የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የሕይወት ሥነ ሥርዓት (15)

12- የመጣህበትን አትርሳ

ሕይወት መንገድ ነው ። መንገድ የመጣንበት ደግሞም የምንሄድበት ነው ። ሀብት ቢነጥፍ ፣ ጉልበት ቢከዳ ፣ ወዳጅ ጠላት ቢሆን ሕይወት ይቀጥላል ። ሁሉም ሰው የራሱ የሆነ ሕይወት አለው ። በእግዚአብሔር ፈቃድ የጀመረች ሕይወቱ በእርሱ ፈቃድ ትቆማለች ። ከበሽታ የተነሣ ቢመረር ፣ ከማጣት የተነሣ ቢያለቅስ ፣ ከወዳጅ ሞት የተነሣ ቢከፋው ሕይወት ትቀጥላለች ። አቀባበሉ ግን ቀጣዩን ብርሃን ወይም ጨለማ ያደርገዋል ። በአንድ ዓይነት መከራ ውስጥ የሚያልፉ ሁለት ሰዎች አንዱ ቢስቅ ሌላው ቢያለቅስ ጉዳዩ የአቀባበል ነው ። አቀባበሉ ያቀለዋል አሊያም ያከብደዋል ። ያመንነውን እንወርሳለንና “ይህ ክፉ ነገር ለበጎ ነው የመጣው” ስንል በጎ ይሆናል ። አቀባበል ጨለማውን ብርሃን ያደርጋል ። መንገድ ከፍታም ዝቅታም አለው ። ሕይወት መንገድ ናትና የክብር ዘመን እንዳለ ሁሉ የውርደት ዘመንም አለ ። አልጫ አልጫ የሚል ቃል ተናግረን እንደ ጥቅስ የሚነገርበት ዘመን አለ ። የጥበብ ቃል ተናግረን “ምነው ሞቶ ባረፈው” የምንባልበት ዘመን አለ ። አንዳንድ ሁኔታዎች መታገል ሳይሆን መታደል የሚያመጣቸው ሊሆኑ ይችላሉ ።

ተራራ የወጣው መንገደኛ ቁልቁለት እንደሚወርድ እርግጠኛ ነው ። ከተራራ ቀጥሎ ተራራ አይመጣምና ። የከበረም መዋረዱ አይቀርም ። “ፖለቲከኛና አትሌት በቃህ ካልተባሉ አያቆሙም” ይባላል ። እንደ ከበሩ ዞር ማለት ትልቅ ጥበብ ነው ። ከሐር መነሳንስ ወደ ጭቃ ጅራፍ ሳይለወጥ ዞር ማለት አዋቂነት ነው ። ይልቁንም በአገራችን ወረት በዙፋን ተቀምጦ እየገዛን ይመስላል ። “አንቱ” ያልነውን ሰውዬ “አንተ” ለማለት እንቸኩላለን ። መንገድ ተመዝማዛ ነው ። ቀጣዩ አልታይ እያለን የምንጨነቅበት ፣ ተስፋ ዘይቱ እንዳለቀ መቅረዝ ጭል ፣ ጭል የሚልበት ጊዜ ጥቂት አይደለም ። ተስፋ መቍረጥም የሕይወት አንድ አካል ነው ። ያልገባን ነገር ቢኖርም “እግዚአብሔር አዋቂ ነው” ማለት ያሳርፋል ። “እግዚአብሔር አዋቂ ነው” ማለት “እግዚአብሔር ያውቅልኛል” ማለት ነው ። መንገድ ሸካራ ነው ። ውስጣችን በሰዎች ክፋት የሚበከልበት ፣ ጥርጣሬ ቀናችንን የሚዋጋበት ጊዜ ብዙ ነው ። ሰዎችን ይቅር ለማለት ከራሳችን ጋር ግብ ግብ ውስጥ የምንገባበት ፣ ቂመኝነትን ዳግም ላለመጎዳት የሚጋረድ ጋሻ አድርገን የምንመለከትበት ጊዜ አያሌ ነው ። “ተበድዬስ ይቅር አልልም” እያልን እንዘፍናለን ። ይቅር የምንለውማ ስንበደል ነው ። ፍቅር የመበደል አጥር ሲሻገር እውነተኛ ይሆናል ።

ሕይወት መንገድ ነው ። መንገድ መነሻ አለው ፣ መንገድ መድረሻ አለው ። እግዚአብሔርን ማመን ያስፈለገን መነሻና መድረሻ ያለው ሕይወት ለመያዝ ነው ። እግዚአብሔርን ካላመንን ሕይወታችን መነሻና መድረሻ የሌላት ፣ መሐል ባሕር ላይ ያለ መቅዘፊያ የተለቀቀች ጀልባ ትሆናለች ። የመጣንበት የምንሄድበትን ይወስነዋል ። የመጣንበትን በትክክል ማሰብ ከቻልን ምስጋና በአፋችን ይሞላል ። ሰውን መበደል እንጸየፋለን ። ሌሎችን ለመርዳት እንነሣሣለን ። መካሪ ሁነን አዲስ ትውልድን እናበረታታለን ። ግፍን እንጸየፋለን ። ማንንም አንንቅም ። አዎ ሕፃናት ነበርን ። ሕፃናትን መውደድና ማክበር አለብን ። አዎ ዕራቁታችንን ተወልደናል ። ስለዚህ ድሀ ነበርኩ ማለት የሚያሳፍር አይደለም ። ያለ ፍትሕ ታስረናል ። ስለዚህ ያለ ፍትሕ ሌሎችን መጉዳት አይገባንም ። አንድ ድቃቂ ሣንቲም ሊቸግር እንደሚችል ኑሮአችን ምስክር ነው ። የመጣንበትን ብናስብ እጆቻችን ለመርዳት ይዘረጉ ነበር ።

አዎ የመጣህበትን አትርሳ ። የመጣኸው ካፈር ነው ። አንድ ቀን ወደ አፈር ትመለሳለህና ኩራትን ተው ። ፊደል ለማወቅ ብዙ ወራት የፈጀብህ ፣ በብዙ ጥረት አዋቂ የሆንህ ፣ የብዙዎችን ጉልበት የጨረስህ ነህና ሰውን “ደንቆሮ” ብለህ ለመሳደብ አትድፈር ። ዕድሉን ቢያገኝ ሁሉም ሊቅ ይሆን ነበር ። ያደግህበት ሰፈር ዛሬ ካየሃቸው ውብ ከተሞች የሚበልጥ ትዝታ ያለው ነውና ያደግክበትን ቀዬ ዞር ብለህ ተመልከት ። ያሳደጉህ እናቶች ፣ ዛሬም ረሀብ ዘመድ ሆኖ አልላቀቅ ያላቸው የአባትህና የእናትህ ጓደኞች አሉና ሄደህ ጠይቃቸው ፣ ካለህ ላይ አካፍላቸው ። ትንሹ ማሙሽ አድገህ ለመስጠት በመብቃትህ ፈጣሪያቸውን ባንተ ምክንያት ያመስግኑት ። መምህራኖችህ ዛሬ ከእነርሱ የበለጠ እውቀት ብትይዝም የወጣህባቸው መሰላል ናቸውና አክብራቸው ። ዋጋቸውንም ሂደህ ንገራቸው ። የወጣህበት መሰላል ለመውረድም ይረዳልና ወጣሁ ብለህ ገፍተህ አትጣለው ። አንተን አንቱ ያሰኘህ ሕዝብ ነውና ሕዝብህን አትናቅ ። ሕዝብ ያንተ ሎሌ ሳይሆን አንተ የሕዝብ አሽከር መሆንህን እመን ። የሥልጣን በትር አንድ ቀን ከእጅ ያመልጣል ። የደጁን ስትገፋ ልጅህ እንደ አቤሴሎም ለሞት ይፈልግሃል ። ሥልጣን ፀሐይ ነው ። ምንም ቢደምቅ መጥለቁ አይቀርም ። አዎ የድሀ ልጅ ነበርህና የመጣህበትን አትርሳ ። በማጣት ዘመንህ ፣ በእስር ወራትህ የገባኸውን ቃል ኪዳን አትዘንጋ ። ዛሬ ሽቱ ስለተቀባህ ሰው ሁሉ የሚሸት መስሎህ አትጸየፈው ። የአንድ ቀን ውኃ ስታጣ አንተም ለመበላሸት ቅርብ ነህ ። የመጣህበትን አትርሳ ። ይህችን ከተማ ስትቀላቀል የነበረህን መደናገር አትዘንጋ ። ስለዚህ ማንንም መጤ ብለህ አትናገር ። ሁሉም ሰው መጤ ነው ። አንድ ቀን ይሄዳል ። በዚህ ዓለም ላይ መሰንበት እንጂ መቅረት የለም ።

የመጣህበትን አትርሳ ። እግዚአብሔር ብቻውን አስተማረኝ ብለህ ያስተማሩህን አትካድ ። እግዚአብሔር ብቻውን ረዳኝ በሚል ዘይቤ የሰውን ውለታ አታጥፋ ። የእናቴን ጡት አልጠባሁም ፣ የማንም ውለታ አላለፈብኝም ብለህ አትገበዝ ። ያልተቀበልከው ምንም ነገር የለም ። ከተቀበልህም የምትመካበት አንዳች ነገር የለህም (1ቆሮ. 4 ፡ 7) ። የዛሬ ስኬትህ የሁልጊዜ ስኬት አይደለምና እንዳረጀ ወዳጅ በበላህበት ቤት ጓሮ አትለፍ ። እንደ ጎርፍ በመንገድ ያገኘኸውን ተሸክመህ አትጓዝ ። አንገት የተሠራው ለጌጥ ሳይሆን ዞሮ ለማየት ነው ። ከስንት ሞት አምልጠህ ፣ የወዳጅህን ሞት አትመኝ ። ካልጨመሩበት ይቀንሳልና ወዳጅህን ወዳጅ አገኘሁ ብለህ አትግፋው ። ወረት የሰይጣን ልጅ ያደርጋል ። እወድሃለሁ ያለህ ሁሉ አይወድህምና ወላጆችህን አትግፋ ። “የወረት ውሻ ስሟ ወለተ ጴጥሮስ ነው” ይባላል ። እፍ ለማንደድ ፣ እፍ ለማጥፋት ነውና ዛሬ ካገኘኸው ጋር እፍ አትበል ። የፊት ወዳጅህን ጨርሰህ ክፉ ነው አትበል ፣ የኋላው ይታዘብሃል ። አዎ የመጣህበትን ታውቀዋለህ የመጣህበትን አትርሳ ። የመጣህበት ሲጠፋህ የምትሄድበት ይጠፋሃል ። ወዳጅ በብር አይለወጥም ፣ ወዳጅ ውድ ነው ፣ በወርቅ አይለወጥም !

ከወዳጅህ ጋር ለማርጀት ያብቃህ !

ይቀጥላል

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሚያዝያ 17 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ