የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የሕይወት ሥነ ሥርዓት (16)

13- ንግግርህ ብቁ ይሁን

የሰው ልጅ ከእንስሳ የሚለየው አሳቢ ፣ ተናጋሪና ሕያው ፍጡር በመሆኑ ነው ። ጨርሶ አለመናገር ዱዳነት ፣ ያለ ዕረፍት መናገርም የተከፈተ መቃ መሆን ነው ። ዝም ያለ ሁሉ ጨዋ አይደለም ። የሚናገረው እውቀት የሌለው ሰው ዝም ይላል ። አውሬም ሲያደፍጥ ዝምታ ገንዘቡ ነው ። ስለሌላው አያገባኝም ብሎ የሚያስብ ሰው ዝም ይላል ። የርኅራኄ ወሬ የተነሣ እንደሆነ በሌላ ወሬ ያስቀይሰዋል ። የዘመኑ ወንጌል አማኝ ነን ባዮች ክፉ አትስማ በሚል መርሕ የሰው ችግር ሲሰሙ ውስጣዊ ጆሮአቸውን ይደፍናሉ ። ላለመራራት ይጠነቀቃሉ ። ብዙ ሰው ለእውነት ዝም ብሎ ለሣንቲም ይለፈልፋል ። አገር ሲወድም ዝም ብሎ ትዳሩ ሲናጋ “ሕዝብ ይፍረደኝ” ይላል ። ዝም ያለ ሁሉ አዋቂ አይደለም ። “አደራህን ንግግርህ አይጥምምና እንዳትናገር” ተብሎ በማስጠንቀቂያ የወጣ ዝም ይላል ። “አንገት ደፊ አገር አጥፊ” እንዲሉ ዝም የሚሉ ሰዎች በተንኮልና በመግደል ይናገራሉ ።

እግዚአብሔርን ለማዳመጥ ፣ የማዳኑን ቀን በተስፋ ለመጠበቅ ዝም የሚሉ አሉ ። “ብናገር ሰው ይቀየመኛል ፤ ዝም ብል እግዚአብሔር ያዝንብኛል” ብለው በመወላወል ዝም የሚሉ አሉ ። ቅዱስ ለመባል የቲያትር ዝምታ የሚለማመዱ ፣ “እርሱ እኮ ደርባባ አቡን” ይመስላል ለመባል ዝም የሚሉ ግብዞች አሉ ። ጢም አቡን ፣ ዝምታ ሊቅ አያደርግም ። መናገራቸው ለውጥ ስላላመጣ ትዳራቸው እየታወከ ፣ ልጆቻቸው አብዮት እያካሄዱባቸው ዝም የሚሉ አሉ ። ከመከራ የተነሣ ደንዝዘው “በማላውቀው ቀንና ሕይወት ውስጥ ነው የምኖረው” ብለው ዝም የሚሉ አሉ ። ዘረኞችም የአገሬ ሰው የሚሉት ሰው እስኪመጣ ዝም ይላሉ ፣ ከዚያ በኋላ የዘመኑ ልሳን ያቀልጡታል ። የሚገርመው ዘረኞችን እኛው ከወንዛቸው ልጅ አስተዋውቀናቸው በቋንቋቸው መናገር ጀምረው ይርሱናል ፣ ቀጥሎ ዘመዴ እኮ ነው ብለው የአክስት ልጅ መሆናቸውን ይነግሩናል ። ዘረኞች የሚዋደዱት የሚጠሉት ወገን እስኪጠፋ ድረስ ነው ። ዘረኞች ጭንቅላታቸውን ቆሻሻ መድፊያ ያደረጉ ፣ የፖለቲከኞች ቅርጫት ናቸው ።

የሚፈልጉትን ነገር ለማግኘት ዝምታን እንደ መሣሪያ የሚጠቀሙ የአዋቂ ሕፃናት ብዙ ናቸው ። እነዚህ ሰዎች አስፈራርተው ገንዘብ ከሚቀበሉ ዘራፊዎች የሚለዩ አይደሉም ። ቁሳዊ ፍላጎታቸውን ለማሟላት የሰውን የሕሊና ሰላም ይሰርቃሉ ። ተለዋዋጭ ስሜት ያላቸው ፣ አንዴ ሳቂታ አንዴ አኩራፊ የሚሆኑ ሰዎች ከመሬት ተነሥተው ዝም ይላሉ ። እነዚህ ሰዎች አውቆ አበድ ናቸው ። ቋሚ ማንነትም ስለሌላቸው ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ሰው አልባ ይሆናሉ ። አዎ ዝምታው አንድ ዓይነት ነው ፣ ምክንያቱ ግን ብዙ ነው ።

ተናጋሪ ሰውም ሊቅ ወይም የዋህ አይደለም ። አንዳንድ ሰዎች ጆሮ ጠገብ ስለሆኑ የሰሙትን እንደ መቅረፀ ድምፅ ደግመው የመናገር ብቃት አላቸው ። “እገሌ ቢናገርም ሆዱ ባዶ ነው” ይባልላቸዋል ። እነርሱም “አንዴ ከተናገርኩ በኋላ በውስጤ ምንም አልይዝም” ይላሉ ። ጥይትም ከተተኮሰ በኋላ ቀለሃው ባዶ ነው ። ተናግረውም እንደገና በተግባር የሚበድሉ ድርብ በደለኞችና በቀለኞች አሉ ። ብቻ የሰው ክብሩ ዝምታውና መናገሩ ሳይሆን የት እንደሚናገር ማወቁ ነው ።

አንተ ግን ንግግርህ ቀና እንዲሆን ከሠላሳ በላይ ነጥቦች ተቀምጠዋል ተከተል፦ ከታገሥህ ቶሎ ቶሎ ለማቅረብ እንሞክራለን ።

ይቀጥላል

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሚያዝያ 21 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ