጣም እየጮኸ የሚያወራ ሰው ሰላም ይነሳችኋል ። ስለዚህ ሥነ ሥርዓትን ትፈልጋላችሁ ማለት ነው ። አንድ የእርዳታ ተቋም ሂዳችሁ ኃላፊዎቹ በአራዳ ቋንቋ ሲናገሩ ብትሰሙ የያዛችሁትን እርዳታ ኪሳችሁ ከታችሁ ትመለሳላችሁ ። ስለዚህ ሥነ ሥርዓት ካያችሁ ልባችሁ ይራራል ፣ እጃችሁ ይሰጣል ማለት ነው ። ፀጉሩ የተንጨባረረ ፣ ልብሱ የተተለተለ የባንክ ሠራተኛ ካያችሁም ገንዘባችሁን ለማስቀመጥ ትፈተናላችሁ ። ስለዚህ የአለባበስ ሥነ ሥርዓት ትፈልጋላችሁ ማለት ነው ።
ሥነ ሥርዓት ገና ከጠዋቱ ልጆች ሊለማመዱት የሚገባ ይህችን ዓለም የሚከፍቱበት ቁልፍ ነው ። ጨዋ ልጅን የማይወድደውና የማይስመው የለም ። በልጆቻችሁ ሥነ ሥርዓት የእናንተ ብቃት ይታያል ። ሥነ ሥርዓት ወደ ኋላ ተመልሶ አስተማሪውን እንዲመሰገን ያደርጋል ። ሕፃናት ሥነ ሥርዓትን መማር አለባቸው ። የመጀመሪያው በቀላሉ ይይዙታል ። ሁለተኛው ታግለው ከመማር ይድናሉ ። የተለቀቀ ሰውነት እየሰፋ ይሄዳልና የልብስ ዓላማው ሰውነትን ለማረቅም ነው ። ያልታረቀ/ ያልተያዘ የሰውነት ክፍል እየገዘፈ ይመጣል ። ጫማ ካላረግን እግር ትልቅ ይሆናል ። ሕፃናት ሥነ ሥርዓት የሚማሩት ከከሰሩ በኋላ እንዳይባንኑ ነው ። ብዙ ሰው ነቅቷል ። ግን ብዙ ዕድሎችን አበላሽቷል ።
ለትምህርት አይረፍድም ። እስክንሞት ድረስ የመማርና የመለወጥ ዕድል አለን ። ቢሆንም የተማርነውን በሌሎች ላይ ተርጉመን ፣ ተባርከን ለበረከት እንድንሆን ዕድሜ ያስፈልጋል ። በጌታ ቀኝ የተሰቀለው ወንበዴ የማመን ጊዜ ነበረው ፣ ፈያታዊ ዘየማን የምግባር ጊዜ ግን አላገኘም ። ድሆችን ለመርዳት ፣ የቀማውን ለመመለስ ጊዜ አልነበረውም ። የክርስቶስ ደም ዘላለማዊ ካሣ ስለሆነ ገነት ገብቷል ። የእግዚአብሔር ዓላማው እንድናምን ብቻ ቢሆን ባመንን ቀን በሞት ይወስደን ነበር ። ዓላማው ኖረን በጎ ለመሥራትና ለመመስከር ስለሆነ ያቆየናል ። አዎ ለሥነ ሥርዓት አይረፍድምና አሁኑኑ መነሣት ያስፈልጋል ። በዚህ ዓለም ላይ የጊዜ አጠቃቀም ፣ የወዳጅ አያያዝ ፣ የገንዘብ ድልድል ፣ የንጽሕና መንገድ ፣ የሰላምታ ፣ የቤተሰብ ምሪት ሥነ ሥርዓቶች አሉ ። የአምልኮ ፣ የአመራር ፣ የአነጋገር ሥነ ሥርዓቶች አሉ ። የአካሄድ ፣ የአረማመድ ፣ የአለባበስ ፣ የአመለካከት ሥነ ሥርዓቶች አሉ ። እነዚህን ሥነ ሥርዓቶች ከያዝን ለማዳበር ፣ ካላወቅናቸው አውቀን ለመኖር መነጋገር አስፈልጎናል ። ይህንንም በታላቅ አክብሮት እናቀርባለን !
እግዚአብሔር ያግዘን
ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
መጋቢት 4 ቀን 2016 ዓ.ም.